ጠንካራ ማንነት እንዴት መገንባት ይቻላል?

አንድ ሀገር ኃያል ነው የሚባለው ምን ሲኖረው ነው? በርግጠኝነት ብዙ መልስ ይኖራችኋል። አንድ ሀገር ኃያል ነው የሚባለው በገንዘብ ትልቅ አቅም ሲኖረው፣ በርካታ የተማሩና የሥራ ፈጠራ ባለቤቶች ሲኖሩት፣ የተደራጀ የጦር አቅም ሲኖረው፣ በዲፕሎማሲው ከሌሎች ሀገራት ጋር ተግባብቶ ሲሰራ፣ ተፅእኖ ፈጣሪ ሲሆን፣ ከሁሉ በላይ ውስጣዊ መረጋጋትና ሰላም ሲኖረው፣ በተለይ ደግሞ በዛ ሀገር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ለእኩልነት፣ ለሰላምና እድገት ብለው ጠንክረው የሚሰሩ ከሆነ ነው።

ይህን በግለሰብ ደረጃ ስንወስደው ሰው እንዴት ኃያል ወይም ጠንካራ ማንነት ያለው ሊሆን ይችላል? ኃያል ሰው ማለት ከሁሉ በላይ ውስጡ የተረጋጋ፣ ውስጣዊ ሰላም ያለው፣ ከራሱ ጋር የተስማማ ነው። ከውጪው ዓለም ጋር በተለይ ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚግባባ፣ የሚስማማና ተፈላጊ ነው። በሥራው፣ በገቢው፣ በእውቀቱ፣ በመንፈሳዊ ሕይወቱ …ወዘተ በተለያዩ አቅጣጫዎች የሰላ ማለት ነው ኃያል ሰው። ጠንካራ ማንነት ያለው ነው። ጠንካራ ማንነት የሌለው ሰው ደግሞ መጀመሪያ በራሱ አይተማመንም፣ ሁለተኛ ደግሞ ሰዎች ይንቁታል፣ ይገፉታል፣ ተፈላጊ አይሆንም።

ዴል ካርኒጌ ‹‹የሰው ልጅ ትልቁ ጥማቱ ተፈላጊ እንደሆነ ማሳየት ነው›› ይላል። ታዲያ ጠንካራ ማንነት ሳይኖርህ ማን ይፈልግሃል? ዋናው ጥያቄ ግን እንዴት ያን ጠንካራ ማንነት መገንባት እችላለሁ? የሚለው ነው። እነሆ ጠንካራ ማንነት የሚገንቢያ መንገዶቹ…

1ኛ. ከውጭ መጠበቅ ማቆም

ይህ ጠንካራ ማንነት ለመገንባት የመጀመሪያው ርምጃ ነው። ውጫዊው ዓለም ተቀይሮ የእኛም ሕይወት እንደሚቀየር እናስባለን። እንዲህ ቢሆን፣ ሰዎች እንዲህ ቢያደርጉልኝ፣ ሥራ እንዲህ ቢሆንልኝ፣ ሁኔታው እንዲህ ቢሆን፣ ሀገሪቱ ሁኔታ እንዲህ ቢሆን ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ያው የሰውን ልጅ የሚያኖረው በተስፋ አይደል፤ አንድ ምሽት ዛሬ ማደሩን የማያውቅ ሰው ለዛሬ አስር ዓመት ያቅዳል። ያ እምነት ነው፤ ተስፋ ነው። ግን ተስፋህ ከንቱ መሆን የለበትም።

ተስፋህ ከንቱ መሆን የሚጀምረው መቼ መሰለህ? ሽንበቆ ከሆነ ሰው፣ ሊሰበር፣ ሃሳቡን ሊቀይር፣ ቃሉን ሊያጥፍ ከሚችል ሰው መጠበቅ ስትጀምር ነው። የሆነ ነገር ያደርጉልኛል፣ ሕይወቴን ይቀይሩልኛል፣ ወደፊት ይወስዱኛል፣ ያሻግሩኛል ብለህ ከሰዎች የምትጠብቅ ከሆነ ደካማነት ይቆጣጠርሃል። ጠንካራ አይደለህም። የብዙ ሰውን ልብ የሚሰብረው ከሰው መጠበቅ ነው። የሆነ ሰው እንዲህ ያደርግልኛል፣ ገንዘብ ይሰጠኛል፣ ይረዳኛል፣ እንደ ጀምር ያደርገኛል ብሎ ይጠብቃል። ያ ሰው ደግሞ በራሱ ዓለም ነው ያለው። ረስቶታል። ምክንያቱም ሁላችንም በራሳችን ዓለም ነን።

