“ሀሳባችን ሁሉ መብላት፣ መጠጣት፣ መብለጥ ሆኖ ትሕትና እና መተሳሰብ እየጠፋ ሲሄድ ሀገር ይረበሻል” – መምህር አማረ ተስፋ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከሚፈጸሙ ሥርዓተ አፅዋማት አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን በመስቀል ላይ መሰቀሉን በማሰብ የሚከናወነው የሁዳዴ ፆም ነው። ፋሲካም በመባል ይታወቃል። በዚህ የፆም ወቅት በገና የተባለው የዜማ መሣሪያ ደግሞ በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል። ስለ ዜማ መሣሪያው እንዲሁም በዚህ ወቅት የተመረጠበትን፣ ፆሙን አስመልክቶ ደግሞ መከናወን ስላለባቸው በጎ ተግባራት እንዲሁም ከሀገር ሠላም ጋር በማያያዝ ከመምህር አማረ ተስፋ ጋር ቆይታ አድርገናል።

መምህር አማረ ተስፋ፤ በትምህርቱ፣ በሥራውና በመንፈሳዊ ሕይወቱ ከበሬታ የሚሰጠው ሰው ነው። አንተ ብሎ ለመጥራት የሚቀል ሰው ሆኖ ስላገኘነውና እርሱም ስለፈቀደልን በዚሁ አጠራር እንቀጥላለን። መምህር አማረ የበገና መምህር ነው። በመደበኛ ሥራውም በአዲስ አበባ ከተማ ፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት በመምህርነት እያገለገለ ይገኛል። መምህሩ፣ የመንፈሳዊ አገልግሎቱን የጀመረው በታዳጊነቱ በቤተክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ በመዘመር፣ የሕፃናት መዝሙር ክፍል ኃላፊ ሆኖ በማገልገል ነው።

አገልግሎቱን የዩኒቨርስቲ ተማሪም ሆኖ በመቀጠል መንፈሳዊነቱን የበለጠ አጠናከረው። በመዝሙር የጀመረው መንፈሳዊ አገልግሎት ስለበገና ማወቅ እና በገና መደርደር ፍላጎት አደገ። በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት የትምህርት እድል አግኝቶ አዲስ አበባ ከተማ ሲመጣ የበገና ትምህርት በመማር ፍላጎቱን አሳካ።

በአሁኑ ጊዜም ከመደበኛ ሥራው ውጭ ባለው ጊዜ በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል ውስጥ በገና ያስተምራል። ተማሪዎችንም አስመርቋል። ስለመንፈሳዊ ሕይወት አጠቃላይ የሆነ እውቀትና ግንዛቤ እንዲኖረው በዲግሪ መርሐ ግብር ለአምስት ዓመታት የሚሰጠውን ሥነ መለኮት (theology) ትምህርት እየተከታተለ ይገኛል።

ሰው ከመብላት፣ መጠጣት ባለፈ መንፈሳዊ ምግብም ያስፈልገዋል የሚለው መምህር አማረ፣ መንፈሳዊ ሕይወት በእውቀት ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ እራስንም ሆነ ቤተሰብን በአግባቡ ለመምራት፣ ልጅ ሲወለድም በሥነምግባር አንጾ ለማሳደግ አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻል። አንድ ሰው ምሉዕ ሆኖ ለመገኘት ከመደበኛ ሥራው ውጭ የሚኖረውን ጊዜ መንፈሰዊ ሕይወቱን ሊያጠነክሩ በሚችሉ ነገሮች ላይ ለማሳለፍ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል የሚል እምነት አለው።

ስለትውልድ አካባቢው፣ ስለትምህርቱና ሥራው እንደገለጸልን ከሆነ፤ ተወልዶ ያደገው ባሕርዳር ከተማ ነው። የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም የተማረው በባሕርዳር ሹምአባው፣ ድልችቦና እና ግዮን፣ ባሕርዳር መሰናዶ በሚባሉ ትምህርት ቤቶች ነው። ከፍተኛ ትምህርቱን ደግሞ በአዳማ ዩኒቨርሲቲ በውድ ሳይንስ (WOOD SCINCE) የትምህርት ዘርፍ ለአምስት ዓመት ተምሮ በመጀመሪያ ዲግሪ በ2002 ዓ.ም ተመርቋል።

