የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የበርካታ ባህል፣ ታሪክና የተፈጥሮ ሀብቶች መገኛ ነው። ክልሉ የልዩ ልዩ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መኖሪያም ሲሆን፣ በመቻቻልና በፍቅር የሚኖርበት የኢትዮጵያ ክፍል ነው።
ክልሉ ከሚታወቅባቸው ባሕላዊና ታሪካዊ እሴቶቹ መካከል የቤኒሻንጉል ብሔረሰብ ባሕላዊ ቤት አሠራር ይጠቀሳል፤ በዚህ የቤት አሠራር ላይ ተመስርቶ የተገነባው ጥንታዊው የሼህ ሆጀሌ የችሎት አዳራሽም ሌላው የክልሉ ታሪካዊ ቅርስ ነው። የሼህ ሆጀሌ ችሎት አዳራሽ እና የቤኒሻንጉል ባሕላዊ ቤት አሠራር በኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ተመዝግበዋል።
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቋንቋና የጋራ ባህል እሴቶች ዳይሬክቶሬት የሼህ ሆጀሌ የችሎት አዳራሽ ታሪክ ከ1817 እስከ 1931 በሚል ያዘጋጀው ጥናታዊ ጽሑፍ አዘጋጅ አቶ ፈንታሁን ደጀን እንደገለጹት፤ የሼህ ሆጀሌ ችሎት አዳራሽ በአሶሳ ወረዳ በዓይነቱ የመጀመሪያ ከመሆኑ ባሻገር በወቅቱ የአሶሳ አስተዳደር ማዕከላዊ መቀመጫ በመሆን አገልግሏል። ሼህ ሆጀሌም ይህን ማዕከል ከማስገንባት ባለፈ በመሪነት ዘመናቸው ከዚሁ ማዕከል በመነሳት ማህበራዊ፤ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ተግባራትን በማከናወን የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱበት ነው።
የአካባቢውን ተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም የችሎት አዳራሹን ከተለመደው የወቅቱ የቤት አሠራር በማሻሻል በጡብ ማስገንባታቸው ችሎት አዳራሹ ረጅም እድሜ የቆየና በግዘፈ አካል እንዲገኝ ማስቻሉም ይጠቅሳሉ። በተለይ ፍትህ ለጎደላቸው፣ ለተጣሉ፣ ፍርድ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ በዚህ አዳራሽ ውስጥ አባቶችንና ባለሟሎቻቸውን ጭምር በማሳተፍ ማህበረሰቡን በቅንነት ያገለግሉበት እንደነበር ይገልጻሉ።
የክብ ቅርፅ ቤት
የጥናቱ አዘጋጅ አቶ ፈንታሁን፤ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በተለይም በቤኒሻንጉል ብሔረሰብ ዘንድ የክብ ቅርፅ ባህላዊ የቤት አሠራር ዘይቤ የተለመደ መሆኑን ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ አብዛኛዎቹ ብሔረሰቦች ክብ ቅርፅ ያላቸው ቤቶች እንደሚሰሩ በመጥቀስም፤ ክብ ቤት መሥራት ሰዎች ከተግባራዊ ልምዶቻቸውና ከአካባቢ ሁኔታቸው ያገኙትን ዕውቀት በመጠቀም የመረጡት መሆኑን ያብራራሉ። በክብ ቅርፅ የሚሠራ ቤት የተለያዩ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የሚገልጹት የጥናቱ አዘጋጅ፤ ክብ ቤት የተሻለ ጥንካሬ ያለው መሆኑ፤ ከጉልበትና ቁሳቁስ አንፃር በተነፃፃሪነት ወጪው ቀላል እንዲሁም ውስብስብነት የሌለውም መሆኑ ከጥቅሞቹ ጥቂቱ እንደሆኑ ይገልፃሉ። በውስጥና በውጭ ተጨማሪ ቅጥያዎችን ለመሥራት ምቹ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።
