“የኮሪደር ልማቱ ከቀድሞ የተሻለ መኖሪያ ቤት እንድናገኝ አድርጎናል ” -የፒያሳ አካባቢ የልማት ተነሺዎች

አዲስ አበባ፦ የመንገድ ኮሪደር ልማቱ ከቀድሞ የተሻለ መኖሪያ ቤት እንድናገኝ አድርጎናል ሲሉ የፒያሳ አካባቢ የልማት ተነሺዎች ተናገሩ።

የኮሪደር ልማት ተነሺ የሆኑት አቶ ግርማ ገዜ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ መንግሥት በገባው ቃል መሰረት በልማት ምክንያት ከአካባቢያችን ለተነሳን ነዋሪዎች ምትክ ቦታ በአግባቡ ሰጥቷል። በዚህም “ከቀድሞ የተሻለ መኖሪያ ቤት እንድናገኝ አድርጎኛል” ብለዋል።

በቀድሞ የመኖሪያ አካባቢያቸው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ዜጎችም የተሻለ መኖሪያ እንዲያገኙ ያስቻለ ዕድል መሆኑን አንስተው፤ አሁን የተሰጣቸው ቤት በስፋት ከቀድሞ በሦስት እጥፍ እንደሚበልጥ እና የራሱ የሆነ መጸዳጃ ቤት እንዲሁም መታጠቢያ እንዳለው ተናግረዋል።

በቅያሪ የተሰጣቸው ቤት የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን ለሽያጭ ያቀረበው ቤት መሆኑን የተናገሩት አቶ ግርማ፤ ቅያሪ ቤቱ ሁሉም ዓይነት መሠረተ ልማቶች የተሟሉለት በመሆኑ ለመኖር ምቹ ነው። ይህ እድል ቀሪ ዘመናቸውን ደስተኛ አድርጎ እንደሚያኖራቸው ነው የተናገሩት።

ልማት የሀገር ዕድገት መገለጫ መሆኑን የገለጹት አቶ ግርማ፤ ሕዝብንም ባማከለ መልኩ ሲከናወን ደግሞ ይበልጥ ደስ የሚያሰኝ ነው ሲሉ ተናግረዋል። እሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ ለዘጠና እማወራና አባዎራዎች ምትክ ቤት መሰጠቱንም ገልጸዋል።

ሌላዋ የልማት ተነሺ ወይዘሮ ሮማን ጌታቸው በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን የመንገድ ሽፋንና ዘመናዊነት እንዲሁም የትራንስፖርት ፍሰት የሚያሳድግ ነው። በተለይ በዶሮ ማነቂያ አካባቢ የነበረውን ችግር የሚቀርፍ ነው ብለዋል።

በዶሮ ማነቂያ አካባቢ ለ40 ዓመት መኖራቸውን የሚገልጹት ወይዘሮ ሮማን፤ የአካባቢው ነዋሪ ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ተጠጋግቶ ይኖር ነበር። በዚህም አብዛኛው ነዋሪ የመጸዳጃና የመታጠቢያ ቦታዎች እንዳልነበሩት ይናገራሉ። አሁን ይህ ችግር መፍትሔ ሊያገኝ ችሏል ብለዋል።

በአንድ ክፍል ቤት ውስጥ ለስምንት ይኖሩ እንደነበር የሚናገሩት ወይዘሮ ሮማን፤ መንግሥት የማልማት ሥራዎቹን ሳይጀምር ከነዋሪዎች ጋር ምክክር አድርጓል። በዚህ መሠረት በምትክ የተሰጣቸው ቤት አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች የተሟሉለት በመሆኑ ቤተሰባቸውን በደስታ እንደሚያኖር ተናግረዋል።

የልማት ኮሪደር ሥራው በዋነኛነት ከተማዋን የሚመጥን መንገዶችን የማስፋፋት ሥራ፣ ወጥና ዘመናዊ የመብራት ዝርጋታ፣ የመንገድ ዳር የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች፣ ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት፣ ሰፋፊ እና ምቹ የእግረኛ መንገዶች፣ የብስክሌት መንገድ፣ ያረጁ ሕንፃዎች ጥገና እና የማስዋብ ሥራን ያካተተ ነው።

በተጨማሪም የልማት ኮሪደር ሥራው የከተማዋን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴ የሚያሳድግ እንዲሁም ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ቅንጅት የታየበት የልማት ሥራ ነው። ይህም ስድስት ክፍለ ከተሞችን ያካልላል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን  መጋቢት 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You