እንደተመረቀም ቻግኒ በምትባል ከተማ ውስጥ በሚገኝ ቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ በተማረው የትምህርት ዘርፍ በመምህርነት ሥራ ጀመረ። በአጋጣሚውም ተጠቃሚ መሆን ችሏል። ከመምህርነት ሥራው ጎን ለጎን ለቢሮና ለቤት ውስጥ የሚውሉ የእንጨት ውጤቶችን እየሠራ ለገበያ በማዋል ገቢ በማግኘት ይጠቀም ነበር። ዩኒቨርስቲ ሲገባ ግን ውድ ሳይንስ የትምህርት ምርጫው አልነበረም። የተማረው ትምህርት ጥቅም እንዳለው የተገነዘበው ሥራ ከገባ በኋላ ነው።

የዛሬው የዘመን እንግዳችን የሆነው መምህር አማረ፤ በቻግኒ ለአምስት ዓመታት በመምህርነት ካገለገለ በኋላ፤ በ2008 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት ውስጥ የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት እድል አገኘ። ትምህርቱንም ጥሩ ውጤት አምጥቶ በመመረቁ በኢንስቲትዩቱ ውስጥ እንዲያስተምር ጥያቄ ቀረበለት። ጥያቄውን ተቀብሎ በኢንስቲትዩቱ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን በማስተማር ለስድስት ዓመት ተኩል አገልግሏል። አሁንም እያገለገለ ይገኛል። ከእንግዳችን ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አጠናቅረን አቅርበነዋል። መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ በገናን ከስሙ ትርጓሜ በመነሳት ስለ አገልግሎቱ፣ መቼና እንዴት እንደተጀመረ ብታብራራልን።

መምህር አማረ፡- በገና ማለት በገነ ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ሲሆን፣ ትርጉሙም ቃኘ፤ ደረደረ፣ መታ ማለት ነው። አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በሁለት መልኩ “ሲጠብቅና ሲላላ” ብለው ሲተረጉሙ፣ በገና (ሲላላ) ነዘረ፣ መታ፣ ደረደረ፣ ማለት ሲሆን፤ በገና (ሲጠብቅ)፡- ነደደ፣ ተቆጣ ማለት ነው። የግዕዙ መጽሐፍ ቅዱስ በገናን መዝሙር በማለት ይጠቅሳል። በገና “በ” እና “ገና” በመነጣጠል የሚያስገኘውን ትርጉም በመጠቀም የእግዚአብሔርን ከልዑል መንበሩ ወርዶ ፍጹም ሰው መሆን፣ እያደነቁ በገና በዓል ወይም በገና ወቅት የሚደረደር የምስጋና መሣሪያ ስለሆነ በገና ተባለ ተብሎ ይተረጎማል።

በገና በትክክል መቼና እንዴት ተጀመረ ለሚለው ጥያቄ መልሱ ከባድ ቢሆንም የጥበባት ምንጫቸው መጽሐፍ ቅዱስ በመሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገልጾ የምናገኘው የምስጋና ወይም የዜማ መሣሪያ በገና መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። በገና ለመጀመሪያ ጊዜ የደረደሩት ደግሞ የላሜህ ልጅ የዩባሰ /ኢዮቤል/ ልጆች ናቸው። በገና ከፍጥረተ ዓለም ብዙም ባልራቀ ሁኔታ ከክርስቶ ልደት በፊት 3800 ዓ.ዓ የነበረ ነው።

በገና ከትውልድ ትውልድ ሲተካ ይዘቱም ሆነ ዓይነቱ እየተሻሻለ መጥቶ የበገና አጠቃላይ ማኅበራዊ ሚናውም ሆነ መንፈሳዊ አገልግሎት ይበልጥ ጎልቶ የታወቀው በመዝሙረኛው (በበገነኛው) በቅዱስ ዳዊት ዘመን ነው። በገና ወደ ኢትዮጵያ የገባው ከቀዳማዊ ምሊክ ዘመን በፊት ነበር የሚል ሲሆን፣ በመጽሐፍ ጉባኤ ካልዕ ላይ የንግስተ ሳባ እናት አዝሚና ንጉሥን በበገና እና በከበሮ አምላኳን እያመሰገነች የምታገለግል በቤተ መንግሥት ትኖር እንደነበር ተጽፏል። በገና በሀገራችን በታሪክ በስፋት የሚታወቅ በቤተ መንግሥት ውስጥና በአቅራቢያው በሚገኙ መኳንንት ቤት እንደነበርም ታሪክ ያስረዳል።