አቶ ፈንታሁን እንዳብራሩት፤ የሼህ ሆጀሌ የችሎት አዳራሽ የቤኒሻንጉል ባህላዊ ቤት ሠራርን የተከተለ ነው። በአሶሳ ወረዳ ቤኒሻንጉል የሚታየው ባህላዊ የቤት አሠራር በቅርጽ ክብ ሆኖ ለግንባታውም ጥቅም ላይ የሚውሉት ቁሳቁስ እንጨት፣ ቀርከሃ፣ ሣርና ለመምረጊያ አፈር ናቸው። የቀርከሃ ተክል በዋነኛነት ለቤት መሥሪያነት ይውላል።
የሼህ ሆጀሌ አዳራሽ ግን በወቅቱ ለዘመናዊ ቤት አሠራር ጥቅም ላይ ከሚውለው ጡብ የተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ ቅርጹና የባህላዊ ቤት አሠራር ሥርዓቱ የማህበረሰቡን ባሕልና ዘይቤ እንዲወክል ተደርጎ የታነፀ መሆኑን ተናግረዋል።
በብሔረሰቡ ዘንድ ‹‹እያንዳንዱ አባወራ የቤተሰብ መኖሪያና ሌላ ተጨማሪ የእንግዳ ማረፈያ “ሀልዋ” ይሰራል›› የሚሉት አቶ ፈንታሁን፤ ከመንደሩ /ከሰፈሩ/ ከሚኖሩ ታዋቂ ሰዎች ግቢ ከዋናው ቤት በተጨማሪ “ዴዋን’’ የተባለ ለመመካከሪያ፣ ለመሰባሰቢያና ለእርቅ መፈጸሚያ እንዲሁም ለእንግዳ መቀበያ ሆኖ የሚያገለግል ሰፊ ቤትም እንደሚሠራ አብራርተዋል። የሼህ ሆጀሌ የችሎት አዳራሽም ያንን መሠረት አድርጎ ማህበረሰቡን ለማገልገል ታሳቢ በማድረግ እንደተሠራ ተናግሯል።
ባሕላዊ የቤት አሠራር ቅደም ተከተል
አቶ ፈንታሁን እንዳብራሩት፤ ባሕላዊ ቤቱ ከመሠራቱ አስቀድሞ የሚያርፍበት ቦታ በሚገባ እንዲፀዳ ይደረጋል። በመቀጠል ለእንጨት ወይም ቀርከሃ ማቆሚያ ጉድጓድ ወደ ታች በክብ መስመር ወይም ምልክት በተደረገበት ልክ ይቆፈራል። በአብዛኛው ቋሚዎቹ ባለ ያላቸው እንጨቶች ናቸው። የጉድጓዱ ስፋትና ጥልቀት መጠን እንደ ቋሚው እንጨት ወይም ቀርከሃነትና እንደ ቤቱ ትልቅነት ደረጃ ተገምቶ የሚዘጋጅ ነው።
ቤቱ የሚያርፍበት ወለል የሚለካው በእንጨት ወይም በክንድ በተለካ ገመድ ነው። ቋሚ እንጨቶቹ ወይም ቀርከሃዎቹ ከተተከሉ በኋላ የተሰነጠቀ ቀርከሃ በተተከሉት እንጨቶች ከአንዱ በር ተነስቶ ወደ ጎን በተተከሉት ቋሚዎች እየተጠላለፈ (ከቋሚዎቹ ከአንዱ በውስጥ አቅጣጫ ከቀጣዩ ቋሚ ደግሞ ከውጭ አቅጣጫ በውስጥና በውጭ እያቀያየሩ) በማሳለፍ ከወለሉ ጀምሮ እስከ ግድግዳው አናት ድረስ በዙር እንዲቀጥል ይደረጋል። የግድግዳ ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ ተሰንጥቆና ተደራርቦ በጥቅል መልክ የተዘጋጀ ቀርከሃ በክቡ የግድግዳ አናት ቋሚ ባላዎች ራስ ላይ ዙሪያውን እንዲያርፍ ተደርጎ ልክ እንደ “ቢም” ይቀመጣል።
