መጋቢት 24 በኢትዮጵያ ታሪክ

ከ13 ዓመታት ወዲህ እና ከ6 ዓመታት ወዲህ መጋቢት 24 ቀን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታሪካዊ ቀን እንዲሆን አድርጎታል። የመጀመሪያው፤ ከ13 ዓመታት በፊት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበት ቀን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ መሪ ሆነው የተመረጡበት ነው። ሁለቱን ሁነቶች በዝርዝር እናያለን። ከዚያ በፊት የዚህ ሳምንት ክስተት የሆኑ ሌሎች የታሪክ አጋጣሚዎችን እናስታውስ።

ከ94 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 24 ቀን 1922 ዓ.ም ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ አረፉ። ዳግማዊ አጼ ምኒልክ በፀና ሲታመሙ ልጅ ኢያሱ ሚካኤል እንዲነግሱ ተደረገ። በነበረው የፖለቲካና የሥልጣን ሽኩቻ መጋቢት 17 ቀን 1909 ዓ.ም ልጅ ኢያሱ ሚካኤል ከሥልጣን ተሽረው ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ነገሡ። ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዋ ሴት የሀገር መሪ ሆነው በታሪክ ውስጥ ይጠቀሳሉ።

ከ133 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 25 ቀን 1883 ዓ.ም የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ባለቤት እቴጌ መነን አስፋው ተወለዱ። በያኔው አጠራር ወሎ ጠቅላይ ግዛት አምባሰል አውራጃ የተወለዱት እቴጌ መነን እናታቸው ወይዘሮ ስህን ሚካኤል ይባላሉ። ወይዘሮ ስህን እና እቴጌ መነን በተሰየሙላቸው ትምህርት ቤቶች በብዙዎች ዘንድ ይታወቃሉ።

ከ83 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም በፋሽስቱ ጣሊያን ተይዛ የነበረችው አዲስ አበባ በኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ቁጥር ስር ዋለች።

በጀኔራል ሰር አለን ጎርደን ከኒንግሃም እየተመራ በደቡብ አቅጣጫ፣ በሶማሊያ በኩል፣ የዘመተው የእንግሊዝ ጦር የኢትዮጵያ አርበኞችን እያገዘ አዲስ አበባን በመቆጣጠር ጣሊያንን ከአዲስ አበባ አስለቀቁ። በሌላ በኩል በዚሁ ቀን፣ መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም ለአምስት ዓመታት ያህል በስደት የቆዩት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ከምዕራብ አቅጣጫ በኢትዮጵያውያን አርበኞች እና በሜጀር ጀኔራል ኦርድ ቻርለስ ዊንጌት በሚመራው የእንግሊዝ ጥምር ጦር (የጌድዮን ኃይሎች) የፋሽስትን ሠራዊት ድል እያደረጉ ከሱዳን በኦሜድላ በኩል ደብረ ማርቆስ ደረሱ። ለዚህ ውለታው ይመስላል ጀኔራል ዊንጌት አዲስ አበባ ውስጥ በስሙ ትምህርት ቤት ተሰይሞለታል።

በነገራችን ላይ በደርግ ዘመነ መንግሥት የአርበኞች ቀን ይከበር የነበረው መጋቢት 28 ቀን ነበር። ከዚያ በፊት የአርበኞች ቀን ይከበር የነበረው ንጉሠ ነገሥቱ አጼ ኃይለሥላሴ አዲስ አበባ በገቡበት እና የጣሊያን ወራሪ ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ መውጣት በተረጋገጠበት ሚያዚያ 27 ቀን ነበር። ኢህአዴግ ደርግን ካስወገደ በኋላ የአርበኞች ቀን በድጋሚ ሚያዝያ 27 ቀን እንዲሆን ተደርጎ እነሆ አሁንም በዚሁ ቀን ይከበራል።

ከ7 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም ጀግናው አርበኛ ሌተናል ጀኔራል ጃገማ ኬሎ አረፉ። ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በግፍ በወረረበት ዘመን ጀኔራል ጃጋማ በ15 ዓመታቸው ዘመቱ። በዚህ በአፍላው የወጣትነት ጊዜያቸው የ3500 አርበኞች አለቃ ነበሩ። በምዕራብ ሸዋ የነበረውን የፋሽስት ጦር ሰቅዘው የያዙት ጀግናው ጃጋማ ኬሎ፤ አምስት ዓመት ሙሉ በጀግንነት ሲጋደሉ ከማሸነፍ በቀር አንዴም ቢሆን ተማርከውም ሆነ ተሸንፈው አያውቁም። በተለያዩ የጦር ውሎዎች ላይ ባደረጉት ተጋድሎ በጠላት ላይ ከፍተኛ ጀብዱን ከመቀዳጀት ባሻገር፤ በርካታ የጣሊያን የጦር አዝማቾችን ማርከው ለጨካኝ ፋሽስቶች የኢትዮጵያውያንን ርህራሄ አሳይተዋል። የማረኳቸውን በርካታ የጣሊያን ጀኔራሎችም ለእንግሊዝ አስረክበዋል።

