መጽሐፍት በታዳጊዎች

ሠላም ልጆችዬ እንዴት ናችሁ? ሳምንታችሁ እንዴት ነበር? በጥሩ እንዳሳለፋችሁ እገምታለሁ፡፡ ልጆችዬ ባላችሁ ትርፍ ግዜ ብዙ ነገር እንደምትሠሩበት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የምታነቡ እንዳላችሁም ተስፋ አደርጋለሁ። እሺ ልጆችዬ ጽሑፎችንስ ምን ያህሎቻችሁ ትሞክራላችሁ? አንዳንድ ተማሪዎች የፃፉትን ለወላጆቻቸው፣ ለጓደኞቻቸውና ለመምህራኖቻቸው ያሳያሉ፡፡

ይህን የሚያደርጉት ለምን ይመስላችኋል? ‹‹አስተያየት ለመቀበል፡፡›› ብላችሁ መለሳችሁ አይደል? ‹‹ጎበዞች››፡፡ ጽሑፎች ለተለያየ ዓለማ እንደሚጻፍ መቼም ታውቃላችሁ ብዬ እገምታለሁ፡፡ የተረት፣ ታሪካዊ፣ ሳይንሳዊ እና የተለያዩ ይዘት እንዲሁም መልዕክት ያላቸው መጻሕፍት ሰዎች ስለጉዳዩ መረጃ እንዲኖራቸው ያላወቁትን እንዲያውቁ፣ እነሱ ያወቁትን የተረዱትን ነገር ሌሎች እንዲያውቁላቸው ለማድረግ በመጽሐፍቶቻቸው አማካኝነት ያላቸውን ሃሳብ ለአንባቢያን ያቀርባሉ፡፡ እናም ልጆችዬ ገና በታዳጊነት ዕድሜያቸው ልጆች ቢያውቋቸው እውቀት ያገኙበታል፡፡

ግንዛቤያቸውም ከፍ ይላል፡፡ ጎበዝ ልጆች እንዲሆኑ ያስተምሯቸዋል ብለው የተለያዩ መልዕክት ያላቸውን መጽሐፍትን የጻፉት ታዲጊዎች ለእናንተ እናቀርብላችኋለን፡፡ በተጨማሪም የጻፉበትን ምክንያታቸው ምን እንደሆነ እናንተ ልጆች እንድትማሩበት ብለን አዘጋጅተነዋል፡፡ ከታዳጊ ዮሴፍ መለሰ እንጀመር፡፡ እድሜው አስራ አራት ነው፡፡ ‹‹ላሊበላ›› የተሰኘ መጽሐፍ ጽፎ ለአንባቢያን አቅርቧል፡፡

ልጆችዬ ታዳጊው ይህንን ለምን የጻፈው ይመስላችኋል? ሁሉም ልጆች ላሊበላን የማየት አጋጣሚ ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ እነርሱ ላሊበላን ማየት ባይችሉም በመጻሕፉ ግን ስለ ላሊበላ ማወቅ እና መረዳት እንዲችሉ ለማገዝ አስቦ የፃፈው ነው። ሌላኛዋ የልጆች መጽሐፍ የጻፈችው ፊርደውስ ሡልጣን ትባላለች፡፡ የአስራ አንድ ዓመት ታዳጊ ናት። የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን ‹‹ሣራ እና ቢታንያ›› የተሰኘ መጻሕፍ ጽፋለች፡፡

እርሷም መጽሐፉን የጻፈችበት ምክንያት አላት፡፡ ምክንያቷ ደግሞ ምን መሰላችሁ ልጆችዬ? ጓደኝነት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ለልጆች ለማስተማር ብላ ነው የጻፈችው፡፡ ዮናታን ልዑልሰገድ የስድስተኛ ክፍለ ተማሪ ሲሆን ዕድሜው አስራ ሁለት ነው፡፡ ‹‹እርሳስ እና እስኪሪቢቶ›› የተሰኘ የልጆች መጽሐፍ ጽፏል፡፡ ምክንያቱ ምን መሰላችሁ? ሰውን ሳናውቀው ፍርድ አለመስጠት፣ ሰውን ሳንረዳ ስለሰዎች ማንነት በመገመት አለመወሰን። እኔ እበልጣለሁ አለማለት፡፡ ሰውን እኩል መውደድ እና ከሰው ጋር ራስን አለማወዳደር እንደሚገባ ለማስገንዘብ በማሰብ ነው መጽሐፉን የፃፈው፡፡ የአስራ አንድ ዓመቱ ታዳጊ ቢኒያም መለሰ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡

የእርሱ መጽሐፍ ‹‹ሁለቱ እህትማማቾች እና ሰባት ተረቶች›› ይሰኛል፡፡ ራሱን ጨምሮ ልጆች ሥራን መውደድና መልመድ እንዳለባቸው ለማሳወቅ ነው የጻፈው፡፡ ‹‹ቅቤ እና ቋንጣ›› ይሰኛል የጻፈችው መጽሐፍ፡፡ ስሟ ደግሞ ሄመን ብሩክ ይባላል፡፡ እድሜዋ አስር ዓመት ሲሆን የምትማርበት የክፍል ደረጃዋ ደግሞ አራተኛ ነው፡፡ እርሷ ቅቤ እና ቋንጣ ብላ በሰየመችው መጻፍ ሰዎች ራሳቸውን ብቻ እየወደዱ ሌሎችን መጥላት ጥሩ እንዳልሆነ ማወቅ እንዳለባቸው ለማሳወቅ ነው፡፡ ይህንን ነገር ሰዎች እንዲያውቁት እፈልጋለሁ በማለት ጽፋለች፡፡

እርሷ የተረዳችውን መልካም ነገር ሌሎች ልጆች እንዲያውቁት ብላ የልጆች መጽሐፍ ከጻፉት ታዳጊዎች መካል አሜን ልዑል ሰገድ አንዷ ናት፡፡ አሜን ዕድሜዋ አስር ሲሆን የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ ‹‹የሁለቱ ጓደኛሞችና ቤተሰብ ታሪክ›› ይሰኛል የመጽሐፏ ርዕስ፡፡ አሜን እንደሌሎች ልጆች እርሷም የጻፈችበት ምክንያት አላት፡፡ አንድ ሰውን ለመረዳት እና ችግሩን ለማወቅ መሞከር ጥሩ እንደሆነ ለማሳወቅ አስቤ ነው መጽሐፉን የፃፍኩት ትላለች፡፡ እስካሁን ካቀረብንላችሁ በዕድሜ ትንሿ ልጅ የማርያም ብሩክ ትባላለች፡፡ ዕድሜዋ ሰባት ነው።

የአንደኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ እርሷም ‹ማርካን እና ሪማስ› በሚል ርዕስ መጽሐፍ ፅፋለች፡፡ የእርሷ ጽሑፍ ዓላማም ሰውን ሰው መሳደብ እንደሌለበት ለማሳወቅ እንዲሁም ለማስገንዘብ በማሰብ ነው፡፡ ልጆችዬ ከእነዚህ ጎበዝ ልጆች ምን ተማራችሁ? ብዙ መልዕክቶችን በመጻሕፍት አማካኝነት ማስተላለፍ እንደሚቻል እና ብዙ ነገሮችን ማሳወቅ እንደሚቻል ተረድታችኋል ብለን እንገምታለን፡፡ ልጆችዬ እናንተም እንደእነርሱ ለመጻፍ ሃሳብ ያላችሁ ካላችሁ ወላጆቻችሁን፣ ጓደኞቻችሁን እና መምህራን በማማከር እንዲሁም የጻፋችሁት ጽሑፍ ላይ ሃሳብ እና አስተያየት እንዲሰጧችሁ ብታደርጉ ውጤታማ ትሆናለችሁ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ለማንኛውም ልጆችዬ ለዛሬ በዚሁ እናብቃ አይደል? እንደተለመደው ትኩረታችሁን በትምህርታችሁ ላይ ብቻ እንድታደርጉ በማሳሰብ በዚሁ እንለያያለን፡፡ መልካም ሳምንት!!

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን መጋቢት 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You