አዲስ ዘመን ድሮ

አዲስ ዘመን ቀደም ባሉት ዓመታት እትሞቹ ከማኅደሩ ያሰፈራቸው ብዙ ጉዳዮች ዛሬ ላይ ለትውልድ የሚሻገሩ ታሪክ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ለትውስታ ያህል ቀንጭበን በ“አዲስ ዘመን ድሮ” ዓምዳችን በየሳምንቱ በጥቂቱ ማስታወሳችንን ቀጥለናል፡፡ ለዛሬ ከመረጥናቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል፤ እድለኛዋ ባልቴት በተከታታይ ዓመታት የብሔራዊ ሎተሪ አሸናፊ ሆነው የተገኙበት ሚስጥሩ ምን ይሆን…በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተማሪዎች የደንብ ልብስ ሲጀመር፤ የትጥቆቹ ዝርዝር ፈገግታም ግርምትንም የሚያጭሩ ናቸው፡፡ ወጣ ስንል ደግሞ አንድ አሕጉራዊና ሌላ ዓለም ዓቀፋዊ ጉዳዮችን እናገኝበታለን፡፡

ያምናዋ ባለ 10 ሺህ ዘንድሮም 50 ሺህ አገኙ

የብሔራዊ ሎተሪ በተለይ ለእንቁጣጣሽ በዓል የተዘጋጀው የመጀመሪያው አንደኛ ዕጣ በሙሉ ለወይዘሮ ተዋበች ኪዳኔ ደርሷል፡፡

ወይዘሮ ተዋበች በአሁኑ ሎተሪ ሀምሳ ሺህ ብር ያገኙ ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት የ10 ሺ ብር ዕድል ደርሷቸዋል፡፡

ዕድለኛይቱ የ59 ዓመት ወይዘሮ የስምንት ልጆች እናትና አያት ናቸው፡፡ ወይዘሮ ተዋበች በጠጅ ንግድ የሚተዳደሩ የይፋት ተወላጅ በአዲስ አበባ ሚያዚያ 27 አደባባይ ገደማ የሚኖሩ ናቸው፡፡

ወይዘሮ ተዋበች ይህንን ዕድል ያገኙት 37 ቲኬት ገዝተው ነው፡፡ በጠቅላላው ወይዘሮ ተዋበች ከ5 መቶ በላይ ቲኬት መግዛታቸውን ገልጸዋል፡፡ ያሁኑም 50 ሺህ ብር የደረሳቸው የአንድ አይነት ቁጥር ሙሉ ሴሪ በመግዛታቸው ነው ሲል የብሔራዊ ሎተሪ አድሚንስትሬሽን ጽ/ቤት ገልጧል፡፡

(አዲስ ዘመን መስከረም 7 ቀን 1957 ዓ.ም)

ተማሪዎች በታኅሣሥ ወር የመለያ ልብስ ይኖራቸዋል

የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፤ ወንዶችም ሴቶችም የትምህርት ቀን ልብስ እንዲለብሱ የሚል ሕግ የትምህርትና የሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ስላወጣ፤ ሕጉ ከዚህ ዓመት ጀምሮ በሥራ ላይ እንደሚውል አቶ ዓምደ ሚካኤል ሀብቴ የትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቂያ ክፍል ሹም ገልጠዋል፡፡

ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ለወንዶች አንድ ቦላሌ ሱሪ፤ አንድ ቁምጣ ሱሪ፤ አንድ ሸሚዝና አንድ ኮት ዋጋው በጠቅላላው 9.80(ዘጠኝ ብር ከሰማኒያ ሳንቲም) ለአንደኛ ደረጃ ሴቶች ተማሪዎች፤ አንድ ቀሚስ፤ አንድ ሸሚዝ(ብላውዝ) አንድ የውስጥ ሱሪ( ሙታንታ) ዋጋው በጠቅላላው 6.65 (ስድስት ብር ከስድሳ አምስት ሳንቲም) ነው፡፡

ለሁለተኛ ደረጃ ወንዶች ተማሪዎች አንድ ቦላሌ፤ አንድ ቁምጣ፤ አንድ ሸሚዝና አንድ ኮት ዋጋው በጠቅላላው 13.20 (አሥራ ሦስት ብር ከሃያ ሳንቲም) ለሁለተኛ ደረጃ ሴቶች ተማሪዎች አንድ ቀሚስ፤ አንድ ሸሚዝና አንድ የውስጥ ሱሪ (ሙታንታ) ዋጋው በጠቅላላው 8.96 (ስምንት ብር ከዘጠና ስድስት ሳንቲም) እንደሚሆን ወሬው በተጨማሪ አስገንዝቧል።

የግልና የሚሲዮን ትምህርት ቤቶች፤ ከትምህርትና ከሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ጋር በመስማማት ተማሪዎቻቸው ዩኒፎርም እንዲኖራቸው ሳይደረግ እንደማይቀር በተስፋ ይጠበቃል ሲሉ አቶ ዓምደ ሚካኤል አስረድተዋል፡፡

