የኮንጎና ኮርያ ዘማቹ ጀግና

ወታደር ላቀው ኪዳኔ ይባላሉ። ስለ ዓደዋ አውርተው አይጠግቡም። አያቶቻቸው የዓድዋ ዘማቾች በመሆናቸው ደግሞ ፍቅሩና ስሜቱ የተለየ ነው። ‹‹ክተት ሰራዊት ምታ ነጋሪት የሚለውን የእምዬ ምኒልክን ጥሪ ሰምቶ ከአራቱም የሀገሪቱ መአዘናት እየተጠራራ የዘመተው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው። እከሌ ዘምቷል፤ አከሌ አልዘመተም ለሚል ወሬ አይመችም›› ሲሉም ይገልጻሉ።

ወታደር ላቀው ስለ ዓድዋ ጦርነት፤ ስለተገኘው ድል፣ ስለ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ጀግንነት ታሪኩን ለሌሎች መንገር ያስደስታቸዋል። እርሳቸው የዘመቱበትን የኮንጎና ኮርያውን ጦርነት የሚያወጉት እንኳን ስለ ዓድዋው ጦርነት ብዙ ካስረዱ በኋላ ነው። በጨማታቸው መካክል ስለዓደዋ ሳያነሱ አያልፉም። ታሪኩንም ከአያቶቻቸውና ከአባታቸው ስለሰሙ ጠንቅቀው ያውቃሉ።

‹‹ለአንዲት ኢትዮጵያ ሲሉ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ደማቸውን አፍስሰዋል፣ አጥንታቸውን ከስክሰዋል፣ ህይወጣቸውንም ሰጥተዋል›› የሚሉት ወታደር ላቀው፤ ድሉ እጅግ ደማቅ፤አንፀባራቂና በጭቆና ስር ለነበሩት አገራት በሙሉ ብርሃን ያሳየ መሆኑንም ያብራራሉ። ድሉ «መከራን፣ ጭቆናን፣ ተገዢነትን ማሸነፍ ይቻላል፤ ነፃ መውጣት ይቻላል» የሚል አስተምህሮ ዓደዋ ተራሮች ላይ ለዘላለም እንዲቀረጽ ስለማድረጉ ፤ከሁሉም በላይ የዓድዋ ድልን ልዩና ሰርክም አዲስ የሚያደርገው መለያ ስለመሆኑ አበክረው ያስገነዝባሉ።

ሀገር ተወራለች፣ ዳር ድንበር ተጥሷል በማለት ሽማግሌ፣ አሮጊት፣ ወጣቱም ሆነ ጎልማሳው የሀገሩን ዳር ድንበርና ነፃነት ለማስከበር የተመመበት ስለመሆኑ በመረጃ እያስደገፉ ያነሳሉ። በአንድነት ተመው ግማሽ ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጦርነቱን በድል መወጣት እንደቻሉም ይናገራሉ። ዓድዋ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን ጭምር ትልቅ ኩራት እንደሆነ ደጋግመው ይናገራሉ።

ስለዓደዋ ጦርነትና ስለተገኘው ድል አውርተው የማይጠግቡት ወታደር ላቀው፤ታሪካቸውን ለመስማት በዙሪያቸው ሰዎች ሲሰበሰቡ በጣም ይደሰታሉ። በተለይም ወታቶች በትእግስት ሲያዳምጧቸው እንደሚደሰቱ ይገልጻሉ። አንዳንዶችም ታሪክ አዋቂነታቸውንና ለትውልድም ለማስተላለፍ የሚያደርጉትን ጥረት ያደንቁላቸዋል።