ይህ የሆነበትን ምክንያት በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተገለጸው፤ ቅዱስ ዳዊት ንጉሥ ሆኖ ሳለ በገና በመደርደር እግዚአብሔርን ያመሰግን ነበር። በወቅቱም ነገሥታቱ በሥርዓተ ቤተ-ክርስቲያን ያደጉ ስለነበር በገና መደርደር ባይችሉ እንኳን የራሳቸው በገና ደርዳሪ ነበራቸው። ለምሳሌ፡- አፄ ቴዎድሮስ፣ አፄ ዮሐንስ፣ አፄ ምኒሊክ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ ልጅ እያሱ ንጉስ ሚካኤል ይጠቀሳሉ።

ይህ ማለት ግን በገና በቤተመንግሥት ብቻ ይደረደር ነበር ማለት አይደለም። በግል ፍላጎትና ጥረታቸው በገናን ከሚደረድሩ አባቶች እየተማሩ የሚደረድሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ነበሩ። በቤተክርስቲያናችን ብዙ መጽሐፍትን በመጻፍ የምናውቃቸው ሊቁ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ አንዱ ሲሆኑ፣ በ 1922 ዓ.ም የበገና መዝሙር ለሕትመት አብቅተዋል።

አዲስ ዘመን፡- በገናን ለመጠቀም ጊዜና ሰዓት መምረጥ ይጠበቃል? በዚህ የዐቢይ የፆም ወቅት ጥቅም ላይ እንዲውል የተመረጠበት የተለየ ምክንያት አለ?

መምህር አማረ፡- በገና በብዙ ሰዎች አዕምሮ ውስጥ የተፈጠረው በዐቢይ የፆም ወቅት ብቻ ጥቅም ላይ እንደሚውል ነው። ነገር ግን በገና ከዓመት እስከ ዓመት መደርደር ይቻላል። በበገና በጣም መደሰታችንን የምንገልጽበትና የምናጨበጭብበት አይደለም። ድምፅም ከፍ ብሎ አይሰማም። በገና ፀሎት የምናደርግበት፣ ልመናን የምናቀርብበት በፆም ወቅት በብዛት ጥቅም ላይ የሚውል የዜማ መሣሪያ ነው። በገና በዐቢይ የፆም ወቅት በብዛት ጥቅም ላይ የሚውለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለኛ ብሎ የተቀበለውን መከራ በማሰብ ለፀሎት የምናውለው የዜማ መሣሪያ ነው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከታወጁ ሰባት አፅዋማት ውስጥ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፆመው ፆም ትልቁና በኃዘኔታም የሚፆም በመሆኑ ነው በማዘወተር የሚደረደረው።

በዚህ የፆም ወቅት መሰበራችንን ማዘናችንን፣ ለቅሶአችንን እንገልጻለን። በገና ለመደርደር በእርግጥም ሰዓት ይፈልጋል። በተለይም በግል ለመጠቀም የራስ ጊዜ፣ የተመስጦ ጊዜ ይፈልጋል። በገና በመደርደር የሚታወቁት እንደነ ስብኃት ዓለሙ አጋ ያሉ የሚደረድሩት ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ተነስተው ነው። በዚህ ሰዓት መደርደር አንድ የሕይወት ክፍላቸው አድርገውታል።

ከእግዚአብሔር ጋር የሚነጋገሩበት መሣሪያቸው ነው ማለት ይቻላል። በበገና መታጀብ ያለበት ነገር ካለ ደግሞ እንደአስፈላጊነቱ ጥቅም ላይ ይውላል። በኅብረት ሆኖ አገልግሎት ይሰጥበታል። ለአብነትም በጥምቀት ወቅት ታቦታት ከማደሪያቸው ወጥተው ወደ ጥምቀተ ባሕር ሲሸኙና ወደማደሪያቸው ሲመለሱ በኅብረት በበገና ደርዳሪዎች ይታጀባል። በግል ደግሞ ለፀሎት ይውላል ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡- በገና ማኅበራዊና ሀገራዊ ጠቀሜታም እንዳለው ይነገራል። እንዴት?

