‹‹ነብይ በአገሩ አይከበርም›› የሚለውን አባባል የፈጠረው ይሄው ነብይን የማያከብረው ህዝብ ነው። ሲቀጥልም ‹‹የቅርብ ጠበል ልጥ ይራስበታል›› ይላል። ይሄ አባባል ብዙም ሲባል ስለማልሰማው ትንሽ ላብራራው መሰለኝ። በአንድ አካባቢ የፈውስ ጠበል ቢመነጭ የአካባቢው ሰው ብዙም አይጠቀምበትም፤ ከሩቅ አካባቢ የሚመጣ ሰው ነው የሚፈወስበት። የአካባቢው ሰው ጠበሉን እንደማንኛውም ውሃ የደረቀ ልጥ ለማራስ ነው የሚጠቀመው። የአካባቢው ሰው ጠበል ሲያስፈልገው ወደሩቅ አካባቢ ነው የሚሄደው።
የራሳችን የሆነን ነገር እንደማናከብር ግልጽ ማሳያዎች አሉን። የግሪክ ፈላስፎችን ስም ከነሙሉ ታሪካቸው የሚያውቃቸው ኢትዮጵያዊ ብዙ ነው። የንግግሮቹ ማጣፈጫዎች ሁሉ እነዚህ የአውሮፓና የአሜሪካ ፈላስፎች ናቸው። ይሄ መሆኑ ችግር የለውም ነበር፤ ችግሩ የራሳችን የሆነን ነገር ግን እናሳንሳለን። አንድ ውይይት ላይ የሰማሁትን ቀልድ መሰል እውነታ ልንገራችሁና ወደዋናው ጉዳይ ልግባ።
አንድ ኢትዮጵያዊ ለህክምና ሆስፒታል ይገባሉ። ሆስፒታሉ ውስጥ ያሉት ሐኪሞች አንዱ ፈረንጅ አንዱ ሐበሻ ናቸው። ሰውየው ማደንዘዣ ተወግተው ታከሙ። ታክመው እንደወጡ ሐበሻው ሐኪም ስለጤንነታቸው ጠየቃቸው። ‹‹አሁንማ ሙሉ ጤናዬ ተመልሶ፤ ደህና ሆኜ! አይ ፈረንጅ! ›› ብለው ሲያደንቁ፤ ኢትዮጵዊው ሐኪም ህክምናውን ያደረገላቸው እሱ እንደሆነ ይነግራቸዋል። ይህኔ ሰውየው በስጨት ብለው ‹‹ለካ ለዚህ ነው በዚህ በጎኔ በኩል አሁንም ይወጋኛል!›› በማለት በኢትዮጵያዊው ሃኪም ላይ እምነት እንዳልነበራቸው ገልፀዋል።
አለቃ ገብረሐና ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ናቸው። የሀሳብ ሊቅ ናቸው። ዳሩ ግን አልተዘመረላቸውም። ታሪካቸው እንኳን የሚገኘው ‹‹ያልተዘመረላቸው›› የሚለው የፍጹም ወልደማርያም መጽሐፍ ላይ ነው። በእርግጥ ቀልዶቻቸውን የያዙ ሌሎች መጽሐፎችም አሉ። ጥናታዊ ጽሑፎችም አሉ። ያም ሆኖ ግን አለቃ ገብረሐና የፈላስፋነታቸውን ያህል ያልተዘመሩ ሰው ናቸው። እንዲያውም በአፈታሪክ ያሉ የሚመስላቸው ሁሉ አሉ። በአፈታሪክ ያሉ ያስመሰለው ነገር ስለእርሳቸው በጽሑፍ ደረጃ የተባለ ነገር ስለሌለ ነው። በቃል ደረጃ ግን ብዙ ተብሎላቸዋል፡፡
የአለቃ ገብረሐና ቀልዶች ቀልድ ተብለው የሚታለፉ አይደሉም። ጥልቅ ፍልስፍና ያላቸው ናቸው፡፡የሚመልሷቸው መልሶች ‹‹እንዴት በዚያ ቅጽበት ይህን ያህል ተመራመሩ!›› ያሰኛል። ብዙ ጊዜ ሰምና ወርቅ ያላቸው ናቸው። በሰሙ በወል የሚታወቅ ነገር ያወሩና በቅኔው የልባቸውን ይናገራሉ። እኛ ቀልድ አደረግነው እንጂ እርሳቸው የሚናገሩት ግን የልባቸውን ነው፤ ለማሳቅ ወይም ለማዝናናት ሳይሆን ሰዎችን በነገር ጎሸም ለማድረግ ነው፡፡
