ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ሕዝበ ሙስሊሙ ፈጣሪን ሊለምን ይገባል

አዲስ አበባ፡- ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሕዝበ ሙስሊሙ ፈጣሪን ሊለምንና የተቸገሩ ወገኖችን ሊደገፍ እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ገለጹ፡፡

ታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጧር መርሐ ግብር ለአራተኛ ጊዜ “ኢፍጧራችን ለአንድነታችን” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ሕዝበ ሙስሊሙ በአንድነት ፈጣሪውን ሊለምንና በተለያዩ ምክንያቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ሊደገፍ ይገባል ብለዋል።

በአንድነት ተሰባስበን በጎዳና ላይ ስናፈጥር ያለው ደስታው ትልቅ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ሕዝበ ሙስሊሙ ለሠላም ዘብ መቆም አለበት ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ አደጋዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጎዳና ላይ የሚገኙ ወገኖችን ስናስብ ከፍተኛ ኅዘን ይሰማናል ያሉት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም፤ ሠላም እንዲሰፍን ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የመርሐ ግብሩ የበላይ አስተባባሪ ኡስታዝ አቡበክር አሕመድ እንደተናገሩት ታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጧር አንድነትን

የምናንጸባርቅበት፣ ያለው ለሌላው የሚያካፍልበት እንዲሁም አብሮነት የበለጠ የሚጎለብትበት ነው።

ረመዷን የአንድነትና የመተባበር መንፈስን የያዘ ወር መሆኑን ገልጸው፤ እንደ ሀገር አንድነታችን ለማሳደግ አስተዋፅዖ እንዳለው ተናግረዋል።

ጾመኞች በሚያፈጥሩበት ጊዜ የሚያደርጉት ዱዓ በፈጣሪ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሆኑን ገልጸው፤ በጦርነት ሳቢያ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ጸሎት (ዱዓ) እንዲያደርግ ምዕመናኑን ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸይኽ ሡልጣን አማን ኤባ በበኩላቸው፣ ለታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጧር ስኬት አስተዋፅዖ ያበረከቱ አካላትን አመስግነዋል።

ታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጧር በሠላም እንዲጠናቀቅ ሥርዓቱን በጠበቀ መንገድ እንዲከናወን የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር፣ የጸጥታ አካላትና ሕዝበ ሙስሊሙን ሸይኽ ሡልጣን አማን አመስግነዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቡዜና አልቃድር፣ የመጅሊስ አመራሮች፣ ኡላማዎች፣ ኡስታዞች እንዲሁም የእምነቱ ተከታዮች ተገኝተዋል።

በኢፍጧር መርሐ ግብሩ ላይ ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን ከሁሉም ክፍለ ከተማ የተወጣጡ የቁርዓን ንባብ ተወዳዳሪዎች ተሸልመዋል።

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You