መምህር አማረ፡– በገና ሀገራዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታ ያለው የዜማ መሣሪያ ነው። ኃዘንተኛን ለማረጋጋት፣ ደስታን ለመግለጽ፣ ከሕመም ለመፈወስ፣ ውስጣዊ መረጋጋትን ለማግኘት ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው። በቅርስ ጥበቃ እና ቱሪዝም እንዲሁ የጎላ ፋይዳ አለው። በገና በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን የራሱ የሆነ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ሀገራዊ ጥቅሞች ያሉት የዜማ መሣሪያ መሆኑ ተጠቅሷል።

የበገና የዜማ መሣሪያ ሀገራዊ ጥቅሙ ደግሞ ጠላት ሀገርን በወረረ ጊዜ ሕዝቡን ለጦር ለማነሳሳት፤ ድል በነሱ ጊዜም እግዚአብሔርን ለማመስገን አገልግሎቶች ይውላል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በገናን እስከ አሁን በማቆየቷ ጥንታውያን የዜማ መሣሪያዎችን ጠብቆ ለዓለም ከማስተላለፍ ለቅርስ ጥበቃ እና ለቱሪዝም መስሕብ ትልቅ እገዛ በማድረግ ታላቅ ሀገራዊ አስተዋፅዖ አድርጋለች።

በገና ዋናው አገልግሎቱ ግን እግዚአብሔርን በተመስጦ ለማመስገን፣ ለመንፈሳዊ ትሩፋት ማለትም ለምስጋና፣ ለልመና እና ለፀሎት ብቻ ነው። ታቦታትንም ለማጀብ ይውላል። የእግዚአብሔር ታቦት ከዳዊት ከተማ ሰሎሞን ወደ አሠራው ቤተ መቅደስ ሲገባ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ 1ኛ ዜና. 15፣28 “እስራኤል ሁሉ ሆ እያሉ ቀንደ መለከት እና እምቢልታን እየነፉ ጸናጽልና መሰንቆም በገናም እየመቱ የእግዚአብሔርን የቃልኪዳን ታቦት አመጡ። ” ይላሉ።

በገና የሚያወጣው ድምፅ ከሚያስጨንቅ ርኩስ መንፈስ ወይም አጋንንት ይፈውሳል፤ የሰው ልጅ ፈጣሪውን እንዲያስብ ያደርጋል፣ የግጥሙ ይዘት ደግሞ የሚያደምጠውን ሰው ልብ ሰብሮ ወደ ንስሐ እንዲያመራ ያደርጋል።

አዲስ ዘመን፡- በገና ከሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎች የሚለይባቸው ባሕሪያት ምንድን ናቸው?

መምህር አማረ፡- በገና አውታር ካላቸው የዜማ መሣሪያዎች (Chordaphone) የሚመደብ ነው። በመመሰጥ ኃይሉ፤ በእርጋታው፤ ብቻውን የሚዘመርበት በመሆኑ፤ በሥነ ቃሉ እና በመሳሰሉት ዕሴቶቹ የተለየ ነው።

በሰማይም በምድርም አገልግሎት ያለው፤ ለመንፈሳዊ መዝሙር ብቻ የምንጠቀምበት፤ እያንዳንዱ የአካል ክፍሎቹ አሠራር፤ ሥያሜና ምሳሌነታቸውም መንፈሳዊ በመሆኑ፤ ደርዳሪዎቹንም ወደ መንፈዊ ሕይወት የሚመራ መንፈሳዊ መሣሪያ ነው። በገና ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገት እጅጉን ጠቃሚ ነው። የበገና መዝሙር ከሌሎች የዜማ መሣሪያዎች በተለየ ሰው በተመስጦ ራሱን መመርመር እንዲችል፤ የአምላክን ቸርነትና ፍቅር መመልከት እንዲችል፤ ኃጢአትንና መተላለፍን እንዲጠላ፤ ሞቱን እያሰበ ንስሓ እንዲገባ ትልቅ እገዛ የሚያደርግ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በገና ከምን እንደሚሠራና እያንዳንዱ የበገና ክፍል ስላለው ትርጉም ብትገልጽልን።