እኛም ባገኘናቸው ጊዜ በወጣቶች ተከበው ያለፈውን ታሪክ ሲያወሩላቸው ነበር።ከእኛም ጋር ወግ የጀመሩት እንዲሁ ስለ ዓድዋ ታሪክ በማውሳት ነው። ታሪኩን ደግመው ለእኛ ሲያወሩ ወጣቶቹ እንደገና እንደአዲስ ነበር በትኩረት ይሰሟቸው የነበረው። ወታደር ላቀው እርሳቸውም ታሪኩን ለሌላው ሲነግሩ በስሜት ውስጥ ሆነው ነው። ታሪኩን ሲያወሩም ከ126 አመት በፊት የተፈፀመ አይመስልም። በወጋቸው መካከልም ዓይናቸውን ጨፍነው ረዘም ላለ ሰአት በተመስጦ ይቆያሉ። ታሪኩን እንዲህ በተመስጦነና በወኔ ሲያወሩ የ80 አመት የእድሜ ባለፀጋ አይመስሉም።

በዙሪያቸው ሆነው የስሟቸው የነበሩ ወጣቶችም በወኔያቸው እየተደነቁ ነበር የሚያዩዋቸው። መገረማችንን ለመግለጽ ስንተያይ ወታደር ላቀው ድንገት ከእንቅልፉ እንደባነነ ሰው የጨፈኑትን ዓይናቸውን ገልጠውና ተነቃቅተው ..የሚገርማችሁ ስምምነቱ ስውር ደባ ያለው መሆኑ እኮ ነው..ሲሉም በሰፊው የጀመሩልንን የዓደዋ ጦርነት ወግ ቀጠሉ። በውሉ አንቀፅ 17 የጣሊያንኛ ቅጅ መሠረት ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነቷን የምታደርገው በጣሊያን በኩል እንደሆነ የሚያስገድድ መሆኑንም አነሱልን። ይሄም ኢትዮጵያ በተዘዋዋሪ በጣሊያን ሞግዚት የምትተዳደር የሚያደርጋት በመሆኑ ውሎ ሳያድር የስምምነቱ አንቀፅ 17 ውዝግብ ስለማስነሳቱም አከሉልን።

ስለ ጦርነቱ መንስኤ በሰፊው እየዘረዘሩ ያስረዱን ገብተዋል። የአንቀጽ 17ቱ መዘዝ በ1887 ዓ.ም በወርሀ መስከረም በገበያ ቀን ቅዳሜ አፄ ምኒልክ ታሪካዊውን የ «ወረ ኢሉን » ክተት አዋጅ «…አገርንና ሃይማኖት የሚያጠፋ ጠላት ባሕር ተሻግሮ መጥቷል። እኔም የአገሬ ሰው መድከሙን አይቼ ብታገሰውም፤ እያለፍ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፤ አሁን ግን በእግዚአብሔር እርዳታ አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም።ያገሬ ሰው ጉልበት ያለህ ተከተለኝ፤ ጉልበት የሌለህ በጸሎትህ እርዳኝ ፤ …» ሲሉ ማወጃቸውን አጫውተውናል።

እንዲህም ሆኖ አፄ ምኒልክ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ከጦርነት ጥፋት እንጂ ልማት እንደማይተርፍ በመገንዘብ ወራሪው የጣሊያን ጦር ከግዛታቸው ለቆ እንዲወጣ ጠይቀዋል፤ ግን ቀና መልስ አላገኙም። ወራረሪው አሻፈረኝ ከማለቱ ባሻገር በዕብሪት የማይሆን ቅድመ ሁኔታ በመደርደር እሳቸውንና ሀገራቸውን ለማስፈራራት ሞክሯል። ወራሪው በእብሪትና በድፍረት ይደረድራቸው ከነበሩት ውስጥም የአፄምኒልክ ጦር ትጥቅ እንዲፈታ፣ ራስ መንገሻ እንዲታሰሩ፣ መላውን ትግሬን እንዲያስረክብ እና የጣሊያንን የበላይነት እንዲቀበል የጠየቀበት ይጠቀሳልም ይላሉ። እንደ ወታደሩ ገለፃ በዚህም ጦርነቱ አይቀሬ መሆኑ ተረጋገጠ። አፄ ምኒልክ ክተት ሰራዊት ምታ ነጋሪት አዋጁም ለመታወጅ በቃ። – – -አዋጁን ተከትሎ በአፄ ምኒልክ አዝማችነት፣ ከመላው አገሪቱ በከተቱት መኳንንትና መሳፍንት ባለሟልነት ከ100 ሺህ በላይ ወዶ ገብ የገበሬ ጦር እና 29 ሺ ፈረሰኞች በኢትዮጵያዊ አንድነት፣ ጀግንነት፣ ቆራጥነት፣ አልበገር ባይነት፣ ዳር ድንበሩን ፣ ሉዓላዊነቱን ሊያስከብር ቀፎው እንደተነካ ንብ ወደ ሰሜን መትመሙንም አብራርተውልናል ወታደር ኪዳኔ ላቀው። የተመመው ደግሞ የጎርጊስን ታቦት ይዞም ነበር። እንዳከሉልን ታድያ ወራሪው ጣሊያን የመጀመሪያውን የሽንፈት ጽዋ ተከናነበ።

