በአማኑኤል እህል በረንዳ እንደ ወትሮው ሁሉ ግርግሩ ደርቷል። በጠዋቱ ተነስተው ከመኪና ላይ እህል የሚያወርዱ ወዝአደሮችም ሥራቸውን ተያይዘውታል። ኩንታል የጫኑ መኪኖችም መስመር መስመራቸውን ይዘው ተራቸውን ይጠባበቃሉ።ከመኪና የሚወርደው እህል በዕድሜ ጠገብ መጋዘኖች እንደከዚህ ቀደሙ ጣሪያ ድረስ ተደርድሮ ይታያል።
እኔም ይህን ሁኔታ ሳይ ሰሞኑን በከተማችን ሲናፈስ የነበረውን የእህል ውድነት መነሻ «የእህል እጥረት ነው» የሚለው ወሬ ግራ ስላጋባኝ ነጋዴዎችን ጠጋ ብዬ ማነጋገሩን ቀጠልኩ።
እህል በረንዳ በጥራጥሬ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማራው አቶ አሸናፊ ኃይሌ እንደሚሉት፤ እህል በተለይ ደግሞ ጤፍ ከአርሶ አደሩ ነጋዴው ጋር ለመድረስ ቢያንስ አራትና አምስት የደላሎችን ሰንሰለት ማለፍ ይገደዳል። አዲስ አበባም ከደረሰ በኋላ ጥቂት ነጋዴዎች ናቸው የሚጠቀሙት። በጥቅሉ ይህን ሁሉ የድለላ ሰንሰለት አልፎ ሲመጣ እህል መወደዱ አይቀርም። ነገር ግን ሸማቹ ሂደቱን ስለማይረዳ ነጋዴውን ያማርራል።
አቶ አሸናፊ እንደሚሉት የእህል እጥረት የለም፤ ነገር ግን ሕገ ወጥ ነጋዴዎች በመበራከታቸው ምክንያት ችግሩ ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል። ደላሎች ሲፈልጉ ያከማቻሉ፣ መኪና አቁመው ይሸጣሉ፣ ለሚፈልጉት ወፍጮ ቤት ያስረክባሉ እንዲሁም በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር እንዲወጣ ያደርጋሉ።
«እኛ ሕጋዊ ነጋዴዎች ነን፤ ሆኖም ግን የሚገዛን የለም» የሚሉት አቶ አሸናፊ ይሄንኑ ሕገወጥነት ለማስቆም ለመንግሥትም ቅሬታ አቅርበው መፍትሄ እንዳላገኙ ተናግረዋል። ሥርዓት አልበኝነት ስለነገሰ ብቻ የእህል አቅርቦት ሳይጠፋ እህል መወደዱን እንደሚያስገርማቸው ይገልጻሉ።
አቶ ሀብታሙ ዘውዴ በእህል በረንዳ የጤፍ ነጋዴ ሲሆኑ የችግሩ ዋና ምክንያት ለአርሶ አደሩ ቅርብ የሆኑ ነጋዴዎች የሚፈጥሩት ችግር መሆኑን ይገልጻሉ። በሰበሰቡት እህል ላይ የሚጥሉት ዋጋ የተጋነነ መሆኑን ይናገራሉ። በየክልሉ ነጋዴዎች እህሉን በቅርብ ከአርሶ አደሩ በመሰብሰብ ያከማቻሉ ብለዋል። ይህ ሁኔታ ደግሞ እህል በበቂ ሁኔታ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገባ አድርጎታል ሲሉ ያስረዳሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድና የክስ ምርመራ ክትትል ቡድን መሪ አቶ ሀብታሙ ጥላዬ፣ በርካታ ሕገወጥ የእህል ነጋዴዎች እንዳሉ እናውቃለን ብለዋል። ከዚህ በፊት ዘላቂና ቀጣይነት ያለው ባይሆንም እርምጃ ተወስዶባቸዋል ሲሉም ያክላሉ።
ሕገ ወጥ ደላሎችን መቆጣጠር አስቸጋሪ በመሆኑና አስፈላጊው እርምጃም ባለመወሰዱ ምክንያት ሕገወጥ ደላሎች እንዲጠናከሩ ሆኗል። በሁሉም አካባቢ ያሉ ደላሎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ከኅብረተሰቡ ጋር የውይይት መድረክ አዘጋጅተው ልየታ በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የንግዱን ሥራው እንዳያስተጓጉሉ ለማድረግና ዘላቂ እርምጃ ለመውሰድ በዝግጅት
ላይ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ሀብታሙ ከዚህ በፊት የነበረው እርምጃ ዘላቂ አልነበረም። ሆኖም ግን ከፀጥታ አካሉ ጋር በመሆን አስተማማኝ እርምጃ እንደሚወሰድ ይጠቅሳሉ።
እንደ አቶ ሀብታሙ ገለፃ፤ ለእህል ዋጋ መጨመር ምክንያቱ የደላላ ጣልቃ ገብነት ብቻ ሳይሆን በእህል ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች የገዙበትን ዋጋ ሳያሳውቁ ከፍተኛ በሆነ ዋጋ ይሸጣሉ። በተመሳሳይ እህልን በመሰብሰብ የሚያከማቹ ነጋዴዎች የእህል ውድነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምር ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።በቀጣይ ሊወሰድ የታሰበው እርምጃም በሕገ ወጥ ነጋዴዎች ብቻ ሳይሆን ያለ አግባብ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎችን የሚያጠቃልል መሆኑን ይናገራሉ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2011
ሞገስ ፀጋዬ