• ካጓጓዘው የገቢ ጭነት የድርጅቱ መርከቦች ድርሻ 20 በመቶ ብቻ ነው
• 3 ሚሊዮን ቶን ጭነት በማጓጓዝ 1. 3 ቢሊዮን ብር አትርፏል
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ላለፉት አምስት ዓመታት በባህር ካጓጓዘው የገቢ ጭነት ውስጥ የድርጅቱ መርከቦች ድርሻ 20 በመቶ ብቻ መሆኑን አስታወቀ። ባለፉት አስር ወራት ሶስት ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ ገቢ ጭነት በማጓጓዝ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ከታክስ በፊት ትርፍ ለማግኘት መቻሉ ተጠቁሟል።
የድርጅቱ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸብር ኖታ እንዳስታወቁት፣ ድርጅቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ዕድገት በሎጂስቲክስ አቅርቦት ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል። ጭነት በባህር በማጓጓዝ አቅሙም በዓመት ከ4 ሚሊዮን ቶን በላይ ደርሷል።
ባለፉት አምስት ዓመታት በገቢ ጭነት ረገድ በኪራይ መርከቦችን በመጠቀም አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ አሸብር በዚህም የድርጅቱ መርከቦች ድርሻ ዝቅተኛ ነው ብለዋል። በ2007 ዓ.ም የድርጅቱ መርከቦች ድርሻ 36 ሲሆን ከዚህ ጊዜ በኋላ ግን የነበራቸው ድርሻ መቀነሱን ያስታውሳሉ። መርከቦቹ በ2008፣19በመቶ ፤ በ2009፣13በመቶ፤ በ2010፣16በመቶ ድርሻ ዝቀተኛ እንደሆነ አስረድተዋል።
ከዚህ በመነሳት የድርጅቱን መርከቦች ድርሻ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ያስረዱት አቶ አሸብር በተለይ ብትን ጭነቶችንበድርጅቱ መርከቦች ማጓጓዝ የሚያስችል አቅም መፍጠር መቻል ቀሪ የቤት ሥራ ነው ብለዋል።
ባለፉት አስር ወራት 2 ሚሊዮን 991 ሺ 436 ቶን የሚጠጋ ገቢ ጭነት በማጓጓዝ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን 384 ሺ ብር በላይ ከታክስ በፊት ትርፍ ማግኘት እንደቻለ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። በጭነት አስተላላፊነት አገልግሎት በኩል 137 ሺ 992 ኮንቴይነር ፣ 3264 ተሽከርካሪዎች በመልቲሞዳል ስርዓት ወደ ሀገር ውስጥ ወደቦችና የጉምሩክ ፍቃድ ያላቸው መጋዘኖች ለማድረስ ተችሏል። በተመሳሳይ 1 ሚሊዮን 751 ሚሊዮን 628 ቶን ገቢ ጭነት እና 194 ሺ 603 ቶን ወጪ ጭነት በዩኒሞዳል ትራንስፖርት ስርዓት ለማስተላለፍ መቻሉን አቶ አሸብር ገልፀዋል።
ድርጅቱ በአጠቃላይ ከሚሰጣቸው የተለያዩ አገልግሎቶች ጠንከር ያለ ገቢ ለመሰብሰብ ችሏል ያሉት ዳይሬክተሩ ከዚህ ባሻገርም የአ ገሪቱን ኢኮኖሚ ከመደገፍና አትራፊነቱን ጠብቆ ከመቀጠል በተጨማሪ ወጪ ንግድን ለማበረታታት ባለሀብቶችን እየደገፈ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለሀብቶች ለምርት ግብዓትነት ለሚያስገ ቧቸው ጥሬ ዕቃዎች እና ወደ ውጪ ለሚልኳቸው ምርቶቻቸው ከየብስ ትራንስፖርት 25 በመቶ እንዲሁም ከባህር ትራንስፖርት 5 በመቶ የዋጋ ቅናሽ አድርጓል።
በዚህም ባለፉት አስር ወራት ከየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት ከ15 ሚሊዮን ብር ፣ ከባህር ትራንስፖርት ከ52ሺ በላይ ዶላር ድጋፍ አድርጓል። በአጠቃላይ ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ቅናሽ በማድረግ ባለሀብቶችን ማበረታታቱን አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2011
ሀብታሙ ስጦታው