በሁለት ሰዓት ውጊያ አምባላጌ ላይ ነበር ፋሽስቱ የሽንፈት ጽዋውን የተከናነበው። ንጉሰ ነገስት ሚኒልክ ከነሠራዊታቸው ወደ ሰሜን መትመማቸውን ተከትሎ የፋሽስት ጣሊያን ሰራዊት ወደ መሀል ትግሬ እንዲንቀሳቀስ ትዕዛዝ ሰጠ።የአምባላጌው አኩሪ ድል ኢትዮጵያውያን በጣሊያን ላይ የተቀዳጁት የመጀመሪያው ታላቅ ፋና ወጊ ድል መሆኑም በፍጥነት በዓለም ናኘ።

ኢትዮጵያ በብልሁና በመለኛው አፄ ምኒልክ መሪነት የተቀዳጀችው የዓደዋ ድል ከወታደራዊ ስኬቱ በላይ ሃይማኖታዊ፤ ስነ ልቦናዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው እጅግ የጎላ ለመሆን መቻሉንም ወታደር ላቀው ኪዳኔ አውግተውናል። ኢትዮጵያውያን የውጭ ኃይልን ድል መንሳት እንደሚችሉ ያረጋገጡበት፤ የአፄ ምኒልክን ጦር የውጊያሞራል ያነቃቃ ከመሆኑ ባሻገር በአገር ውስጥም ሆነ በውጭም የንጉሡ ክብር፣ ከፍ ያለ ተቀባይነት እንዲያገኝ አስችሏል። የአፄ ምኒልክ ጦር ግስጋሴውን ቀጥሎ መቀሌን ተቆጣጠረ። ይሄን ተከትሎ ስብሀትና ሀጎስ የተባሉ ለጣሊያን ያደሩ ባንዳዎች ከድተው ለንጉሡ መግባታቸው ለወራሪው አስደንጋጭ መርዶ ነበር። የንጉሡ ጦር በወርሀ የካቲት እኩሌታ ለዓድዋ ጥቃት ዝግጁ ሆነ። የጣሊያንና የኢትዮጵያን ጦር ወዲህና ማዶ ተፋጠጠ። የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በተካሄደ ጦርነት የፋሽስቱ የጦር መሪውና ሌሎችም ጄኔራሎች ጦር ተሸነፈ። ሸሸ። ወደ 11ሺህ የሚጠጋ የጣሊያን ጦር ሙት፣ ቁስለኛ፣ ምርኮኛ ሆነ ፤

እኝህ በአደዋ ወኔ የተቃኙ ጀግና ወታደር ኪዳኔ ላቀው እንዳወጉን የዓደዋ ድል ኢትዮጵያ በጦርነት አውዶች በመሳተፍ ጭምር የሌሎች ሀገራትን ነፃነት በማስከበሩ ረገድ ታማኒነት እንድታገኝ አድርጓል። ወታደር ኪዳኔ ላቀው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥያቄ መሠረት ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ1951 ወደ ኮርያ እንዲዘምቱ ጥሪ ካቀረበችላቸው የቃኘውን ሻለቃ ጦር ሠራዊት አባላት መካከል አንዱ ለመሆን የበቁት በዚሁ መልኩ ኢትዮጵያ ተመራጭ በመሆኗ እንደሆነም በመጠቆም ነው ወደ ራሳቸው የጀግንነት ገድል የተሸጋገሩት።