እኚህን ጀግና አርበኛ፤ በዚሁ በሳምንቱን በታሪክ፣ በባለውለታዎቻችን እና በሌሎች ዓምዶቻችን በተለያየ ዓውድ በዝርዝር ማስነበባችን ይታወሳል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ

ከ13 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የመሠረት ድንጋዩ ሲያስቀምጡ እንዲህ አሉ። ‹‹የሕዳሴ ግድብ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የላብ ፊርማ ያረፈበት ነው። ›› እነሆ ይህ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የላብ ዐሻራ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክ ሆኖ ይታወሳል።

ዕለተ ቅዳሜ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ረፋድ፤ በያኔው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በአሁኑ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለመላው ኢትዮጵያውያን አንድ ታላቅ ብስራት ተበሰረ። ሀገራዊ አቅምን የሚያሳይ፣ የተፈጥሮ ሀብት ፍትሐዊ ክፍፍልን የሚያስተምር፣ ሰላም እና መተባበርን የሚመሰክር፣ ሕዝባዊ ጥቅምን የማሳየት ዓላማ ያለው፣ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የጥረት ዐሻራ የሚታተምበት፣ ሀገር በአንድ ልብ የሚያስብበትና በአንድ ሳምባ የሚተነፍስበት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሊገነባ የመሠረት ድንጋይ ተጣለ።

ይህ በኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን የሆነ የሕዳሴ ግድብ እንደሚገነባ ለኢትዮጵያውያን ተበሰረ። ይህን ለዘመናት የማይደፈር መስሎ የኖረ ዓባይ የቀድሞው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ደፈሩት። በንግግራቸውም እንዲህ አሉ። ‹‹…የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የላብ ፊርማ ያረፈበት ግድብ በመሆኑ የሕዳሴ ጉዟችን መሐንዲሶች እኛው፣ ግንበኞቹና ሠራተኞቹ እኛው፣ የፋይናንስ ምንጮችና አስተባባሪዎች እኛው፣ በአጠቃላይ የሕዳሴ ጉዟችን ባለቤቶች እኛው መሆናችንን የሚያሳይ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታችን ነው።» ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በኋላ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የላቡን ፊርማ በማሳረፍ፣ መሐንዲስ፣ ግንበኛና ሠራተኛ፣ የፋይናንስ ባለቤት መሆኑን አረጋገጠ።

የመንግሥት ሠራተኛው ከደመወዙ፣ ነጋዴው ከወረቱ፣ ገበሬው ከምርቱ፣ ተማሪው ከደብተርና እስኪሪቢቶው ወጪውን በመቀነስ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሕዳሴው ግድብ ባለቤት መሆኑን አስመሰከረ። በዓባይ ጉዳይ ላይ ለዘመናት ሲንከባለሉ የኖሩ ጥያቄዎች ምላሽ አገኙ። በቅኝ አገዛዝ ዘመን ዓባይ በኢፍትሐዊ ቦይ እንዲፈስ የተወሰነባቸው ውሳኔዎች በዚያች ዕለት በዚያች ቀን ዋጋ እንደሌላቸው ተረጋገጠ። ስሙ ብቻ የተረፋቸው የናይል ተፋሰስ ሀገሮች አንድም በኢኮኖሚ አቅም ማጣት፣ አንድም በአውሮፓውያን ኢፍትሐዊ ውሳኔ ከደጃቸው ለሚፈሰው ዓባይ ለበርካታ ዘመናት የበይ ተመልካች ሆነው ኖረዋል። ዳሩ ግን የቅኝ አገዛዝ ዘመን አክትሞ፣ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ዘመናቸው አለፈና ዓባይ በፍትሐዊ ቦይ እንዲፈስ ተወሰነ።

ዓባይ በወኔ እና በቆራጥነት እንደሚገነባ የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ በቆራጥ ወኔ ተናገሩ። ያኔ ባረጀ እና ባፈጀ አገዛዝ የነበረው አመለካከት ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው ወኔያቸውን አሳዩ። እስኪ በፓርላማው ውስጥ ከተናገሩት ንግግር ደግሞ ይችን እንውሰድ።