‹‹እንዲህ እኮ ነበር፣ ያ ነገር እንዴት ሆነ?›› ስትሉት ‹‹እንዴ የቱ? ምን ብዬ ነበር?›› ብሎ ሙልጭ አድርጎ ሊክዳችሁ ይችላል። ወይም ደግሞ ‹‹አዬ ሁኔታዎች እኮ እንደጠበኳቸው አልሆኑም፤ በቃ ምን ማድረግ ይቻላል›› ብሎ ቅስማችሁን ሰብሮትም ሊሆን ይችላል። አየህ! ሁሉም ሰው በራሱ ዓለም ላይ ነው። ያንተ ችግር ሳይሆን የሚያሳስበው ሁሉም ሰው የራሱ ችግር ነው የሚያሳስበው። እያንዳንዱ ሰው ጫማ ውስጥ ጠጠር አለ። ያንን ጠጠር ስለማውጣት ነው የሚያስበው። ያንተ ጫማ ውስጥ ያለው ጠጠርማ አንተን ነው ሊያሳስብህ የሚገባው።

ከሰዎች ብቻ አይደለም ከሁኔታዎች መጠበቅ አቁም። ነገሮች ሲረጋጉ እማራለሁ፣ እጀምራለሁ… ወዘተ አትበል። በትንሹ ጀምር። ለምሳሌ ቢዝነስ መጀመር አስበህ ከሆነ ብዙ ገንዘብ አውጥተህና ቤት ተከራይተህ አትግባ። ግን አትተኛ፤ ቁጭ አትበል። ስለቢዝነስ አጥና። ሰዎችን ጠይቅ። ከቻልክ በትንሽ ገንዘብና መጠን ቢዝነስ ጀምር። ቤት ሳትከራይ፤ ንግድ ፍቃድ ሳታወጣ ሞክረው። እንደሚያዋጣህ ስታውቅ ትገባበታለህ። ያለበለዚያ አንተ ብትለወጥ፤ ባትለወጥ ጊዜው ይነጉዳል። ሁኔታው ጥሩ እስኪሆን ብለህ አትጠበቅ። ያለበለዚያ ደካማ ትሆናለህ።

2ኛ. ኃላፊነት ውሰድ

ሰበበኛ አትሁን። ያንተ ሕይወት ባለመቀየሩ፣ የምትፈልገው ነገር ባለመሳካቱ ሌሎችን ተጠያቂ አታድርግ። በቤተሰቤ ምክንያት ነው፣ በሀገሬ ምክንያት ነው፣ በእናቴና በአባቴ ምክንያት ነው የሚል ብዙ ነው። አንዳንድ ሰው እድሉን ያማርራል። ሌላው ደግሞ ፈጣሪን ሳይቀር ይወቅሳል። በሱ ምክንያት እኮ ነው፣ ስንቴ ጠይቄዋለሁ፣ እምቢ ብሎኝ እኮ ነው ብሎ የሚያለቅስ ብዙ ሰው አለ። አንተ ግን ሰበበኛ መሆን የለብህም። ደካማ የምትሆነው ሰበበኛ ከሆንክ ነው።

አንተ ጋር ያለው ትልቁ ችግርህ በውስጥህ ነው። ነገር ግን ለማሳበብና በሰዎች ሰበብ ለማድረግ ግን ቀላል ስለሆነ ከውጭ ትፈልጋለህ። የሆነ ሰው እኮ ነው እንዳልለወጥ ያደረገኝ፣ ቤተሰቤ እኮ ነው ትላለህ። ግን ወደራስህ ተመልከት። የትኛው ሰው አንተን አስገድዶ ህልምህን እንዳታሳድድ፤ የምትፈልገውን ነገር እንዳታደርግ የከለከለህ? አንተ ራስህ አይደለህ እንዴ ያላመንክበትን ነገር ሰዎች አድርግ ሲሉህ እሺ ብለህ ያልከው። መቼ እጅህን ጠመዘዙህ፣ መቼ አስገደዱህ፣ ጥይት ደቅነው ነው እንዴ ያልፈለከውን ነገር ያስደረጉህ? በራስህ ፍላጎት ነው ያደረከው።

አየህ! ኃላፊነትን መወሰድ ማለት የራሴን ሕይወት ከፈጣሪ ቀጥሎ እኔ እቀይረዋለሁ። እስከዛሬም ያልተለወጥኩት በራሴ ምክንያት ነው። ማለት አለብህ። ይሄ ትልቅነት ነው። ትልቅ ማንነት ነው። ለምን መሰለህ? አንተ አይደለህ እንዴ ህልምህን፣ ስንት የምታምንበትን ነገር ተስፋ ቆርጠህ ያቆምከው፤ ለምን በሰው ታሳብባለህ? አየህ! የጠንካራ ማንነት ባለቤት መሆን ማለት እኔ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ፣ ሸክሙን እሸከማለሁ ማለት ነው።