ወታደር ላቀው ከኮርያ ዘመቻ መልስ በቀጥታ ደግሞ ባልበረደ ወኔ ወደ ኮንጎ ለመዝመት የበቁ ጀግና ወታደርም ነበሩ። የ87 ዓመቱ ወታደር ላቀው እንደሚያስታውሱት ያኔ ኮርያ ሲዘምቱ ታላቅ ወንድማቸው ሙሉነህ ላቀውም አብረዋቸው ነበሩ። ስሙ በታላቅና ታናሽነት ይጠራ እንጂ ዕድሜያቸው ብዙም ርቀት አልነበረው። ኮርያ ሲዘምቱ ታላቃቸው የ17 እሳቸው ደግሞ የ15 ዓመት ዕድሜ ታዳጊዎች ነበሩ።

ሁለቱም በክቡር ዘበኛ ውስጥ ተቀጥረው ብዙም ሳይቆዩ ነው የቃኘው ሻለቃ ጦር ሠራዊት አባል በመሆን ሰላም ለማስከበር ወደ ኮርያ የዘመቱት። አባታቸውም ለረጅም ጊዜም በውትድርና ሙያ አገልግለዋል። እሳቸውና ወንድማቸው ግን በአባታቸው በቤት ውስጥ ጥብቅ የሆነ ወታደራዊ ስነስርዓት እንዲተገብሩ ተደርገው ከማደጋቸውና፤ በአካባቢውም የአባታቸውን ጀግንነት የሚመስል ወኔ ታንፀባርቃላችሁ ከመባላቸው ውጭ ልጆች በመሆናቸው ስለ ውትድርና ሙያ በጥልቀት የሚያውቁት ብዙም ዕውቀት አልነበራቸውም። በተለይ ኮርያ ሲዘምቱ ስለውጊያ የነበራቸው ዕውቀት አልነበረም።

አሁን አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ “የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ብሔራዊ ፓርክ ተብሎ በሚጠራው ፊት ለፊት ባለውና ‹‹ዘበኛ ሰፈር››እየተባለ በሚጠራው ሰፈር ውስጥ ቀኑን ሙሉ ያሳልፉት የነበረው ኳስ በመጫወት እንደነበርም ያወሳሉ። ታድያ አንድ ቀን አባታቸው ከዚሁ ኳስ ሜዳ መጡና ሁለቱንም ወደ ከቡር ዘበኛ ወስደው አስረከቧቸው። ኳስ ጨዋታው በዚሁ ተቋጨ።ሥራ መቀጠራቸውን ሁሉ ያወቁት ይሄን አድርጉ ፤ይሄን አድርጉ የሚል ትዕዛዝ ሲሰጣቸውና ወታደራዊ ስልጠና ለመውሰድ ዝግጅት እንዲያደርጉ ሲነገራቸው ነበር።

የወንድማቸውን ለጊዜው እኛ ስንጠይቃቸው ትዝ ባይላቸውም ሥራውን ሲቀጠሩ እሳቸው የሦስተኛ ክፍል ደረጃ የቀለም ትምህርት እንደነበራቸውም

ያወሳሉ። እናም ክቡር ዘበኛ በሬዲዮ ኦፕሬተር ሙያ አሰለጠናቸውና እዛው ክቡር ዘበኛ ውስጥ መሥራት ጀመሩ።አሁን ሲያስቡት እንደሚመስላቸው አባታቸው ታናሽና ታላቅ የሆኑትን ልጆቻቸውን ከማስተማር ይልቅ ገና በታዳጊነታቸው ወደ ክቡር ዘበኛ ወስደው ያስቀጠሯቸው ደሞዛቸው 18 ብር ብቻ በመሆኑ የሚያስተምሩበት እጅ አጠሯቸው ሊሆን ይችላል።የያኔ 18 ብር የወታደር ደሞዝ ምንም እንኳን ኑሮ ርካሽ በመሆኑ ይበቃል ቢባልም ቤት ኪራይ ለመክፈል ፣ለቀለብ፣ የነሱን ተከታይ ትንንሽ ልጆች ለማስተማር በፍፁም የሚያስችል አልነበረም። በዚህ ላይ ከ18 ብሩም የሚቆራረጥ ነበር። ከተቆራረጠ በኋላም እንደገና በየጊዜው ለዚህ ለዚህ ተብሎ የሚዋጣ ገንዘብ በመኖሩ አባታቸው ቤተሰቡን ለማስተዳደር ተቸግረው እንደነበር ያስታውሳሉ። ልጆቻቸው የጀግንነት ወኔያቸውን እንዲወርሱላቸው አስበው ሊሆን እንደሚችልም ይገምታሉ።