መምህር አማረ፡– በገና ከእንሰሳት እና ከዕፅዋት ተዋፅዖኦ የሚሠራ የዜማ መሣሪያ ነው። ከእንሰሳት ተዋፅዖ የሚሠራ የበገና አካላት አውታር፣ የድምፅ ሳጥኑ የሚለብሰው ቆዳ እንዚራ፣ ድህነጻ። ከዕፅዋት ተዋፅዖ የሚሠሩ የበገና ክፍሎች ቀንበር (ጋድም)፣ ምሰሶ፣ የድምፅ ሳጥን፣ በርኩማ፣ መቃኛ፣ ጌጡ እና መወጠሪያ ናቸው። እነዚህም ከዋንዛ፣ ከቀረሮ፣ ከዝግባ፣ ከጽድ ይሠራሉ።

ቀንበር (ጋድም)፡- የበገና የላይኛው ጋድሙ ክፍል ሲሆን፣ የሥልጣነ የእግዚአብሔር ምሳሌ ነው።

መቃኛ፡- በመንፈስ ቅዱስ ይመሰላል። ሕግጋትን በመስጠት የምዕመናን ሕይወት የሚጠብቅ እርሱ ነውና። አንድም ይህን ዓለም ድል በነሱ ቅዱሳንና ፃድቃን ሰማዕታት ይመሰላሉ።

የቀኝ ምሰሶ፡- የፍቅረ እግዚአብሔር፣ የብሉይ ኪዳን አንድም የመጋቤ ብሉይ የቅዱስ ሚካኤል

የግራ ምሰሶ፡- የፍቅረ ቢጽ (ሰው) አንድም የሐዲስ ኪዳን አንድም የመጋቤ ሐዲስ የቅዱስ ገብርኤል

አውታር፡- ከበግ፣ ከበሬ፣ ከላም አንጀት የሚሠራ የበገና የአካል ክፍል ነው። የአስርቱ ትዕዛዛት ምሳሌ ነው። ሕግጋቱ አስር በሚሆኑ በኦሪት ጸንታችሁ ተገዙ ሲል ነው። አንድም በአስሩ የስሜት ሕዋሳት ይመሰላል። አስር ሕዋሳት ባለው ሰውነት ምግባር ይዛችሁ ተገዙ ሲል ነው።

ገበቴ (የድምፅ ሳጥን)፡- ፍሬሙ በእንጨት ተሠርቶ በቆዳ የሚለበጥ የበገና ክፍል ነው። የእመቤታችን ምሳሌ ነው። ከድምፅ ሳጥኑ (ገበቴው) የበገናው ድምጽ እንደሚገኝ ከእመቤታችንም አካላዊ ቃል ወልድ ጌታችን መድኃኒታችን እና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገኝቷል።

በርኩማ፡- ‘’በ’’ የሚመስል ቅርጽ ያለውና በአውታሩና በገበቴው መካከል ያለ የበገና ክፍል ነው። ሙሴ አስርቱን ትእዛዛት የተቀበለባት የደብረሲና ተራራ ምሳሌ ነው።

መወጠሪያ፡- አውታሮችን ከታች ወጥሮ የሚይዝ የበገናው የታችኛው ክፍል ሲሆን፣ የአዳም ዘር (የሰው ልጆች) ምሳሌ ነው።

እንዚራ፡- አውታሩ ጥሩ ድምፅ በሚያወጣ መልኩ ለማስተካከል የሚጠቅም ከቆዳ የተሠራ የበገና የአካል ክፍል ነው። በተጋድሎ ላይ ያሉት ክርስቲያኖች ምሳሌ ነው።

ድህንጻ፡- ከቀንድ የሚሠራ መግረፊያ ሲሆን፣ አገልግሎቱም አውታሮችን በመግረፍ ድምፅ እንዲሠጥ የሚያደርግ መሣሪያ ነው። ድህንጻ በክርስቶስ ይመሰላል። ድህንጻ አሥሩን አውታሮች እየተመላለሰ እንደሚደረድራቸው፤ ኢየሱስ ክርስቶስም በብሉይ ኪዳን የሰጣቸውን አሥሩን ትዕዛዛት በሐዲስ ኪዳንም አጽንቷቸዋልና ነው።

አዲስ ዘመን፡- በገና የዜማ መሣሪያን ማንኛውም የእንጨት ባለሙያ ሊሠራው ይችላል? በገናን ለመማር የተለየ መስፈርት ይጠይቃል?

