- የምርጫ ቦርድ አባላት ሹመት
- የፍርድ ቤት እጩ ዳኞችና ፕሬዚዳንቶች ሹመት
- የ30 ሚሊዮን ዩሮ የብድር ስምምነት አጽድቋል
- የባንክ ሥራ አዋጅን ለቋሚ ኮሚቴው መርቷል
የህዝብ እንደራሴዎቹ ትናንት ባካሄዱት አምስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 44መደበኛ ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቀረበውን የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት ሹመትና አራት ረቂቅ አዋጆችን በማጽደቅ የባንክ ሥራ አዋጅን ደግሞ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 1133/2011 አንቀጽ አምስት መሠረት ወይዘሮ ብዙወርቅ ከተተ፣ አቶ ውብሸት አየለ፣ ዶክተር ጌታሁን ካሳና አቶ አበራ ደገፋ የምርጫ ቦርዱ አባላት ሆነው ሲሾሙ፤ አቶ ውብሸት አየለ በምክትል ሰብሳቢ፤ በአሁኑ ወቅት የቦርዱ ሰብሳቢ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በያዙት ኃላፊነት እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡ ሹመቱ በአብላጫ ድምፅ በ17 ተቃውሞና በአንድ ተዓቅቦ ጸድቋል፡፡
የምርጫ ቦርድ አባላቱ ሹመት ከመካሄዱ በፊት የሥራ ልምዳቸውና የትምህርት ደረጃቸው እንዲሁም ከየትኛውም የፖለቲካ አባል ድርጅቶች ገለልተኛ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን፤ ብዛታቸው አሁን ካለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር አንጻር ሲታይ አነስተኛ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በሌላም በኩል፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ አምባሳደር መስፍን ቸርነት አማካኝነት ለሹመት የቀረቡት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እጩ ዳኞች፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እጩ ፕሬዚዳንት እንዲሁም እጩ ምክትል ፕሬዚዳንቶች ሹመት በአንድ ተቃውሞ በአስር ተዓቅቦና በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡
አምባሳደር መስፍን እንዳሉት፤ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 81(2) መሠረት የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ያቀረባቸው ተሿሚዎች በህግ ትምህርት የሰለጠኑ በቂ ልምድ ያላቸው፣ በታታሪነት፣ በፍትሐዊነት፣ በሥነ ምግባር፣ መልካም ስም ያተረፉና በዳኝነት ሙያ ለመስራት ፈቃደኛ የሆኑ ናቸው፡፡ በዚህም አቶ እስቲበል አንዱዓለም፣ ወይዘሮ ወርቅነሽ እሱባለው፣ አቶ መላኩ ካሳዬ፣ አቶ ደረጀ አያና፣ አቶ ኑረዲን ከድር፣ አቶ ወርቁ መገርሳ፣ ወይዘሮ ሌሊሴ ደሳለኝ፣ ወይዘሮ ሩታ ገብረ ጻዲቅ፣ አቶ ሐፍዝ አባጀማል፣ አቶ ብርሀኑ መንግስቱ፣ ወይዘሮ ነጻነት ተገኝ፣ አቶ ሀብታሙ እርቅይሁን፣ ወይዘሮ ማርታ ተካ፣ ወይዘሮ አበባ እንቢአለ፣ አቶ መሐመድ አህመድና አቶ ደጀኔ አያንሳ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ሆነው ለማገልገል በህዝብ እንደራሴዎቹ ምክር ቤት ፊት ቀርበው ቃለ መሀላ ፈጽመዋል፡፡
ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቶ ብርሃነመስቀል ዋቅጋሪ ፕሬዚዳንት፣ ወይዘሮ ተናኜ ጥላሁንና አቶ ተኽሊት ይመስል ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሲሾሙ፤ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቶ ፉአድ ኪያር ፕሬዚዳንት፣ ወይዘሮ አሸነፈች አበበና አቶ ተስፋዬ ንዋይ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲያገለግሉ ምክር ቤቱ ያጸደቀ ሲሆን፤ ነጻና ገለልተኛ በመሆን ውጤታማና በህዝብ የሚታመን የዳኝነት ዘርፍ የመገንባት ሥራ በሙሉ ቁርጠኝነት እንዲያገለግሉም ኃላፊነት ሰጥቷል።
ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ መንግሥትና በአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ መካከል ለሴቶች የንግድ ሥራ ፈጠራ ብቃት ማሳደጊያ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት አዋጅ አጽድቋል። የብድር ስምምነቱም የሥራ እድል ፈጠራ ፕሮጀክት በማጠናከር በሴት ፈጣሪዎች ለሚመሩ አነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች የብድር ፋይናንስ በማቅረብ ድጋፍ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑን፤ የስድስት ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ30 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅና ጥቅም ላይ በዋለውና ለአበዳሪው ባልተመለሰው የብድሩ ገንዘብ ላይ በዓመት 0ነጥብ75 በመቶ ወለድ የሚከፈልበት መሆኑን፤ ቀድሞ ከነበሩት አስር ከተሞች በተጨማሪ ከኦሮሚያ ሦስት፣ ከአማራ ሁለት፣ ከደቡብ ሁለትና ከትግራይ አንድ እንዲሁም ሐረሪና ድሬዳዋ ከተሞች ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል።
የመንግሥት ወጭ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ከሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል የወጣውን ረቂቅ አዋጅ ምክር ቤቱ ያጸደቀ ሲሆን፤ አዋጁ የፌዴራል መንግሥት ለክልል መንግሥታት የሚሰጠውን የበጀት ድጋፍና ልዩ ድጎማዎች በህገ መንግሥቱ መሠረት ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ መደንገጉን፤ የዋና ኦዲተርና ምክትል ኦዲተሮች በታወቀና በህግ በተሰጠ ጊዜ ያለስጋት እንዲሰሩ ለማስቻል፤ እንዲሁም የኦዲት ሥራውን በተሻለ ለመምራት የሚያስችል አደረጃጀትና ሥርዓት ለመፍጠር አጋዥ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አህመድ የሱፍ ገልጸዋል።
የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ የተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ያለዋስትና መብት ረቂቅ አዋጅን ምክር ቤቱ በትናንትናው ውሎው አጽድቋል። አዋጁ ተንቀሳቃሽ ንብረትን በብድር በማስያዝ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ በማድረግና በኢንቨስትመንት በማሳተፍ ተጨማሪ የሥራ እድሎችን ለመክፈት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑም ተደምጧል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ ካጸደቃቸው ውስጥ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባለሥልጣን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ተጠቃሽ ሲሆን፤ ይኸውም ረቂቅ አዋጁ የቴሌኮም አገልግሎትን ወደ ግል በማዛወር መንግሥት በቴሌኮም ዘርፉ ያለውን አገልግሎት ለህብረተሰቡ በጥራት እንዲዳረስ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የሚያስችል አቅጣጫ ያስቀመጠ መሆኑ ተጠቅሷል።
በተጨማሪም ፓርላማው የባንክ ሥራ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ የመራ ሲሆን፤ ረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ዜጎች በባንክ ዘርፉ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ አገሪቷ ከዓለም ንግድ ድርጅት ጋር ከምታካሂደው ድርድር ጋር የማይጋጭና የተጣጣመ መሆኑን የመንግሥት ተጠሪው አስታውቀዋል። ረቂቅ አዋጁ በቋሚ ኮሚቴው ታይቶ ከጸደቀ በኋላ የአክሲዮን ግዥው የሚካሄደው በኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን፤ ባለ አክሲዮኖቹም የሚያገኙት የትርፍ ድርሻ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ባለአክሲዮን በብር የሚከፈላቸው እንደሚሆንም ተጠቁሟል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2011
አዲሱ ገረመው