ፈተናዎችን የተሻገረው የአፍሪካ ጨዋታዎች

አፍሪካውያንን ከሚያስተሳስሩና እርስ በእርስ ያላቸውን ግንኙነት ከሚያጎለብቱ ጉዳዮች መካከል የስፖርት መድረኮች ጎልተው ይጠቀሳሉ። የአፍሪካ ጨዋታዎች ፓን አፍሪካዊነትን ከማቀንቀን ባለፈ አፍሪካዊያን ወጣቶች የውድድር እድል እንዲያገኙ ከማድረግ አንጻርም ከፍተኛ ሚና አለው። በዚህ እሳቤ የተጠነሰሰው የአፍሪካ ጨዋታዎች በተለያዩ ምክንያቶች ሲካሄድና ሲቋረጥ አሁን ካለበት ደርሷል። ዘንድሮም ለ13 ጊዜ በጋና አስተናጋጅነት ሲካሄድ ቆይቶም ዛሬ ይጠናቀቃል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ረጅም እድሜ ካስቆጠሩ የስፖርት ውድድሮች መካከል ሊጠቀስ የሚችለው የአፍሪካ ጨዋታዎች መነሻውን እአአ 1920 ያደርጋል። የዘመናዊው ኦሊምፒክ መስራችና አባት የሆኑት ፈረንሳዊው ፔሪ ደ ኩበርቲን አማካኝነት መካሄድ እንደጀመረም ይነገራል። ይሁንና በወቅቱ በአፍሪካ ሀገራት ተንሰራፍቶ በነበረው የነጮች የቅኝ አገዛዝ ምክንያት ተቀባይነትን ያገኘ አልነበረም። ቅኝ ገዢዎች ስፖርትን ምክንያት አድርገው አፍሪካዊያን ስለነጻነታቸው የሚሰበሰቡበት መድረክ ይሆናል የሚል ስጋት ነበረባቸው። በዚህ ሁኔታ ያልተሳካው ይህ ሙከራ ከአምስት ዓመት በኋላ በአልጄሪያ አልጀርስ እንዲካሄድ ከውሳኔ ቢደረስም በመጨረሻው ሰዓት ሊጨናገፍ መቻሉን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በ1995 ዓ.ም ያሳተመው መጽሔት ላይ ሰፍሮ ይገኛል።

በድጋሚ እአአ በ1929 በግብጽ አሌክሳንደሪያ ሊካሄድ ተሞክሮ ነበር፣ ይሁንና በራሷ መቆም ያልቻለችው አፍሪካ እንደፈለጉ በሚያደርጓት ቅኝ ገዢዎች በድጋሚ እንዳይካሄድ ተደርጓል። በተደጋጋሚ የተሰናከለው የዚህ ውድድር ሃሳብም ዳግም እውን ሊሆን ሌሎች አስርት ዓመታትን ማስቆጠር የግድ ሆኖበታል። እአአ በ1960 ደግሞ ፈረንሳይ የምትገዛቸው ሀገራት መካከል ‹‹የፈረንሳይ ማህበረሰብ›› ውድድር ለማዘጋጀት ሙከራ ብታደርግም ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮችን ያላሳተፈ በመሆኑ ምክንያት ዓላማውን ሊያሳካ አልቻለም።ነገር ግን ወቅቱ አፍሪካዊያን ሀገራት ከቅኝ ከገዢዎች ተላቀው የራሳቸውን እጣ ፋንታ መወሰንና እርስ በእርስ ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር የጀመሩበት መሆኑን ተከትሎ የመላ አፍሪካዊያን ጨዋታን የሚመለከተውን ጉዳይ አጀንዳቸው ውስጥ ሊያካትቱ ችለዋል።

በአህጉሪቷ የሚገኙ ሀገራትን አንድነት ለማጠናከር ስፖርት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው በመገንዘብ አፍሪካዊያን መሪዎች እአአ በ1963 በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ወቅት ውድድሩ እንዲካሄድ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ታሪክ ያወሳል። ህብረቱ ይህንን ተግባራዊ የሚያደርገው ደግሞ በየሀገራቱ ከሚገኙ ብሄራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ጋር በመሆን ነው። በስምምነቱ መሰረት ውድድሩ በየሁለት ዓመቱ የሚያዘጋጅ ኮሚቴ የሰየሙ ሲሆን፤ እአአ በ1965 የመጀመሪያውን የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች በኮንጎ ብራዛቪል እንዲካሄድ አድርጓል። በዚህ ውድድር ላይ 30 ሀገራት በ2ሺ500 አትሌቶቻቸው ተወክለው ሲሳተፉ ግብጽ ደግሞ በርካታ ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ የደረጃ ሰንጠረዡን በበላይነት ልትቆጣጠር ችላለች።

ቀጣዩ የመላ አፍሪካ ጨዋታዎችን እንድታዘጋጅ የተመረጠችው ማሊ ብትሆንም በወቅቱ በሀገሪቷ በነበረው የመንግሥት ለውጥ ምክንያት ሊካሄድ ባለመቻሉ ለተጨማሪ ዓመት ሊራዘም የግድ ሆኗል። እአአ በ1971 ሁለተኛውን የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች እንድታዘጋጅ ናይጄሪያ ተመራጭ ብትሆንም የዝግጅት ጊዜው አንሷል በሚል እስከ 1973 ሊራዘም የግድ ሆኗል።ከዚያ በኋላ ያሉት ዓመታት የተለመዱት የአፍሪካዊያን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አንዳንድ መስተጓጎሎች ይከሰቱ እንጂ በየአራት ዓመቱ የተሳታፊ ሀገራትን ቁጥር እንዲሁም ውድድር የሚካሄድባቸውን ስፖርቶች በማሳደግ 13ኛው ላይ ደርሷል። በእርግጥ እንደ ውድድሩ ኦሊምፒክ ከሚካሄድበት አንድ ዓመት ቀድሞ የሚከናወን ቢሆንም በታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ የውድድሩ አዘጋጅ የሆነችው ጋና መሰናዶዋን ባለማጠናቀቋ ምክንያት ተራዝሞ የፓሪሱ ኦሊምፒክ ወራት ብቻ እየቀሩት ተካሂዷል፡፡

145 ሚሊዮን ዶላር በወጣበት በዚህ ውድድር ላይ ከ54 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡና ከ2ሺ600 በላይ የሚሆኑ አትሌቶች በ30 ዓይነት ስፖርታዊ ውድድሮች ለአሸናፊነት ተፋልመዋል። ይህም እአአ በ2019 በሞሮኮዋ ራባት ከተካሄደው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች በአራት ብልጫ ያለው ነው፡፡

አፍሪካዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ አቋም ያላት ኢትዮጵያም በዚህ ውድድር ከመጀመሪያው አንስቶ ስትሳተፍ ቆይታለች። ይሁንና የምትሳተፍባቸው የውድድር አይነቶች ጥቂት በመሆናቸው ምክንያት በርካታ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ስሟን ከሜዳሊያ ሰንጠረዡ አናት ማሳረፍ አልቻለችም። ባለፉት 12 የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ተሳትፎዋም 45 የወርቅ፣ 54 የብር እንዲሁም 75 የነሐስ በድምሩ 174 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ በደረጃ ሰንጠረዡ 7ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You