አዲስ አበባ፡- መልዕክት የመላክና የመቀበል አገልግሎት የሚሰጠው ዲ.ኤች.ኤል የተባለው ዓለም አቀፍ ተቋም ሠራተኞች ያለ ክፍያ ትርፍ ሰዓትና የእረፍት ቀን እንዲሰሩ ያስገደዳቸው መሆኑን አስታወቁ። ዲ.ኤች.ኤል በበኩሉ የሠራተኞች ትርፍ ሰዓት ክፍያ ሠራተኛውን ለመጥቀም ሲባል ከደመወዝ ጋር ጭማሪ ተደርጎ እየተከፈለ መሆኑን ገልጿል።
ለደህንነታቸው ሲባል በዚህ ዘገባ ላይ ስማቸው የተቀየረው የድርጅቱ ሠራተኛ አቶ አበበ ደበበ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፣ ዲ.ኤች.ኤል ሠራተኞቹ ባልተስማሙበት ሁኔታ የትርፍ ሰዓትና የእረፍት ቀን ክፍያ ከደመወዝ ጭማሪ ጋር ተካቷል በሚል የእረፍት ቀንና ትርፍ ሰዓቶችን ካለ ክፍያ ለመስራት ተገደዋል። ድርጅቱ አንድ ሠራተኛ በሳምንት መስራት ካለበት 48 ሰዓት በላይ ካለምንም ተጨማሪ ክፍያ እንዲሰራ እያደረገ በመሆኑ ዓለምአቀፍ ህግንም የሚጣረስ ነው።
አቶ አበበ እንደሚሉት፣ በሳምንት ከሰኞ እስከ ዓርብ ባሉት ቀናት ብቻ 50ና ከዚያ በላይ ሰዓት እየሰሩ ይገኛሉ። ይህም በማህበራዊ ህይወታቸውና በጤንነታቸው ላይ ከፍተኛ ጫና ከመፍጠሩም ባሻገር ቀድሞ የሚያገኙትን ገቢ በእጅጉ እንዲቀንስ ተደርጓል። ተጨምሯል የተባለው ደመወዝ ቀርቶባቸው ቀድሞ በነበረው ደመወዝ የትርፍ ሰዓት ክፍያ እየተፈፀመላቸው እንዲሰሩ ቢጠይቁም የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ደርሷቸዋል። የእረፍት ቀንና ትርፍ ሰዓት ስራውም ይሁን ክፍያው ይቅርብን ብለው ያቀረቡት ቅሬታም አዎንታዊ ምላሽ አላገኘም።
የትርፍ ሰዓት ክፍያን አካቶ ተጨመረ ከተባለው ደመወዝ በፊት የሚሰሩት ትርፍ ሰዓት ሆን ተብሎ እንደተቀነሰ ወይም እንደተገደበ ተናግረዋል። ከዚያም የሦስት ወራት የትርፍ ሰዓት ክፍያ አማካይ ተይዞ ደመወዝ ጭማሪው ላይ መካተቱን አስረድተዋል። ይህ ደግሞ ሆን ተብሎ የትርፍ ሰዓት ስራ እንዲቀንስ ከተደረገ በኋላ አማካኝ ተብሎ ተሰልቶ ጭማሪ በተባለው ደመወዝ እንደተካተተ አብራርተዋል።
የደመወዝ ጭማሪው ሲመጣ ሠራተኛው በሳምንት 48 ሰዓት እንደሚሰራ በድርጅቱ በኩል እንደተነገረውና በመልካም ጎኑም እንደተቀበለው የሚናገሩት አቶ አበበ፣ እሳቸውና ሌሎች በተመሳሳይ የድርጅቱ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባልደረቦቻቸው ከሚሰሩት የሥራ ባህሪ አኳያ ትርፍ ሰዓትና የእረፍት ቀን መስራት የግድ እንደሆነ ለድርጅቱ በመግለፅ ቅሬታ አቅርበዋል። ያም ሆኖ ድርጅቱ በተለይም በእረፍት ቀን ‹‹በድርጅቱ ሥራ የሌላቸው የስራ ክፍሎች የላቸውም፣ የእናንተ የሥራ ክፍል ሥራ ስላለው መስራት አለባችሁ›› የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።
