አዲስ አበባ:- የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኑሮን ለማሻሻልና ልማትን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና እንዳለው የሳይንስና ከፍተኛ ትምርት ሚኒስቴር አስታወቀ። አገር አቀፍ የቴክኒክና ሙያ የክህሎትና ቴክኖሎጂ ውድድር በመካሄድ ላይ ይገኛል።
«በክህሎትና በስነ- ምግባር የታነጸ ትውልድ ለሰላምና ለልማት ዋስትና ነው» በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ባለው ውድድር ላይ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ አብዱዋስ አብዱላሂ እንደተናገሩት ትምህርትና ስልጠናው ኑሮን ለማሻሻልና ዘላቂ ልማትን ለማምጣት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው።
እንደ ሚኒስቴር ዴኤታው ገለጻ ቴክኒክና ሙያ የቴክኖሎጂ አቅምን በመገንባት የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን በማረጋገጥ በኩል ላቅ ያለ ሚናን ከመወጣቱም በላይ፤ ዓለም አቀፍ ቴክኖሎጂዎችን በመቅዳት፣ በማላመድና በማሸጋገር የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ተወዳዳሪ ለማድረግ ያግዛል።
አገሪቱን ከችግር የሚያወጣት ቴክኖሎጂን መቅዳት አልተቻለችም ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታው፤ ለዚህ ዋናው ምክንያቱ ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቀናጅቶ አለመስራት፣ የማበረታቻ ስርዓት አለመኖር፣ የተሰሩ ቴክኖሎጂዎች ለህዝብ ይፋ ማድረጊያ መድረክ አለመዘጋጀት ተጠቃሾቹ መሆናቸውን አብራርተው፤ በቀጣይ የተሰሩትን ለማበረታታት እንዲሁም ወደ ዘርፉ የሚቀላቀሉትን አካላት ለመደገፍም እንደዚህ ዓይነት መድረኮች ወሳኝ በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውን ጠቁመዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትርና የቴክኒክና ሙያ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ አህመድ ሸዴ በበኩላቸው «ንግስት ባለፉት ዓመታት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረትን ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፤ በዚህም አገሪቱ የምትፈልገውን የሰው ሀይል ከማፍራት አንጻር ውጤቶች ታይተዋል። ወደፊትም መሰራት ያለባቸው ስራዎች ብዙ ናቸው» ብለዋል።
የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና በተለይም አሁን በአገር ደረጃ ከተጀመረው ሪፎርም አንጻር ምርትና ምርታማነትን በማስፋት በኩል ቁልፍ ሚና ይጫወታል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ዜጎች ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ተገቢውን ስልጠና እንዲያገኙ የሚሰጡ ስልጠናዎችም አገሪቱ ያለችበትን የእድገት ደረጃ ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ መስራት ያስፈልጋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ዘርፉን የሚቀላቀሉ ሰልጣኞች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም በማህበረሰቡ ዘንድ እንደ ሁለተኛ አማራጭ መታየቱ አልቀረም፤ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሰልጣኞች ሥራ ፈላጊ ብቻ ሳይሆን ሥራ ፈጣሪም እንዲሆኑ በማስቻል ይህንን የተዛባ ግንዛቤ ማስተካከል ይገባል።
በሌላ በኩል ይህን መሰሉ አገር አቀፍ ሲምፖዚየምና ኤግዚቢሽን እንዲሁም የውድድር መድረክ ፋይዳው የጎላ ከመሆኑም በላይ በዘርፉ ያሉ ሰልጣኞች የጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾችን የተነሳሽነት ስሜት በመፍጠርና በማነቃቃት ፋይዳው ትልቅ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተልዕኮው ሰፊ ነው፤ ከዚህም መካከል ተመዝኖ ብቁ የሆነ የሰው ሀይልን በማቅረብ የአገሪቱን የግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ በማሸጋገር ይጠቀሳል፤ ይህንን ለማድረግም ሰልጣኞች ብቁና አምራች ሆነው እንዲወጡ ማስቻልም ይገባል ብለዋል።
ከዚህ አኳያ እስከ አሁን የተሰሩ ስራዎችና ያልተሰሩ እንዳሉት ሁሉ ለተከናወኑት ተግባራት የሚገባቸውን እውቅና ሳንሰጥ ሌላውን መስራት ስለማይቻል መጀመሪያ የሰሩትን በማበረታታት በቀጣይ የጎደለውን የመሙላት ተግባር እንደሚከናወን ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የክህሎት የተግባራዊ ምርምር ውድድርና አውደ ርዕይ ላይ በክልል ደረጃ በአሰልጣኞች የተዘጋጁና 1ኛ የወጡ 9 ቴክኖሎጂዎች፣ በሰልጣኞች የተዘጋጁ 5፣ በኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች 4፣ በድምሩ 18 ቴክኖሎጂዎች የቀረቡ ሲሆን ፤ በክህሎት በ9 ፕሮጀክቶች 72 አሰልጣኞችና 54 ሰልጣኞች፤ እንዲሁም በተግባራዊ ምርምር 9 ሰልጣኞች ለውድድር ይቀርባሉ። 127 ቴክኖሎጂዎችም ለህዝብ እይታ እንደሚቀርቡ ከመድረኩ ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2011
እፀገነት አክሊሉ