አለቃ ገብረሐና ደፋር ፈላስፋ ናቸው። ሃይማኖትና ንጉስ በማይደፈርበት በዚያን ዘመን እንኳን (አስቡት በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለት ነው) ደፍረው የሚናገሩ ናቸው። ነገሥታቱን እና መኳንንቱን ሁሉ በቅኔ እየሸፋፈኑ ይናገራሉ። እንዲያውም ከእቴጌ ጣይቱ ጋር በጣም ይጣሉ እንደነበር ይነገራል፤ እቴጌዋን በተመለከተም ነውር የሆኑ ነገሮች ሳይቀሩ ይወርፏቸው ነበር።
አለቃ ፈጣሪንም አይፈሩም። አንድ ነገራቸውም ተደጋግሞ ሲነገርላቸው ይሰማል። ‹‹ሰዎችን ‹ጠላታችሁን እንደራሳችሁ ውደዱ› ትላለህ፤ ታዲያ አንተ ለምን ኃጢያተኞችን ሲዖል ትከታለህ?›› ሲሉ በፈጣሪ ላይ ተሳልቀዋል።
አንዴ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲህ ሆነ፡፡
አለቃ በዝናብ የበሰበሰና ለአይን ማራኪ ያልሆነ የቆዳ ልብስ ለብሰው ቤተ ክርስቲያን ይገባሉ። የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋዮች ይበሳጩና ይቆጧቸዋል። ‹‹ቤተ ክርስቲያን ንጹህ ልብስ እንጂ እንዴት ይሄን ለብሰው ይገባሉ! እንዲያውም ቆዳ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አይገባም!›› ሲሉ ይቆጧቸዋል። አለቃ ሆዬ በማግስቱ በጠዋት ይሄዱና እንደ ብራና፣ ከበሮ… የመሳሰሉ የቤተ ክርስቲያን የቆዳ ውጤቶችን እያወጡ ወደ ውጭ ይወረውራሉ፤ ይህን እያደረጉ ሳለ የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋዮች መጡ። አሁንም በቁጣ ‹‹እንዴት እንዲህ ያደርጋሉ?›› ተብለው ሲጠየቁ ‹‹ምነው ትናንት ቆዳ ቤተ ክርስቲያን አይገባም አላላችሁም ነበር እንዴ?›› ብለው ተሳልቀዋል።
ምንም እንኳን ፍልስፍና ማለት ሃይማኖትን መቃወም ባይሆንም አለቃ ገብረሐና ግን እንዲህ የሚሟገቱ፤ ነገሮችን በምክንያት ለማሳመን የሚጥሩ ነበሩ። ወጣ ያለ ባህሪ ያላቸው ናቸው።
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የምናተኩረው በቀልዶቻቸው ላይ ቢሆንም ስለግለታሪካቸው ግን ከአንድ የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጽሑፍ ላይ ይህን እንውሰድ፡፡
የአባታቸውን ስም አንዳንዶች ደስታ ተገኝ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ገብረማርያም ነው ይላሉ፤ ምናልባት አንዱ ዓለማዊ ሌላው የክርስትና ስማቸው ሊሆን ይችላል። እናታቸው መልካሜ ለማ የሚባሉ ቢሆንም ታህሳስ 10 ቀን 1978 ዓ.ም በታተመ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ደግሞ የእናታቸው ስም ሣህሊቱ ተክሌ ተብሎ ተገልጿል። አለቃ ገብረሐና የተወለዱት በ1814 ዓ.ም ሲሆን የትውልድ ቦታቸውም በዛሬው በደቡብ ጐንደር ዞን በፎገራ ወረዳ፣ ልዩ ስሙ ናበጋ ጊዮርጊስ አካባቢ ነው፡፡