የክቡር ዘበኛ ቅጥር የመሆናቸው ምክንያት ያም ሆነ ይህ ተረጋግጦ ባይታወቅም ታናሽና ታላቅ ወንድማማቾቹ እ.ኤ.አ በ1951 ወደ ኮርያ ዘመቱ።የዘመቱት ወታደራዊ ግዳጅ ተብሎ ብቻ ስለተጫነባቸው ብቻ ሳይሆን በሙሉ ፈቃደኝነት ነበር። ወንድማቸውም ሆኑ እሳቸው ለዘመቻው መመልመላቸው ጮቤ እስኪረግጡ አስደስቷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። በእርግጥ ደቡብ ኮርያን የመርዳት ተግባሩ የተቀደሰ ነው ባይ ናቸው። ከኢትዮጵያ ውጪ ያለ አገር የማየት አጋጣሚውም በራሱ እንደ ታዳጊ ወጣት የሚፈልጉት ነበር።በዚህ ሁሉ ምክንያት በወኔ ነው የዘመቱት። እንዴውም የያኔ ስሜታቸውን አሁን ላይ ሲያስቡት በቀጥታ የአባታቸውን የጀግንነት ወኔ በመውረሳቸው የተፈጠረ ነው ብለው ያምናሉ። ወታደር ላቀው ገና ከኢትዮጵያ ሲነሱ ከነበረው ጀምሮም የነበረውን የዘመቻ ሂደቱን አጫውተውናል።

ታድያ ጀግናው ወታደር እንዳወጉን እሳቸው የከባድ መሣርያ ሻምበል ከሆነው አራተኛ ሻምበል፤ታላቅ ወንድማቸው ሙሉነህ ኪዳኔ ደግሞ የደረጃ ጦር ከነበረው ሦስተኛው ሻምበል ተቀላቅለው ነው ወደ ኮርያ የዘመቱት።እሳቸው የነበሩበት የመትረየስ የ100 የሬዴዮ መገናኛ ኦፕሬተሮችን የያዘም ነበር።ይሄ እሳቸው የነበሩበት የመቶ ለብቻው 36 ወታደሮችን አቅፎም የያዘ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሰፈር የ100 አለ ፤የ100 81 የሚባልም ነበር። ከባድ አዳፍኔ የመቶና በቀጥታ የሚተኮስ መሣርያ የሚያስተናግድ 75 የሚባልም ነበር። ታድያ የሻምበሉ አዛዥ ሻምበል ፀጋዩ ጣሰው ሲሆኑ የእሳቸው አለቃ ደግሞ መኮንን ወልዴ ይባላሉ። ሁሉንም አጠቃሎ የያዘው ደግሞ የቃኘው ሻለቃ ጦር ይባላል።

እናም ከዚሁ ቀድመው ገና በታዳጊነት ዕድሜያቸው በመዝመት ከተሰለፉበት የኮርያ ጦርነት ጀምረው በአጭሩ እንዳወጉን ወታደር ላቀው የዘመቻ ኮሪያ ጉዞ በየዙሩ ነው የተካሄደው። ዙሮቹ እስከ አራት ይደርሳሉ። ታድያ እሳቸውና ታላቅ ወንድማቸው የመጀመርያው ጦር ከዘመተ ብዙ ዘግይተው ነበር ወደ ዘመቻ የሄዱት።በዚህ ወቅት ተጋግሎ የነበረው ጦርነትም እየተቀዛቀዘ መጥቶ ወደ ማብቂያው እየተቃረበ ነው ማለት በሚያስችልበት ደረጃ ደርሶም ነበር ቢባል የማያስደፍር አይሆንም። በተለይ በመጀመርያውና በሁለተኛው ዙር ወደ ኮርያ የዘመቱት ኢትዮጵያዊያን ብዙ መስእዋትነት የተከፈለበት የጦርነት ውጊያ ላይ ተሳትፈዋል።

