አዲስ አበባ፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ይጎርፉበት የነበረው የጢስ ዓባይ ፏፏቴ የቱሪዝም መዳረሻ በፏፏቴው አቅራቢያ በተገነባው ኃይል ማመንጫ አማካኝነት የቀድሞ ዝናው እንደሌለና የአካባቢው አስጎብኚዎች እና ኅብረተሰቡ ገቢ መዳከሙ ተገልጿል።
በጉዳዩ ላይ የጢስ ዓባይ ኃይል ማመንጫ ኃላፊ እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መልስ ከመስጠት ተቆጥበዋል። የጢስ ዓባይ የቱሪስት መረጃ ማዕከል የመረጃና ሱፐርቪዥን ዋና ኦፊሰር አቶ ተስፋ አስማረ እንደገለጹት፤ ፏፏቴው በበርካታ የውጭ አገር እና አገር ውስጥ ጎብኚዎች የሚወደድ እና በሚሊዮኖች ገቢ የሚያስገኝ ቢሆንም አሁን ገቢው ቀንሷል። በ1990 ዓ.ም የተሰራው የጢስ ዓባይ ቁጥር ሁለት ኃይል ማመንጫ ግን ወደ ፏፏቴው የሚሄደውን ውሃ 80 በመቶ የሚወስድ በመሆኑ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና በኢንተርኔት የሚሰራጨው የቀደሞው ጢስ ዓባይ ምስልና ዝናው አሁን በቦታው የለም።
እንደ አቶ ተስፋ ገለጻ፤ ግድቡ ብዙ ውሃ ወስዶ የሚሰጠው ኃይል ግን 30 ሜጋ ዋት ብቻ ነው። ይህ ደግሞ የዓባይን ወንዝ እና ከሚወስደው ውሃ አቅም ጋር አይጣጣምም። በተጨማሪም ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ እና ከኃይል ማመንጫው የሚገኘውን ማመዛዘን ቢቻል የቱሪዝሙ እንደሚበልጥ ማወቅ ያስፈልጋል። ከግድቡ በፊት በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ሲጎርፉ የነበረው አሁን ግን ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ታህሳስ 30 ባለው የ2011 በጀት ዓመት ግማሽ ወቅት የመጣው ቱሪስት 27 ሺ 169 ብቻ ነው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 12ሺ 784ቱ ብቻ የውጭ አገራት ጎብኚዎች ናቸው። አብዛኛውም የአገር ውስጥ ጐብኚ 10 ብር ሲከፍል የውጭዎቹ ደግሞ 50 ብር እና ለአስጎብኚዎች ደግሞ እንደየደረጃው ተጨማሪ ይከፍላሉ።
በቡድን የሚመጡ ጎብኚዎች ሲገኙ እና ቅዳሜና እሁድ ከኃይል ማመንጫው ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር የተወሰነ ውሃ እንዲለቀቅ እንደሚደረግ የገለጹት አቶ ተስፋ፣ ቀን ቀን ጎብኚ ሲመጣ ውሃው እየተለቀቀ ምሽት ላይ ብቻ የኃይል ማመንጫው እንዲሰራ ቢደረግ ለአገር የተሻለ ገቢ ማስገኘት እንደሚቻል ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ግን ከባህር ዳር 30 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ቢገኝም መዳረሻው አሰልቺ የፒስታ መንገድ በመሆኑ ለቱሪዝም እንቅፋት ሆኖ መቀጠሉን ገልጿል።
በጢስ አባይ ፏፏቴ በማስጎብኘት ሥራ ይተዳደር የነበረው አለሙ ታዬ እንደገለጸው፤ የፏፏቴው መጠን በእጅጉ መቀነስ የብዙዎችን ወጣቶች ገቢ አሳጥቷል። ከአስር እና አስራ አምስት ዓመታት በፊት በርካታ ፈረንጆች ሲጎርፉበት የነበረው ቦታ አሁን በቂ ኃይል በማይሰጥ ግድብ አማካኝነት ተዳክሟል። በርካታ ጎብኚዎች በኢንተርኔት ካዩት ምስል ጋር አሁን ያለው አነስተኛ ፏፏቴ ሳይመሳሰል ሲቀር ጢስ አባይ አይደለም ብለው ከአስጎብኚዎች ጋር ተጣልተው ይሄዳሉ። በዚህም የበርካታ አስጎብኚዎች እና በቱሪስት ገቢ ላይ መሰረት ያደረጉ የህብረተሰቡ ክፍሎችን ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል።
የአካባቢው ነዋሪና የቱሪስት ጌጣጌጥ ንግድ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ደጌ ጫኔ እና ሙሉ ሁኔ በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ በፏፏቴው መቀነስ ምክንያት ቱሪስት ደስተኛ ባለመሆኑ እና በብዛትም ባለመምጣታቸው የእያንዳንዱ ገቢ ቀንሷል። ከአስር ዓመት በፊት በቀን 500 ጎብኚ ሲመጣ ነበር። አሁን ግን በቀን አምስትም ከመጣ እንደ ብርቅ ይታያል። ግድቡ ኤሌክትሪክ እያመነጨ ነው ቢባልም ለህብረተሰቡ ግን አልደረሰም።
በመሆኑም ከግድቡ ይልቅ ፏፏቴው ነው ለነዋሪው ጥቅም የሚሰጠው። ኅብረተሰቡ በሩ ላይ ከተሰራው ማመንጫ ኤሌክትሪክ ካለመጠቀሙ በተጨማሪ የቱሪስት ገቢውን ስላሳጣው ለግድቡ ያለው ተቆርቋሪነት አነስተኛ ሆኗል። በመሆኑም ነዋሪው የሚፈልገው ከግድቡ አነስተኛ ኃይል ማመንጨት ይልቅ ስለቱሪዝም ጥቅም የሚቆረቆው ኅብረተሰብ በዝቷል።
በጉዳዩ ዙሪያ መልስ እንዲሰጡ የተጠየቁት የጢስ ዓባይ አንድ እና ሁለት ኃይል ማመንጫ ኃላፊ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ዋናው መስሪያ ቤት ኃላፊዎች በጉዳዩ ላይ መልስ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 8/2011
ጌትነት ተስፋማርያም
ፎቶ – ሃዱሽ አብርሃ