‹‹የግድግዳ ሥራው እንደተጠናቀቀ የጣራ ሥራው ይቀጥላል›› የሚሉት አቶ ፈንታሁን፤ የጣራ ሥራው በቀርከሃ ወራጅ ከግድግዳው ድምድማት ወይም ራስ ጀምሮ ዙሪያን ወደ ላይ ከቤቱ መካከለኛ ምሰሶ ጫፍ እንዲገጥም ተደርጎ እንደሚታሰር ይገልፃሉ። ቀጥሎም በጣሪያው ዙሪያ ወደ ጐን የተሰነጠቀ ቀርከሃ ከወራጅ ቀርከሃው ጋር እየታሰረ በተወሰነ ርቀት ዙሮ ገጠም ማገር ተሰርቶ ይጠናቀቃል ሲሉ ያብራራሉ። በመጨረሻም ጣራው በሳር እንዲሸፈን ተደርጎ ግድግዳው ከአፈር በተዘጋጀ ጭቃ ይመረጋል ይላሉ።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ የቤቱ ውስጣዊ የመሀል ዙሪያ አለፍ አለፍ ብሎ በክብ በሚተከሉ ቋሚ ወጋግራዎች ወይም ያለ ምንም ምሰሶ እንደ ቤቱ ትልቅነትና መጠን ታይቶ ይሰራል። የትላልቅ ቤቶች በረንዳው ሰፊ ሲሆን የጣራው ጫፍ ወደ መሬት አቅጣጫ ከሰው ቁመት ዝቅ ብሎ ይወርዳል። በረንዳውም በዙሪያው የእንጨት ቋሚዎች ወይም እንደ “ኮለን” የሚያገለግሉ ድጋፎች ይሰራለታል።
‹‹የቤኒሻንጉል ባሕላዊ ቤት አሠራር ዋነኛ ግብዓት የቀርከሃ ተክል ነው፤ የዚህ መነሻ ምክንያት በአካባቢው የቀርከሃ ተክል በቅርበትና በብዛት መገኘት ነው›› የሚሉት አቶ ፈንታሁን፤ ቀርከሃ ለክብ ቤት ሥራ የተመቸ መሆኑም ሌላው ምክንያት መሆኑን ያብራራሉ። ቀርከሃ በቤት ግንባታው ሂደት ከግድግዳ እስከ ጣራና የሣር ክዳን ድረስ አገልግሎት መስጠት መቻሉና፤ ለአዘጋጃጀት ለማጓጓዝና ለሥራ ያለው ቅለትም በማህበረሰቡ ተመራጭ የመሥሪያ ግብዓት እንዳደረገው አስታውቀዋል።
ሼህ የሆጀሌ ችሎት አዳራሽ መነሻ
ሼህ ሆጀሌ የችሎት አዳራሹን ያሰሩት “አጉመላ’’ በተባለ ቦታ መሆኑን አቶ ፈንታሁን ይናገራሉ። “አጉመላ’’ ትርጉሙ “አጥር ውስጥ” “ግቢ ውስጥ” ማለት መሆኑንም ይገልፃሉ። በ“አጉመላ’’በክብ ዙሪያ የተተከሉ ዛፎች መኖራቸውንም ያነሳሉ።
ከላይ በዝርዝር ለማንሳት እንደተሞከረው የቤንሻንጉል ብሔረሰብ ባሕላዊ የቤት አሠራር ዙሪያው ክብ ነው፤ ጣሪያው ደግሞ ሾጠጥ ያለ ነው። የቤቱ አካል የተዋቀረው ከቀርከሃና እንጨት ሲሆን፣ የቤቱ ዙሪያ በረንዳና የውስጡ ማዕከላዊ ክፍል ዙሪያውን የሚተከሉ ባለ “ባላ” እንጨቶች ወይም ደጋፊዎች ያሉት ነው።
የሼህ ሆጀሌ የችሎት አዳራሽ ይህን የቤኒሻንጉል ብሔረሰብን ባህላዊ ቤት አሠራር መሠረት በማድረግ በሥፍራው መታነጹን አቶ ፈንታሁን ጠቅሰው፤ የማህበረሰቡን ባህል፣ ማህበራዊ መስተጋብር እንዲሁም ወግና ልማድ እንዲያንፀባርቅና እንዲወክል ተደርጎ በአስተዳዳሪው መሠራቱን ይገልፃሉ።
በእያንዳንዱ አባወራ ወይም ቤተሰብ መኖሪያ ከዋናው ቤት በተጨማሪ አንድ የእንግዳ ማረፊያ ቤት እንደሚኖር በመጠቅስም ዋናው ቤት ቁሳቁስ፣ እህል፣ የምግብ ዝግጅት ማድረጊያና በአጠቃላይ ለቤተሰቡ መኖሪያነት እንደሚያገለግል ይናገራሉ። ከዋናው ቤት በተጨማሪ የሚሠራው ሁለተኛው ቤት “ሀልዋ” ወይም “አልሀልዋ” ተብሎ እንደሚጠራ ጠቅሰው፣ አገልግሎቱ እንግዳ የሚያርፍበት፣ አባወራ ከጎረቤት ጋር የሚጫወትበት፣ ከእንግዶች ጋር አብሮ የሚመገብበትና ቡና የሚጠጣበት፣ ምክክር የሚያደረግበት፤ በተለይም የአባዎራዎች ማህበራዊ ግንኙነት መድረክ መሆኑን ያስረዳሉ።