በነገራችን ላይ የተወለዱበትን ዘመን በተመለከተም ብዙ ጊዜ የሚጠቀሰው 1814 ዓ.ም ቢሆንም ሌሎች መደበላለቆችም አሉ። ይህ የሚያሳየው እንግዲህ ታሪካቸው በትክክል እንዳልተጠና ነው። አሁን ወደ አለቃ ገብረሐና ቀልዶች፡፡
ከቀልዶች በፊት ግን አንድ ነገር ልብ መባል አለበት። አለቃ ገብረሐና አሉት እየተባለ የሚቀለደው ቀልድ ምናልባትም የእርሳቸውም ላይሆን ይችላል። አንድ ሰው በሆነ ነገር ታዋቂ ሲሆን ነገሮችን ጠቅልሎ ለእሱ መስጠት የተለመደ ነው። ያ ታዋቂ ሰው ነው ያለው ከተባለ ነገሩ ክብደት የሚኖረው ስለሚመስለንም ነው። ለምሳሌ የአቶ መለስ ዜናዊ ስም የሚቀለዱ ብዙ ቀልዶች አሉ። አንዳንዶቹን አቶ መለስ ዜናዊ ናቸው የተናገሩት ብሎ ለመደምደም ይከብዳል። ዳሩ ግን በይፋ በምክር ቤትም የሚናገሯቸው ነገሮች አስቂኝ ስለሚሆኑ ሰዎች እየፈጠሩም እንዲህ ሊል ይችላል ብለው ይቀልዳሉ፤ ያ እየቆየ ሲሄድ በትክክልም አቶ መለስ የተናገሩት ሊመስል ይችላል። እናም በአለቃ ገብረሐና ቀልዶች ውስጥም ይሄ ነገር ሊያጋጥም ይችላል።
አንዳንዶችን የአለቃ ገብረሐናን ቀልዶች ለመረዳት ልክ እንደ እርሳቸው የቋንቋ ሊቅ መሆንን ይጠይቃል። እርሳቸው በቋንቋ ነው የሚጫወቱት። ያንን ለመረዳት ቋንቋን በፍጥነት የሚረዳ መሆን አለበት። እስኪ ይህችኛዋን ቀልድ እንመልከት።
አለቃ ገብረሐና አንድ ድግስ ላይ ተጠርተው ይሄዳሉ። ሲሄዱ ለድግስ የተዘጋጀው በግ ገና አልታረደም። አለቃ በነገሩ ተበሳጭተዋል። ባለጉዳዮች በጉ ታርዶ ለምግብነት እስከሚዘጋጅ አለቃ እንዳይርባቸው በእልበት መስጠት ፈለጉ። እልበት ማለት ከባቄላ የሚዘጋጅ የማባያ(አምሳለ ወጥ መሆኑ ነው) አይነት ነው። አለቃ በእልበት ብሉ ሲባሉ እምቢ አሉ። እንግዳ ናቸውና ባለጉዳዮች እጃቸውን ይዘው እየጎተቱ ‹‹በሉ ይብሉ›› ሲባሉ አለቃ በውስጣቸው ቆጣ ብለው ‹‹አልበላም አልኩ እኮ! ዛሬ ደግሞ በጉልበት ሆነ እንዴ?›› አሉ ይባላል።
ይሄን የመሰለ ቀልድ ዘግይቶ ሲገባን ነው የሚያስቀን። ሰምና ወርቅ ያለው ሀሳብ ነው። በሰሙ መናገር የፈለጉት ‹‹አልበላም ካልኩ በጉልበት(በሃይል) ነው እንዴ የምታስበሉኝ›› ማለታቸው ነው። በወርቁ ደግሞ መናገር የፈለጉት ‹‹በግ ልበላ ነበር የመጣሁ፤ በጉ እልበት ሆነ እንዴ?›› ማለታቸው ነው።
አለቃ ገብረሐና ወስላታ እንደሆኑ ይታማሉ። ብዙ ቀልዶቻቸውም ከእንዲህ አይነት ውስልትናዎች ጋር የተያያዙ ናቸው። ከዚህ ጋር ከተያያዙት ቀልዶቻቸው አንዱን ብቻ እንውሰድና ብልጠታቸውን እንመልከትበት።