ዊንሰተን ቸርችል እንግሊዞች በጣም የሚኮሩበት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መላው እንግሊዛውያንን ከሂትለር መንጋጋ ፈንቅሎ ያወጣ ነው። ይህ መሪ ‹‹ታላቅ ስትሆን ያንተ ትልቁ ሸክምህ ኃላፊነት መውሰድ ነው›› ይላል። ይህ ማለት አንድ ሰው ኃላፊነት የሚወስድ ከሆነ ኃያልና ጠንካራ ማንነት ያለው ነው ማለት ነው።

ለምሳሌ መቼም በዓለም ላይ ኃያል የምትባለው ሀገር አሜሪካ ናት። አይታችሁ እንደሆነ አሜሪካ በማያገባት ጉዳይ ሁሉ ትገባለች። የራሷን ጣጣ ጨርሳ ጣልቃ የማትገባበት ሀገር የለም። እዚህ ቅርቡ ምሥራቅ አፍሪካ ላይ እንኳን አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር መግለጫ ታወጣለች። የዓለም ፖሊስ አድርጋ ነው ራሷን የምታየው። ግን እዚህ ጋር አንድ የምንወስደው ነጥብ አለ። አሜሪካ ኃያል ሀገር በመሆኗ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ለሚያጠፉ ሀገራት ሁሉ ኃላፊነት ትወስዳለች። በማያገባት ገብታ ልታስታርቅ ትሞክራለች።

አንተም ‹‹እኔ ያልተለወጥኩት በሌሎች ሰዎች ምክንያት ነው፣ በሀገሬ ምክንያት ነው፣ በቤተሰቦቼ ምክንያት ነው፣ በጓደኞቼ ምቀኝነት ነው ካልክ ትልቁን ኃይል ለእነርሱ እየሰጠሃቸው ነው። በቃ! አንተ አትቀየርም እነርሱ ካልተቀየሩ በቀር ማለት ነው። አንተ ደካማ ነህ፣ አቅም የለህም፣ በራስህ ሕይወት ላይ ማዘዝ አትችልም ማለት ነው። እነርሱ እንዲህ ስላደረኩ ነው ያልተቀየርኩት ካልክ ለሌሎች ኃይል እየሰጠሃቸው ነው።

ስለዚህ እኔ በራሴ ጥረት ራሴን ራሴ እለውጣለሁ ስትል ኃይሉን በእጅህ አስገባሃለሁ። የመርከቡ ካፒቴን አንተ ሆንክ ማለት ነው። ለዛ ነው ኃላፊነት መውሰድ ያለብህ። ጠንካራ ማንነት፣ ተፈላጊ ሰው መሆን ከፈለክ ኃላፊነት መውሰድ አለብህ። ያኔ ለውጥ ይጀምራል። ስትለወጥ ደግሞ የናቁህ ሰዎች፣ ዞር ብለው ያላዩህ ሰዎች ምን እናግዝ፤ አብረን እንሥራ ይሉሃል። አየህ! ማንም ሰው የሚንቀሳቀስን እንጂ የተቀመጠን አይወድም፤ ስትንቀሳቀስ ነው የሥራ እድል ራሱ የሚከፈተው። ኃላፊነቱን ውሰድ። ያልተቀየርከው በሌሎች ምክንያት አይደለም። በራስህ ምክንያት ነው።

3ኛ. ተለዋዋጭ ሁን/ደረቅ አትሁን/

ለምሳሌ ኬሚስትሪ ስንማር በዚህ ዓለም ላይ ጠንካራው ቁስ ምንድን ነው ሲባል ብዙ ጊዜ መልስ የምንሰጠው አልማዝ ነው ብለን ነው። አልማዝ ከብረትና ከወርቅ ይጠነክራል። ግን ከአልማዝ በላይ የሚጠነክር ቁስ አለ። ምንድን ነው ከተባለ ውሃ ነው። እንዴት መሰላችሁ ውሃ በቀጭን ግፊት ታምቆ የሚያልፍ ከሆነ የማይሰብረው ነገር የለም። ለዛም ነው ውሃ እጅግ ኃይለኛ ነው የተባለው።

