ሮቤ፡- ‹‹በልማት እየበለፀግን በአንድነታችንም እየጠነከርን እንሄዳለን›› ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ ትናንት በባሌ ዞን ሮቤ ከተማ በተካሄደው ውይይት፤ ኦሮሞ ለአንድነቱ እና ለብልፅግናው ሌት ተቀን ሊሰራ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ የኦሮሞን አንድነት የሚበትን አካል ከዚህ በኋላ እንደማይኖር አስረድተዋል።
በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የዞኑ ነዋሪዎች ለክልሉ አመራር የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል። ከእነዚህ መካከል በዋናነት የመንገድ ችግር እንደሆነባቸው፣ የቱሪዝም መዳረሻ ቢሆንም አስፈላጊው የመሠረተ ልማት አለመሟላቱ፣ የሮቤ ከተማ የማስተር ፕላን አለመኖር፣ ከተማዋ በውኃ እጦት ምክንያት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ሮሮ በማሰማት ላይ መሆኗን፣ ከአየር ማረፊያ እስከ ከተማዋ ያውም መንገድ ተመልካች የሚያስፈልገው መሆኑን፣ ባሌ ሰፊና ታላቅ እንደመሆኗ በአንድ ዩኒቨርሲቲ ብቻ መወሰን ይገባታል ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች ተጠቃሾች ናቸው፣
የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ እንደተናገሩት፤ ከባሌዎች የተነሱላቸው ጥያቄዎች በመንግሥት በኩል የሚታወቁ ናቸው። መንገድን በተመለከተም ከሮቤ ሶፍዑመር፣ ከሮቤ ደሎመና ቦረና፣ እንዲሁም ወደ ሐረርጌም ሆነ ከጊኒር ወደ ሱማሌ ይሰራል። ይህ የሚሆነው ለዞኑ ህዘብ ብቻ ታስቦ ሳይሆን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ስለሚያግዝ ጭምር ነው።
ኅብረተሰቡ ያነሳቸው ሌሎች ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የተጀመረባቸው እንዳሉ ሁሉ በቀጣይም የሚመለሱ ይሆናል ያሉት አቶ ሽመልስ፣‹‹በልማት እየበለፀግን በአንድነታችን ደግሞ እየጠነከርን እንሄዳለን›› ሲሉ ጠቅሰው፤ ለዚህም ሌትተቀን መትጋት የሚጠበቅ መሆኑን አስረድተዋል። የኦሮሞ አንድነት ከዚህ በኋላ ሊፈርስ እንደማይችል ገልፀው፤‹‹እናፈርሳለን ብለው የሚናፍቁ ግን ራሳቸው ይፈርሳሉ እንጂ ህልማቸው አይሳካም›› ብለዋል።
የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ እንደተናገሩት፤ ባሌ እንደ ጀነራል ዋቆ ጉቱና ሌሎችንም ያፈራች እንደ መሆኗ ለኦሮሞ ነፃነት የከፈለችው ዋጋ ላቅ ያለ ነው። እነ አሊይ ጭሪ ያደረጉት ታላቅ ትግል ለዛሬ የኦሮሞ ህዝብ አንድነትም ትልቅ ድርሻ አለው።፡ መሆኑም የኦሮሞን ህዝብ አንድነት ማስቀጠል የሚገባ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
እንደ አቶ አዲሱ ገለፃ፤ አንዳንዶች ኦሮሞን በተለያየ ሰበብ ለመከፋፈል ሲጥሩ ይስተዋላል። ይሁንና ከዚህ በኋላ ኦሮሞን ከኦሮሞ መነጠል አይሞከርም።የኦሮሞን አንድነት ለመበተን የሚጥረውን አካል ኦሮሞ የሚታገስበት ጫንቃ አይኖረውም። በመሆኑም የኦሮሞ ነፃነት በምንም መልኩ ወደኋላ ሊቀለበስ አይችልም። የኦሮሞ ቀጣይ ትግል የሰላም ሲሆን፣ ፖለቲካውም ቢሆን በመደማመጥና በመግባባት ላይ የተመሰረተ ነው።
የሮቤ ከተማ ከንቲባ አቶ አደም ዑመር እንደገለፁት፤ ህብረተሰቡ በሰላማዊነቱ የመታወቁን ያህል ለነፃነቱ በመታገሉ ረገድ ደግሞ ቁርጠኛ ነው። አሁኑ የተገኘው ነፃነት እንዲሁ የመጣ ባለመሆኑም ወደኋላ ሊቀለብሰው የሚችል ኃይል አይኖርም።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ የባሌ ዞን ህዝብም ሆነ ሮቤ ከተማ ነዋሪ የልማት ጥያቄ እንዳለው ይታወቃል። እንደ እነ ሶፍዑመር ዋሻ፣ ድሬ ሼ ሁሴንና ሌሎች መስህቦችም ያሉት እንደመሆኑ በተለያዩ የመሠረተ ልማት እጦት ምክንያት ከዚህ ሀብቱ ማጣጣም አለመቻሉ ይታወቃል። ስንዴው፣ ከብቱና ሌላውም ምርቱን እንደልብ ከአንዱ ወደሌላው በማጓጓዝ የመጠቀም እድሉ በመንገድና በሌሎች የመሰረተ ልማት ችግር ምክንያት ተገድቦበት ቆይቷል። በመሆኑም የተነሱ የልማት ጥያቄዎች እነዚህ ነገሮች ከግምት በማስገባት ይመለሳሉ የሚል እምነት ህብረተሰቡ አለው።
ቀደም ሲል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና በወቅቱ የክልሉ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ የዞኑን ህዝብ ማነጋገራቸው ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 8/2011
አስቴር ኤልያስ