አንድ ዕለት ከቤታቸው ሴት እንግዳ መጥታ ታድራለች። አለቃ በእንዲህ አይነት ድርጊት ይታማሉ። እናም ሌሊት ተነሱና ባለቤታቸውን አስተኝተው ከእንግዳዋ ጋር ይወሰልታሉ። ይህን ሲያደርጉ ባለቤታቸው ሰምታ ታዝባ ዝም ብላለች። አለቃ ለሁለተኛ ጊዜ ሲነሱ ግን ባለቤታቸው ዝም ማለት አልቻለችም። ባለቤታቸው ቆጣ ብላ ‹‹አለቃ የት ሊሄዱ ነው?›› ስትላቸው፤ አለቃ ፈጠን ብለው ‹‹ልደግም›› አሉ ይባላል።
አሁንም በሰምና ወርቅ ሸፋፍነው ነው የተናገሩ። በሰሙ ‹‹ልደግም›› ሲሉ ዳዊት ልደግም (ላነብ) ማለታቸው ነው፤ በወርቁ ግን ‹‹በድጋሜ ልወሰልት ነዋ!›› ማለታቸው ነው።
እንግዲህ በዚያ ቅጽበት እንዴት ይሄን እንዳሰቡት ይገርማል። ባለቤታቸውን ጨዋ ነገር የሚያደርጉ በማስመሰል ዳዊት ልደግም ነው ብለው ውሸት በመናገር አታለሏቸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ምንም ሳይዋሹ በድጋሚ ልወሰልት ነው ብለው ተናገሩ። በአንዲት ቃል ውሸትም እውነትም ተናገሩ ማለት ነው። ዳዊት ልደግም ነው ሲሉ ዋሽተዋል፤ ውስልትናውን ልደግም ነው ሲሉ እውነቱን ተናግረዋል።
አለቃ ገብረሐና በሰምና ወርቅ ብቻ አይደለም የሚናገሩት። ለማንም ግልጽ የሆነ ሰምና ወርቅ የሌለው ቀልድም ይመጣላቸዋል። አለቃ አንድ ቀን ግን ራሳቸውም ተሸውደዋል። በመሸወዳቸውም እንዲህ ቀልደው ነበር።
አለቃ ዓሳማ ሰብል እየበላባቸው ተቸግረዋል። ይሄንኑ ዓሳማ ለመከላከልም ሰብሉን ጥበቃ ያድራሉ። በዚህ የተማረሩት አለቃ ግራ ቢገባቸው አንድ ሰው ያማክራሉ። ያ ሰውም ‹‹አይ አለቃ ይሄ እኮ ቀላል ነው። ሲዞሩ ማደር የለብዎትም፤ አንድ ቦታ ቁጭ ብለው ከሰብሉ ዳር እሳት እያነደዱ ማደር ነው፤ ያኔ ዓሳማው ዝር አይልም›› ይላቸዋል። አለቃም የተባሉትን አደረጉ። ከሰብሉ ዳር ሆነው እሳት ሲያነዱ አደሩ። ጠዋት ሲያዩ ግን ዓሳማው ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰብሉን ጠራርጎታል። በዚህ እየተበሳጩ ወደቤት ሲሄዱ ያ ምክሩን የነገራቸው ሰውየ አገኛቸውና ‹‹አለቃ እንዴት ነው ዛሬስ ዓሳማው?›› ብሎ ሲጠይቃቸው ‹‹ምን እንዴት ነው ትለኛለህ! እያበራሁለት ሲበላ አደረ›› አሉት ይባላል።
ከአለቃ ቀልዶች የምንረዳው ነገር አስቂኝነቱን አይደለም። ተረጋግቶ የማሰብ አቅማቸውንና ውስጣዊ ፍልስፍናቸውን ነው። የአለቃን ቀልዶች በተለያየ አጋጣሚ የምንጠቀማቸው ሀሳባችንን ስለሚገልጹልን ነው። እኝህን የአገራችን ፈላስፋ አፈታሪክ ሆነው እንዳይቀሩ ማስታወስ ያስፈልገናል። በብዙ የውጭ አገር ሰዎች የተሰየሙ ጎዳናዎች እያሉን በአለቃ ገብረሐና ስም አንድ እንኳን ጎዳና አለመሰየሙን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ታዝቦ ነበር። ለአገራችን ሊቃውንት እውቅና ልንሰጥ ይገባል!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 8/2011
ዋለልኝ አየለ