ግን እኮ ውሃ ፈሳሽ ነው፣ አቅም የለውም። ታዲያ ለምድን ነው ከአልማዝ በላይ ጠንካራ የሆነው ካላችሁ ውሃ ሁልጊዜም ተለዋዋጭ ስለሆነ ነው። ለምሳሌ ውሃ ብርጭቆ ውስጥ ሲገባ የብርጭቆውን ቅርፅ ይይዛል። ጠጣር አይደለም። ደረቅ አይደለም። ግትርም አይደለም። አንተም በሕይወትህ እንደውሃው በተለያዩ ቦታዎች ውስጥ መልመድ የምትችል፣ ራስህን የምትቀይር፣ ተራማጅ መሆን አለብህ። በቀላሉ ደረቅ አትሁን።

ያመንክበትን ነገር ለመቀየር የሚያሳምንህ ነገር ከመጣ ሰዎችን ለመስማት ክፍት ሁን። እነርሱን ካደመጥካቸው በኋላ ካሳመነህ፣ የሚጠቅምህ ከሆነ ተቀበለው፤ አድርገው። ለምን ጠላትህ አይሆንም የሚጠቅምህ ነገር ከነገረህ ስማ። ድፍን አትበል። ለምን መሰለህ? አንተ ክፍት ስትሆን አዲስ ነገር ለማወቅ፣ ለመማር ፍቃደኛ ስትሆን የሃሳብ ብፌ ታነሳለህ። የእውቀት ብፌ ታነሳለህ። ቶሎ ትለወጣለህ። በቃ! ቅርጸ ቢስ ሁን። ይህ ማለት ግን የራስህ አቋም፣ የራስህ መርህ አይኑርህ ማለት አይደለም። ግን በገባህበት ቦታ ላይ፣ በምታያቸውና በምትሰማቸው ነገሮች መርማሪና አድማጭ መሆን አለብህ።

እኔ ማንንም አልሰማም፣ አልማርም፣ አልለወጥም የምትል ሰው መሆን የለብህም። እንደውም ክፍት መሆን አለብህ። ተማሪ መሆን አለብህ። ለመማር፣ ለመለወጥ፣ ሃሳብህንና አመለካከትህ ለመቀየር ክፍት መሆን ይኖርብሃል። ሃሳብህን የማትቀይርና ግትር ከሆንክ ግን አትቀየርም፤ አትለወጥም።

4ኛ. ትጥቅህን አሟላ

ትጥቅህን በአንድ በኩል ብቻ ሳይሆን በሁሉም በኩል አሟልተህ የተሳለ ሰይፍ ሁን። ገቢህን ለማሳደግ ወጥረህ ሥራ። ገንዘብህን ቆጥብ። ለአይምሮህ ምግብ ደግሞ እንዲሆንህ የሚጠቅምህን ሁሉ ማንበብና መስማት አለብህ። ለመንፈሳዊ ሕይወትህና ለመረጋጋት ደግሞ መንፈሳዊ ሕይወትህ ላይ መጠንከር አለብህ። አካላዊ ጥንካሬና መዝናናት ላይም ማተኮር አለብህ። የቅርብ ከምትላቸው ሰዎች ጋር ጊዜህን ማሳለፍ አለብህ። ከሰዎች ጋር ባለህ ግንኙነትም ራስህ ላይ ሥራ። እነርሱን ለመቀየር ሳይሆን ራስህን ቀይር። ከዛ ይለወጣሉ እነርሱ።

ትጥቅን ማሟላት ማለት በሂደት መለወጥ ነው። በነገራችን ላይ በአንድ ጊዜ ኃያል ወይም ማንነት ጠንካራ ሰው መሆን አይቻልም። ጠንካራ ማንነት በአንዴ አይገነባም። ደረጃ በደረጃ ነው የምትጓዘው። ነገር ግን ትጥቅህን ማሟላት አለብህ። አየህ! ወታደር ወደ ጦርነት ሲሄድ አንድ ጥይት ብቻ ይዞ አይሄድም። ምክንያቱም እሷን ከተኮሰ በኋላ ይማረካል። አንተም በሕይወትህ በአንድ ነገር ላይ ብቻ ጎበዝ አትሁን። ገቢን ማሳደግ ብቻ ላይ አታተኩር። ምክንያቱም አንተ እውቀት ከሌለህና የሆነ ነገር ላይ ብልህ ካልሆንክ ትሸወዳለህ። ደሞ አትርሳ በዚህ ዓለም ትልቁ ሀብት ሙያ ነው። እውቀት ነው። ልምድ ነው። ገንዘብህ ቢጠፋ፣ ቢወረስ፣ ሀብትህ ቢቃጠል፣ ብትፈናቀል አብሮህ የሚሰደደው ሙያህና እውቀትህ ነው። ስለዚህ የማይቀየር ማንነቶች ላይ ትኩረትህን አድርግ። ራስን መገንባት ማለት እርሱ ነው።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You