ከዚህ ሌላ በአንድ ሰፈር ወይም ጎረቤቶች ታዋቂ ከሆነ ትልቅ ሰው ግቢ ውስጥ ከመኖሪያው በተጨማሪ “ዴዋን” ተብሎ የሚጠራ ቤት ይሠራል። ይህ ቤት የአካባቢው ሰዎች የሚሰበሰቡበት፣ የሚወያዩበት አብረው የሚበሉበትና የሚጠጡበት፣ የሚመክሩበት እርቅ የሚፈጽሙበት፣ በጋራ የሚወስኑበት ማዕከል ነው። የችሎት አዳራሹም የማህበረሰቡን እነዚህን ሁሉ እሴቶች እንዲያቅፍ መደረጉን አቶ ፈንታሁን ይገልፃሉ።
‹‹የሼህ ሆጀሌ ችሎት አዳራሽም በቅርፅ ክብ ሆኖ ዙሪያውን የበረንዳ ቋሚዎች ያሉትና ጣራው በቀርከሃና በእንጨት የተሠራ ከፍ ያለና የአካባቢውን ባህላዊ ቤት አሠራር የተከተለ ነው›› የሚሉት አቶ ፈንታሁን፤ አገልግሎቱም ልክ እንደ ገፅታው ሁሉ በ“ሀልዋ”ና ይበልጡንም በ“ዴዋን” ከሚሰጡ አገልግሎቶች ጋር የተያያዘ መሠረት ያለው መሆኑን ያስረዳሉ።
የሼህ ሆጀሌ አልሀሰን ችሎት አዳራሽ እነዚህን አካባቢያዊ ገፅታዎችና ክንዋኔዎች ወደ ተሻለ ደረጃ በማሳደግ የተገነባ የአስተዳደርና ፍትህ መስጫ አዳራሽ መሆኑንም አስታወቆ፣ የአካባቢውን ጥሬ ሀብት በመጠቀምና በሰው ጉልበት መሠራቱ ሌላው ከባሕላዊ መሠረቱ የሚያመሳስለው መሆኑንም ያብራራሉ።
የችሎት አዳራሹ አገልግሎት
አቶ ፈንታሁን እንደሚሉት፤ የችሎት አዳራሹ የተለያዩ ግልጋሎቶችን ይሰጥ ነበር። በተለይ የአስተዳደርና የፍትህ አገልግሎት በመስጠት ይታወቃል። ሼህ ሆጀሌ ከአንድ በላይ ሚስቶች ስለነበራቸው በየሚስቶቻቸው እየተዘዋወሩ ይኖሩ እንደነበር የሚጠቅሱት የጥናቱ አዘጋጅ፤ በሚዘዋወሩባቸው የግዛት ክልሎች ለሚቀርቡላቸው አቤቱታዎችና ጉዳዮች ወዲያው መፍትሔ ሰጥተው ይመለሱ እንደነበር የተገኙ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩ ይገልፃሉ። በሌላ በኩል በመቀመጫቸው አሶሳ በችሎት አዳራሹ ቀርበው ከሚታዩ ጉዳዮች መካከል የግል ጉዳዮች፣ የባልና ሚስት፣ ከብድር አመላለስ ጋር የተያያዘ ጠብና አልፎ አልፎ ከባለቤትነት /ይገባኛል ባይነት/ ጋር የተገናኙ ክርክሮች ዋና ዋናዎቹ እንደነበሩ ይናገራሉ።
እነዚህን ችግሮች ባለጉዳዮች እንዳመለከቱ እንደነገሩ ቅለትና ክብደት እየታየ ራሳቸው ሼህ ሆጀሌ ቀጥተኛ ውሳኔ ሰጥተው ይመልሷቸው እንደነበርም አመልክተው፣ ጠንከር ያሉ ጉዳዮችና ችግሮች ሲያጋጥሙ በታዋቂ ሰዎች ማለትም የሀገር ሽማግሌዎችንና የሃይማኖት አባቶችን በማማከር የመፍትሔ ሃሳብ አቅርበው በይበልጥ በስምምነት ውሳኔ እንዲሰጥ ያደርጉ እንደነበርም አቶ ፋንታሁን አስታውሰዋል።
ይህ በቡድን ተወያይቶ ውሳኔ የሚሰጥበት አሠራር “ሹራ” ተብሎ እንደሚጠራም ይገልፃሉ። ለሼህ ሆጀሌም ሆነ በአጠቃላይ “ሹራ” ለተባለው አማካሪ ቡድን የሚቀርቡ ጉዳዮች በተጎጂ ግለሰቦች፤ ቅሬታ በተሰማቸው ሰዎችና፤ በተዋረድ በሚገኙ “መክ” “ሙቀደም” “ሸህ” ተብለው በሚጠሩ የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ሊፈቱ ያልቻሉ ግጭቶችና በእነሱ አመልካችነትም ጭምር የሚቀርቡ ጉዳዮች መሆናቸውን አቶ ፈንታሁን ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተውልናል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም