አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ የብሔ ርተኝነት ጥያቄዎች የቋንቋ መሰረተ- ታሪካዊ ማንነቶችን በሚጠቁሙት ጥቂት የማንነት መለያዎች መካከል በመሆኑ የአሁኑን ኢኮኖሚያዊ፣ማህበረ-ቋንቋዊ ማህበረሰቦች በጋራ የመፍጠር ዋነኛ ችግር መሆኑን ምሁራን ገለጹ፡፡አዲስ ወግ አንድ ጉዳይ ‹‹ብሔርተኝነት በኢትዮጵያ›› በሚል መሪ ቃል ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ውይይት ተካሂዷል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ሳይንስ ትምህርት ቤት ውስጥ የሥነ- አእምሮ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ዳዊት ወንድማገኝ፤ የሰው ልጅ ከልጅነት ጀምሮ የማንነት ጥያቄን እንደሚያዳብር ጠቅሰው፤ የግለሰብም ሆነ የቡድን ማንነቶች በጊዜ፣ በአካባቢና ሌሎች ተመሳሳይ ሁኔታዎች ላይ የሰዎች መስተጋብር ውጤቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የግለሰቦች እና ቡድኖች ማንነት መቀበል ጤናማ ቢሆንም ጥቂት የማንነት መለያዎች ለሆኑ ጉዳዮች ብቻ ትኩረት መስጠት ጠንካራ ማኅበረሰብ ለመፍጠር አዳጋች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ሌላው የመነሻ ሀሳብ አቅራቢ ዶክተር አብዲ ዘነበ በበኩላቸው፤ ሀገሪቱ እንደ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ የመሳሰሉ ሌሎች ብዙ ገጽታዎች ያሏት ሲሆን፤ በጥቂት የማንነት ጥያቄ መንቀሳቀስ አሁን ያለውን የአመለካከት ለውጥ አይረዳም ብለዋል፡፡ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን የማንነት ጥያቄን የሚያቀርቡበት መንገድ የሚከፋፍል መሆኑንና የኢትዮጵያ የአካዳሚ መምህራን እና የፖለቲካ አመራሮች የፖለቲካ መዋቅሮችንና ስርዓቶችን የሚያካትት ስነ ምግባር መከተል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር አቶ ሙሳ አደም እንደገለጹት፤ በአሁኑ ጊዜ የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች ማንነት ላይ የተመሰረቱ ትርክቶችን በተሳሳተ መልኩ እየተረጎሙ ይገኛሉ፡፡እስከ አሁን የፖለቲካዊ ምሁራኖች ፖለቲካውን በመዘወር እርስ በእርስ ሽኩቻ ቢያደርጉም፤ የፖለቲካ ሥርዓቱና በመላው አገሪቱ ያለው የአርሶ አደሩ አኗኗር ተመሳሳይ ነው፡፡
አቶ ሙሳ፤ በኢትዮጵያ የማንነት ጥያቄ የሚስተናገድበት መንገድ የሥነ ልሳን አውድን ትኩረት ያደረገ በመሆኑ አብሮነትና አንድነትን ለሚያጎሉ ለሌሎች የማኅበራዊ ጉዳዮች ትኩረት እንዳይሰጥ ጫና አሳድሯል፡፡ የፖለቲካ ዘዋሪዎች በማኅበረሰቦች ውስጥ በብሔርተኝነት ዙሪያ ጭፍን ጥላቻ እንደ አስተያየት በመስጠት ለቅቡልነታቸው እንደሚጠቀሙበትና ይህንን ወደ ጎን በመተው ሊያቀራርብ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ቢደረግ አገሪቷንና ህዝቦቿን ትልቅ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ ማህበረ-ቋንቋዊ ጉዳዮችን እንደ በረከት በማየት አገሪቱን ወደፊት ሊያጓጉዙ የሚችሉትን ጥበቦች በመጠበቅ ጥቅም ላይ መዋል አለባቸውም ብለዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን እንደገለጹት፤ ምንም እንኳን ማንነትን ለመለየት የሚያስችል ጤናማ ሁኔታ ቢኖርም፤ ሚዛናዊ ያልሆነ ትኩረትን መዘርጋት አገሪቱን አደጋ ላይ በመጣሉ ማንነትንና ዜግነትን በተመለከተ ሚዛናዊ ባልሆነበት ሁኔታ ላይ ያለውን ክፍተት መንግሥት ገምግሟል፡፡
በመድረኩ ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 8/2011
አዲሱ ገረመው