መምህር አማረ፡- በገና የድምፅን፣ የአውታርን ፀባይ የሚያውቅ ሰው ያስፈልገዋል። በአጠቃላይ አደራደሩን፣ ታሪኩን፣ የት ቦታ ይቀመጥ የሚለውን ማወቅ ስለሚጠይቅ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኝ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን፣ አማኝ የሆነውም ቢሆን በገናን የሚያውቅና የበገናን ፀባይ የሚረዳ ሰው መሆን ይኖርበታል። እኔ የማውቃቸው በገናን የሚሠሩ ሰዎች ስለበገና ተጠይቀው መመለስ የሚችሉ ናቸው። የሚመረጠውም ንግድን ታሳቢ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ዓላማውንና ጥቅሙን በመረዳት ለማዘጋጀት ጥረት ቢደረግ ነው። ምናልባት የእንጨት ሥራ ባለቤቶቹ ስለበገና እውቀት ኖሯቸው ግን ለባለሙያዎቻቸው እያሳዩዋቸው የሚያሠሩ ሊኖሩ ይችላሉ።

በገና እግዚአብሄርን ለማሰብ፣ ለማመስገን የሚውል በመሆኑ፤ ይህን መፈጸም የሚችል ማንኛውም ሰው መማር ይችላል። ለመማር የእድሜ ገደብ የለም። እኔም የማስተምራቸው በተለያየ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ብዙዎችም የሚማሩት በፍላጎት ነው። አንዳንድ ልጆች ላይ የማስተውለው ግን እችላለሁ የሚል ስሜት ነው። በእርግጥ ችሎታቸውን ያሳያሉ። ነገር ግን በፀሎት ለመጠቀም ጥረት አያደርጉም።

አዲስ ዘመን፡- በገና የዜማ መሣሪያ ሰዎችን በማረጋጋት ትልቅ ሚና ካለው አንፃር አሁን ሀገር ላይ እየተስተዋለ ላለው የሠላም እጦት አስተዋፅዖው እንዴት ይገለፃል? አገልግሎቱን ለማስፋት እየተደረገ ያለው ጥረትስ እንዴት ይታያል?

መምህር አማረ፡- ቤተክርስቲያን ከበገናም በተሻለ ንዋየ ቅዱሳት አሏት። ለአብነትም ፀናጽል የተባለውን ዘወትር እሁድ እና ለበዓላት ጊዜ ትጠቀምበታለች። እንደ ፀናጽል፣ መቋሚያ ያሉት ከቅዱስ ያሬድ፣ ከስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ ከቅዱስ ያሬድ ዜማ ጋር አብረው ተሠርተዋል። መቋሚያ፣ ፀናጽልና ከበሮ የቤተክርስቲያኗ የዜማ፣ የማሕሌት፣ የሰዓታት የአገልግሎት ማቅረቢያ እቃዎች ናቸው። በገና ግን ከዚህ ወጣ ባለ መልኩ በግል ሕይወት ወይንም በማኅበራዊ ጉዳይ በመድረክ እንዲሁም ያዘነ ሰው ለማረጋጋት ጥቅም ላይ የሚውል መሣሪያ ነው።

የበገና አገልግሎትም አንድ ጊዜ ትኩረት እየተሰጠው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ትኩረት እየተነፈገው ወጣ ገባ ባለሁኔታ ነው። በቅዱስ ዳዊት ዘመን በጣም የታወቀ ነበር። ከሦስት ሺ ዓመት በፊት ወደኋላ በገና ሥርዓት ተበጅቶለት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ የዜማ እቃ ነው። ቅዱስ ዳዊት በገናን በማስፋት እርሱም እውቅና ያገኘበት ዘመን ነው የነበረው። ብዙ ነብያትም በገናን እየደረደሩ ትንቢት ይናገሩ ነበር። በአገልግሎቱ እንዲህ ከፍ ያለበት ጊዜ ቢኖርም ዝቅታም ታይቶበታል።