አቶ ዮሐንስ ሃይሌ የተባሉ ሌላው ሠራተኛ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ መብታችሁን ጠይቁ ተብለው ሲጠይቁ ካላንዳች የቃል ማስጠንቀቂያ የደብዳቤ ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል፣ቀደም ሲል በአንድ ወር በአማካኝ እስከ 70 እና 80 ትርፍ ሰዓት ይሰሩ የነበረ ሲሆን ክፍያውም የትኛውም ሠራተኛ በሰራው ልክ እንዲያገኝ የሚያስችል ነበር፡ የትርፍ ሰዓት ክፍያ ከደመወዝ ጭማሪው ጋር ተካቷል ከተባለ ወዲህ ግን የሰራም ያልሰራም እኩል ክፍያ የሚያገኝበት ፍትሐዊ ያልሆነ ስርዓት ተፈጥሯል። ተጨመረ የተባለው ደመወዝም ቢሆን ትክክለኛ ጭማሪ ሳይሆን የትርፍ ሰዓት ክፍያው በአማካኝ ተሰልቶ በነበረው ደመወዝ ላይ ተደምሮ የቀረበ ነው።
ትርፍ ሰዓት እንዳትሰሩ ተብለው ከድርጅቱ ጋር የተነጋገሩበት ወቅት እንደነበር የጠቆሙት አቶ ዮሐንስ፣ የስራው ባህሪ ትርፍ ሰዓት እንዳይሰሩ የሚያደርግ እንዳልሆነ አስረድተዋል። አሁንም እየሰሩ የሚገኙት በዚህ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ እንደሆነ ጠቁመዋል። ድርጅቱ የትርፍ ሰዓት ክፍያን ከደመወዝ ጋር ሲያካትት በትንሽ ወጪ ብዙ ሥራ ከመስራት አኳያ ብቻ አስቦ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ዮሐንስ ‹‹በዚህ ውጤታማ ሲሆኑ ማስረጃው ባይኖረኝም የድርጅቱ ኃላፊዎች የሚጠቀሙት ነገር እንዳለ እናውቃለን» ብለዋል።
የዲ.ኤች.ኤል የኢትዮጵያ ቢሮ የሰው ሃብት አስተዳደር ኃላፊ ወይዘሮ እታገኝ እንደሻው ሠራተኞቹ ያቀረቡትን ቅሬታ አስመልክቶ ለአዲስ ዘመን እንዳመለከቱት፤ የድርጅቱ ሠራተኞች የትርፍ ሰዓትና የእረፍት ቀን ክፍያ ከደመወዝ ጋር እንዲካተት ሲደረግ ከሠራተኛው ጋር ሰፊ ውይይት አድርጓል። ይህን ጥያቄ በሚያነሱት የድርጅቱ ሠራተኞች የሥራ ክፍል በኩል የትርፍ ሰዓት ክፍያን እንደ መደበኛ ገቢ የመቁጠር ችግር አለ። እነዚህ ሠራተኞች የሥራ አፈፃፀማቸውን ከማሳደግ ይልቅ ሥራ በማዘግየት የትርፍ ሰዓት ክፍያ የማግኘት ፍላጎት አላቸው ። ይህም የመነጨው ገንዘብ ከማግኘት ጉጉት የተነሳ መሆኑን ድርጅቱ ይረዳል።
በመሆኑም ድርጅቱ ሠራተኛው ትርፍ ሰዓት ሰራም አልሰራም በሚያገኘው ገንዘብ ሃሳብ ሳይገባው፣ በእረፍትና በህመም ምክንያት ትርፍ ሰዓት ባይሰራ እንኳን ትርፍ ሰዓት ሰርቶ በአማካኝ የሚያገኘው የትርፍ ሰዓት ክፍያ ከደመወዝ ጋር ቢጠቃለል ተጠቃሚ እንደሚሆን በማሰብ መሆኑን አስረድተዋል። ያም ቢሆን ገና በሂደት ላይ ያለ ጉዳይ እንጂ በወረቀት የፀና የድርጅቱ አቋም አለመሆኑን ነው የሚናገሩት። ‹‹ሠራተኛው ካልተስማማው መቀየር የሚቻል ነው፣ ሠራተኛው ሳይፈልግ ለማድረግ ህጉም እንደማይፈቅድ እናውቃለን›› የሚሉት ኃላፊዋ፤ ድርጅቱ ቢቻል ይሄ ቅሬታ በቀጥታ ለአስተዳደሩ ቢቀርብ በመነጋገር ሊፈታ እንደሚቻልና በራቸውም ዝግ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ድርጅቱ ይህን ጉዳይ ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት ከሠራተኛው ጋር የተነጋገርነውም የትርፍ ሰዓት ክፍያ ለአንድ ወይም ሁለት ወር ከደመወዝ ጋር ሆኖ ሠራተኛው ከቀድሞ ገቢው የሚቀንስ ከሆነ እንደሚስተካከል አቋም ይዞ መሆኑን ኃላፊዋ አመልክተዋል። እነዚህ ሠራተኞች በግልፅ ለመነጋገር ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ሳይሆን በሳምንት 48 ሰዓት ባለመስራትና ሌሎች የስነምግባር ችግሮች ጋር በተያያዘ እርምጃ ተወስዶባቸው ሊሆን ይችላል እንጂ ሃሳባቸውን በማቅረባቸው ብቻ እርምጃ እንዳልተወሰደባቸው ምላሻቸውን ሰጥተዋል። ይሄም ሲደረግ ከመሬት ተነስቶ ሳይሆን እንደ ዓለም አቀፍ ድርጅት ተገቢውን ሂደቶች አልፎ ነው ብለዋል።
‹‹እኛም መጠየቅ አንፈልግም፣ የድርጅቱ ስም እንዲጠፋም አንፈልግም፣ ከዚያም በላይ ሠራተኞቻችንን ማስቀየም አንፈልግም፣ሠራተኞቻችን ወደ ቀድሞው አሰራር ይመለስ የሚል ተገቢ ጥያቄ ካቀረቡ የክፍያ ስርዓቱ እንደ ቀድሞው የማይሆንበት ምክንያት የለም›› በማለትም ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የህግ ባለሙያና አማካሪ አቶ ዝናቡ ይርጋ እንደተናገሩት፤ በአሠሪና ሠራተኛ ህጉ መሰረት አንድ ሠራተኛ በቀን ውስጥ ከስምንት ሰዓት በላይ መስራት የለበትም። ይሁን እንጂ ይህ የስምንት ሰዓት ግዴታ እንደ አሠሪውና ሠራተኛው ግንኙነት የሁለት ሰዓት ጭማሪ ሊያደርግ ይችላል። ያም ሆኖ በሳምንት ተደምሮ ከአርባ ስምንት ሰዓት መብለጥ የለበትም።
በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 ዘርፍ ሁለት አንቀፅ 66 ጀምሮ የትርፍ ሰዓት ሥራ የሚፈቀድባቸው ሁኔታዎችን ሲዘረዝር ማንኛውም ሠራተኛ የትርፍ ሰዓት ሥራ እንዲሰራ አይገደድም፣ያም ሆኖ አሰሪው ሌላ አማራጭ መንገድ ሊኖረው አይችልም ተብሎ ሲገመት ወይም አደጋ የሚደርስ መሆኑ ሲያሰጋ፣ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ሲያጋጥም አሰሪው ትርፍ ሰዓት ሊያሰራ ይችላል።
በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ አንድ የተመለከተው በአስቸኳይ የሚሰራ ሥራ ሲያጋጥም የሚሰራው የትርፍ ሰዓት ሥራ በቀን፣ በወርና በሳምንት ተሰልቶ በዓመት ከመቶ ሰዓት መብለጥ እንደሌለበት በዝርዝር መቀመጡን ጠቁመዋል። «የትርፍ ሰዓት ሥራ የሚሰራ ሠራተኛ ቢያንስ ከመደበኛ ደመወዙ በተጨማሪ እንደሚከፈለው አንቀፅ 68 ላይ ተቀምጧል።
አንድ አሰሪ ለምሳሌ በቀን አራት ሰዓት ቢያሰራ በሌላ ጊዜ ተጨማሪ ሰዓት አሰርቶ ማካካስ ይችላል፡» ብለዋል፡ ይህም በሳምንት ከአርባ ስምንት ሰዓት መብለጥ እንደሌለበት ጠቅሰው፤ ሠራተኛው በሰባት ቀን ውስጥ ቢያንስ ጥርት ያለ የ24 ሰዓት ረፍት የማግኘት መብቱም የተጠበቀ መሆኑን አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 8/2011
ቦጋለ አበበ