«አንዱ የግብፅ ስትራቴጂ ያው ትልቅ ወታደር አስቀምጦ ማስፈራራት ነው፤ ይህን በተመለከተ ልንከተለው የሚገባ ፖሊሲ ቢኖር አለመፍራት ነው።» ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በኢትዮጵያውያን እውን ሆነ። ግብፅ በየጊዜው የምታነሳው እንጉርጉሮ ግድቡን ለሰከንድም እንደማያስቆመው ዳግም ተረጋገጠ። ኢትዮጵያ ሰላማዊ ውይይትን ለዓለም አሳየችበት።

ከዚች ዕለት ጀምሮ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የኔ እያለ የሚጠራው ሆነ። ዓባይ የጋራ መግባቢያ፣ የጋራ ማሰቢያ፣ የጋራ ሀብት ሆነ። ኢትዮጵያ በራሷ አቅም አትገነባውም የሚለው የውስጥ ለውስጥ ሹክሹክታ አንድምታ ሳያገኝ ቀረ። በዓባይ ጉዳይ የመጣ ነገር ሁሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ በመሆኑ በጋራ ማዳመጥ ሆነ።

የመገናኛ ብዙኃን ስለ ግድቡ የሚያወሩት ወሬ በሁሉም ሰው ልብ በአንዴ መድረስ ቻለ። ምክንያቱም ስለ ዓባይ ምን ተባለ የሚለው ነገር የሁሉም ሰው ጉጉት ስለሆነ። ይህ ኢትዮጵያንን በአንድ ቋንቋ ያነጋገረ ዓባይ በሁሉም ሰው ልብ ውስጥ የደስታ ምንጭ በመሆን ኩራትን ፈጠረ። ለበርካታ ኢትዮጵያውያንም የሥራ ብቻ ሳይሆን የጥበብ ምንጭ ሆነ። ከተማሪ እስከ ተመራማሪ በዓባይ ላይ ቅኔ በመቀኘት መጠበብ ጀመሩ። ከትምህርት ቤት ሚኒ ሚዲያ እስከ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በዓባይ ላይ ምን እንጠበብ በሚል ውስጣቸውን ጠየቁ። በየመድረኮች ዓባይን የሚያመሰግኑ ስንኞች፣ ዓባይን የሚያስውቡ ዜማዎች ተፈጠሩ። ይህም ለበርካታ ወጣቶች እና ተማሪዎች የጥበብ የፈጠራ ምንጭ ሆነ።

ታላቁን የዓባይ ግድብ ከደለል ለመከላከል ሲባል ለበርካታ አርሶ አደሮች ሌላ አጋጣሚ ፈጠረ። ይህም አርሶ አደሮቹ የሚሰሩት እርከን ዓባይን ብቻ ሳይሆን የአርሶ አደሮችን የእርሻ ማሳም አፈሩን በማስቀረት በውሃ እንዳይሸረሸር እስከ ማድረግ ደረሰ።

የመገደቡ ብስራት የተነገረው ዓባይ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ሌላ የይቻላል መንፈስን እና ወኔን ፈጠረ። እንዲያ በአስፈሪነቱ ይመለክበት የነበረው ዓባይ ለካ እንዲህ በሰው ልጅ ቁጥጥር ሥር መዋል ይችላል? የሚል የይቻላል በራስ መተማመንን ፈጠረ። በቃ! የሰው ልጅ የቱንም ነገር መሥራት ይችላል አሰኘ። ግድቡ ከተጀመረ በኋላ ዓባይ የመታየት እና የመጎብኘት ዕድሉ እየጨመረ፤ በስም ብቻ ያውቁት የነበሩ በርካታ ከተሜዎች ዓባይን በአካል ሄዶ የማየት ጉጉት አደረባቸው።

ያኔ ሲጀመር 5250 ሜጋ ዋት ያመነጫል ተብሎ የታሰባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አቅሙን አሳድጎ ከፍ አድርጓል። ይህ መላው ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ለመላው ዓለም ሰላም እና አንድነትን እየመሰከረ ያለ ታላቅ ግድብ ሲጠናቀቅ የዓለምን ቀልብ በመሳብ ኢትዮጵያ የዓለም የሰላም ተምሳሌት መሆኗን በተግባር ያረጋግጣል። እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን የሚለው መሪ ቃል ይፈፀምና ሌላ እንድንጀምር ማሳያ ይሆናል።

በቅርቡ ደግሞ ኃይል የመመንጨት ብስራት ጀምሯል። በአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከዓመት በፊት እንደተነገረው፤ ይህ የኢትዮጵያውያን ዐሻራ የሆነው ግድብ የትውልድ ቅብብሎሽ ነው። ያሰቡትን (ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ)፣ የጀመሩትን (አቶ መለስ ዜናዊ)፣ እያስፈጸሙት ያሉትን (ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)) እናመሰግናለን!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You