በተለይ በ1960 እና 1970ዎቹ በገና የዜማ መሣሪያ የተዘነጋበት ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል። ዝቅ ባለበት ዘመን ደግሞ እንደነ ስብኀት ዓለሙ አጋ ያሉ እና በስምም በብዙዎች ዘንድ የማይታወቁ በገናን በፆም የሚጠቀሙበት በገና ደርዳሪዎች ከፍ በማድረግም ሚና ተወጥተዋል። በእድሜ ገፍተው ብዙ ነገር ማድረግ እየተቸገሩ ነገር ግን በገናን ሲደረድሩ ተመስጦ ውስጥ የሚከቱ አባቶች አሉን።

በገና ትኩረት ተሰጥቶት በተከታታይ ጥቅም ላይ እንዲውል ቢደረግና በገና ደርዳሪዎችን በስፋት ማፍራት ቢቻል የተረጋጋ፣ ሰከን ብሎ ነገሮችን የሚያይ፣ ችኩል ያልሆነ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል። በገና ደርዳሪዎችም ሆኑ የበገና መምህራንን ረጋ ያሉ፣ ሲናገሩም የማይቸኩሉና ድምፃቸውም ከፍ ብሎ የማይሰማ ለጆሮ የሚጥም ነው። ሀገር እንዲህ ያለ የተረጋጋና ለማዳመጥ ዝግጁ የሆነ ማኅበረሰብ ነው የሚያስፈልጋት።

በገና ለመዝሙር የሚውል የዜማ እቃ ቢሆንም፤ ዝቅ ብሎ ለሌሎች መታዘዝን፣ የሚረብሽንም መንፈስ የሚያረጋጋ፣ አድማጭም የሚያደረግ በመሆኑ አሁን ሀገራችን ካለችበት የሠላም እጦትና ያለመረጋጋት ሁኔታ ውስጥ ለመውጣት በበገና እራስን ማረጋጋት አስፈላጊ ነው የሚል እምነት አለኝ።

በገናን ከሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎች ለየት የሚያደርገው፤ የበገና ትምህርት ማድመጥ ነው ክህሎቱ (ስኪሉ)ለዚህም ነው የማድመጥ ክህሎትን የሚያላብሰው። አሁን ላለው የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ የሚያዳምጥ ትውልድ ነው የሚያስፈልገን። የተረጋጋ፣ ፈጣሪውንም የሚያውቅ ይሆናል።

ለሀገራችን ሠላም መስፈን ብቻ ሳይሆን፣ ለሀገር እድገትም ወሳኝ ነው። አድማጭ ሲኖር ነው በንግዱም ሆነ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ እድገት ማስመዝገብ የሚቻለው። በገና በሠራነው ሥራ ተቆጭተንና አዝነን በመፀለይ የተረጋጋና ሠላም እንዲኖረን በመሆኑ ሀገር ላይም የተፈጠረው የሠላም እጦት በመልካም እንዲመለስ ለማድረግ ይህን መንገድ መከተል ያስፈልጋል።

ሰው በድሎ ወደ ሌላ ነው የሚጠቁመው እንጂ በደለኛነቱን አይናገርም። በበገና የሚደረገው ፀሎት ግን ፈጣሪው በደሉን ይቅር እንዲለው ነው። አሁን እያስተዋልን ያለነው ግን ጥፋተኛ ሆነን እንዴት ጥፋታችንን መሸፈን እንደምንችል ጥረት ስናደርግ የምንታየው። አለፍ ብሎም ጉልበት ውስጥ እንገባለን። በኔ እምነት በገና መጥፎ የሆኑ ድርጊቶችን በማስቀረት፣ የተረጋጋና አድማጭ ትውልድ እንዲኖረን ያስችላል።