(አዲስ ዘመን መስከረም 13 ቀን 1957 ዓ.ም)

የአጭር ቀሚስ ቁጥጥር በሐረር

ሐረር፡ (ኢ-ዜ-አ-) በሐረር ከተማ ውስጥ አጫጭር ቀሚስ እየለበሱ በሚዘዋወሩት ሴቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የሐረር አውራጃ ፖሊስ አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ኃይለሚካኤል ገብሬ ገለጡ፡፡

በተደረገው ቁጥጥር መሠረት በሐረር ከተማ ውስጥ የሀገርን ባሕል የሚያጎድፍ ልብስ ለብሰው የተገኙት 67 ልጃገረዶችና ሴቶች 2ኛ ፖሊስ ጣቢያ እየቀረቡ ዳግመኛ ላለመልበስ መፈረማቸውን ሌተናል ኮሎኔል ኃይለ ሚካኤል አስረድተዋል፡፡

ይኸው አፈጻጸም ለወደፊቱ በየጣቢያው ተላልፎ በሚገባ በሥራ ላይ እንደሚውል ታውቋል፡፡

በዚሁ ይዞታ በከተማው ውስጥ ይታይ ነበረው የአጭር ቀሚስ ለባሾች ቁጥር መቀነሱንና ለወደፊት ጨርሶ እንደሚጠፋ ሌተናል ኮሎኔል ኃይለሚካኤል ገብሬ እምነታቸው መሆኑን ገልጠዋል፡፡

(አዲስ ዘመን ጥቅምት 2 ቀን 1962 ዓ.ም)

ልጃገረዷ በጥፊ ስለተመታች የኩባንያው ሠራተኞች አንሠራም አሉ

ከሌጎስ፤ በናይጄሪያ ውስጥ የሚገኘውን የኪንግስዌይ ግምጃ ቤት ሥራ ይመራ የነበረው እንግሊዛዊው፤ የግምጃ ቤቱ የሽያጭ ክፍል ሠራተኛ የነበረችውን አንዲት ልጃገረድ በጥፊ ስለመታት፤ ይህ ሰው ከሥራው ካልተወገደ በማለት በግምጃ ቤቱ ውስጥ ይሠሩ የነበሩት አንድ ሺህ ናይጄሪያውያን ሠራተኞች ሥራቸውን አቁመዋል፡፡

የግምጃ ቤቱ ባለንብረት የሆነው የተባበረው የአፍሪካ ኩባንያ የሠራተኞች አንድነት ኤክስኪዩቲቭ፤ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ፤ የናይጄሪያዋን ልጃገረድ አደገኛ ጥፊ የመታት የብሪታኒያው ተወላጅ ሚስተር ፒተር ቻድዊክ ከሥራው እንዲወጣ የተጠየቀ መሆኑንና በሚመጣው ቅዳሜ ናይጄሪያን ለቅቆ ይወጣል ሲል አስታውቋል፡፡

የግምጃ ቤቱ የወሬ ምንጭ፤ ሚስተር ፒተር ቻድዊክ የልጃገረዷን ትከሻ መታ በማድረግ በደንብ እንድትሠራ አሳስቧታል ሲል ገልጧል፡፡

በመቶ የሚቆጠር ፖሊስ ግምጃ ቤቱን ከብቦ እንደነበር ወሬው ሲያመለክት፤ እስካሁን አደጋ ያልደረሰ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

(አዲስ ዘመን ኅዳር 26 ቀን 1957ዓ .ም)

ቦንቡን ዕብድ እንዳይተኩሰው

ጥንቃቄ ተደርጓል

ቢትል፤ አንድ አዕምሮው ትክክል ያልሆነ ሰው በድንገት ተነስቶ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን ቃታ በመሳብ ዓለምን ከአደገኛ ሁኔታ ላይ እንዳይጥል አሜሪካ ጥብቅ ቁጥጥር ታደርጋለች ሲሉ፤ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በአንድ የእራት ግብዣ ላይ ተናግረዋል፡፡

የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች እንዲተኮሱ የሚያዘው ፕሬዚዳንቱ ብቻ ነው፡፡ ከእርሱም ጋር ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ይመካከራሉ፡፡

መሣሪያዎቹም የኤሌክትሮኒክስ ቁልፎች ይገኙ ባቸዋል፤ እነዚህንም ቁልፎች ለመፍታት የሚቻለው በምስጢራዊ ዘዴ ነው፡፡ ይህንንም አያያዛችንን በጥብቅ እንከታተላለን ሲሉ መናገራቸውን ሮይተር ገልጧል፡፡

(አዲስ ዘመን የካቲት 13 ቀን 1957 ዓ.ም)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

 

አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2016 ዓ.ም

Recommended For You