አገልግሎቱ እንዲሰፋ በተለይም 1996 ዓ.ም ጀምሮ ማኅበረ ቅዱሳን ባሉት ማሠልጠኛ ተቋማቱ በገና ደርዳሪዎችን በማፍራት በስፋት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የበገና ትምህርት በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን፤ ከሀገር ውጭም ትምህርቱ እየተሰጠ ነው።

ከሀገር ውጭ ፍላጎቱ ሰፊ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ተምረው እውቀቱን ካገኙ በኋላ በውጭ የሚያስተምሩ አሉ። ቴክኖሎጂውን በመጠቀምም በድረገጽ የቀጥታ አገልግሎት (Online) አገልግሎትም ትምህርቱን የሚከታተሉ አሉ። እኔም በቀጥታ አገልግሎት በተለያዩ የአሜሪካን ግዛቶች የማስተምራቸው ተማሪዎች አሉኝ።

ተማሪዎቹ በሕፃናትና በአዋቂ የተመደቡ ሲሆኑ፣ ሕፃናቱ አንዳንዶቹ በውጭ ሀገር ተወልደው ያደጉ ናቸው። ሁሉም ተማሪዎች በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ግን የውጭ የሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተከታዮች ናቸው። በማኅበረቅዱሳንም በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ አዋቂዎችና ሕፃናት ተማሪዎች በብዛት ይገኛሉ።

አዲስ ዘመን፡- በዚህ የፆም ወቅት እያንዳንዱ መንፈሳዊ ለግሉ ከሚያደርገው ፀሎት ለሀገር ሠላም በመትጋት ይፀልያል። ግን ደግሞ ሠላምና መረጋጋት ስጋት እየሆነ ነው፤ እዚህ ላይ ምን ትላለህ?

መምህር አማረ፡- ሠላም በሌለበት የእግዚአብሔር መንፈስ ይርቃል። ይህ ማለት ሰው ከመንፈሰዊ ይልቅ ወደ ሥጋዊ ፍላጎቱ አጋድሏል ማለት ነው። ክፋት ሲበዛ ስቃዩም ይጨምራል። ሀሳባችን ሁሉ መብላት፣ መጠጣት፣ መብለጥ ስለሆነ፣ ትሕትና እና መተሳሰብ እየጠፋ ሲሄድ ሀገር ይረበሻል።

ወንድም ለወንድሙ ማሰብ ካልቻለ አንዱ በሌላው ላይ መነሳት ነው የሚሆነው። በኔ እምነት አሁን ላይ የገጠመን አለመረጋጋትና ሠላም ማጣት ከመንፈሳዊ ሕይወት ዝቅ ከማለት የመጣ ነው። ጥፋቱን ደግሞ ሁላችንም ነው መውሰድ ያለብን። ምክንያቱም መንግሥትም፣ የሃይማኖት ተቋማትም፣ ማኅበረሰቡም ሁሉም የየድርሻውን ቢወጣ ሀገር ሠላም ትሆናለች።

ዓለም ላይ የሚታየው ሩጫ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ ነው። መንፈሳዊውን ዓለም የረሳ ነው። ማዘመን፣ ማፍጠን፣ ማሻሻል የሚል ብቻ ነው። ማምለክ የሚል እሳቤ ይጎለዋል ብዬ አምናለሁ። እንዳንዶቻችንም የሩቁን የአኗኗር ዘይቤ በመመኘትና የእነርሱ እየበለጠብን መንፈሳዊነታችንን እየዘነጋነው ይመስለኛል። የሀገር እድገት ሳይገታ ጎን ለጎን ሰው መንፈሳዊ ሕይወት ያስፈልገዋል ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ እዚህ ላይ ሥራ ያስፈልጋል።

ይህ ሥራ ከቤተክርስቲያን፣ ከቤተሰብ፣ ከማኅበረሰብ፣ ከመንግሥት የሚጠብቅ ነው የሚሆነው። በተለይም ዘመኑ የቴክኖሎጂ ዘመን በመሆኑ ወላጆች ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን (Mobile) ለልጆቻቸው በመስጠት የፈለጉትን እንዲያዩ እድል እየሰጧቸው ነው። ከመስመር የሚያወጡ ነገሮች ላይ ከወዲሁ ከተሠራበት ወደ ልማት እና እድገት መሻገር፤ ሠላምም ማምጣት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።

መምህር አማረ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You