ግግር በረዶ ላይ የተቀበሩ ፈንጂዎች ከማምከን ጀምሮ በደፈጣና በሽምቅ ውጊያ በከፍተኛ ወኔ ተሳትፈዋል። ተሰውተዋል። በሁለተኛው ዙር የተጓዘውና ‹ቲቮ›በተሰኘው ከፍተኛ በረዷማ ተራራ ላይ በተደረገው ውጊያ ሁሉ በመሳተፍ የላቀ መስዕዋትነት ከፍለዋል። በጦርነቱ ማብቂያ ከአሜሪካ ወገን ሆነው ከተዋጉት ሃያ አንድ ሀገራት መካከል ሁሉም በኮሙኒስቶች እጅ የወደቁ ምርኮኛ እስረኞች የነበራቸው ሲሆኑ ኢትዮጵያ አንድም ምርኮኛ እስረኛ ያልነበራት ብቸኛ አገር የመሆኗ ምስጥርም ይሄው የሰራዊቱ ብቃትና በወኔ የመሳተፍ ጉዳይ ነው ብለው ያምናሉ።ብዙዎች የሚሰውት የተሰውትን ጓዶቻቸውን ተሸክመው ለማዳን ሲሉ እንደነበረምና ጀግንነታቸው እዚህ ድረስ የዘለቀ እንደሆነም ያክላሉ።

ታድያ ወደራሳቸው የጦርነት ዘመቻ ጉዞ መለስ ብለው ወታደሩ እንዳጫወቱን ከአዲስ አበባ ሲንቀሳቀሱ መነሻቸው የነበረው ጃንሜዳ ነበር። እዚህ የመጡት ማክ በሚባል ወታደራዊ መኪና ነው ።ከጃንሜዳ ደግሞ በባቡር ወደ ጅቡቲ አመሩ። አሁን የቀናቶቹን ቁጥር ባያስታውሱትም ከጅቡቲ ከ20 ቀናት በላይ ተጉዘው ነበር የኮሪያ ባህር በር ፑዛን የገቡት።

ቀድሞ ቢነገራቸውም ኮርያ ሲደርሱ እንዳረጋገጡት ሰሜን ኮሪያ ደቡብ ኮሪያን በመውረሯ ነው የኢትዮጵያውያኑ እገዛ ያስፈለገው። በአጭሩ ደቡብ ኮርያን መርዳት ነበር የዘመቻው ዓላማ ።ታድያ በወቅቱ ወንድማቸውና እሳቸው የተለያዩት ኮርያ ባህር በር ፑዛን ሲደርሱ ነበር።ታላቃቸው በሽምቅና ደፈጣ ውጊያ ለመሳተፍ በሚያስችለው ቡድን ተቀላቅለው ሲሄዱ እሳቸው በበኩላቸው በፑዛን ለተወሰነ ቀን አረፉና በመገናኛ ሬዴዮ ኦፕሬተር ሙያቸው ወደ ሌላ ቦታ በመሄድ ግዳጃቸውን ለመወጣት በቁ።

በኮንጎ ዘመቻ የተሳተፉት ደግሞ ከዚህ ከኮርያ ዘመቻ መልስ ነው።ታላቅ ወንድማቸው ከዓመታት ቆይታ በኋላ ከኮርያ ዘመቻ በሠላም ወደ ኢትዮጵያ ቢመለሱም በኮንጎ ዘመቻ አልተሳተፉም። እሳቸው ኮንጎ የዘመቱት ከኮርያ ዘመቻ መልስ ብዙ ራሳቸውን በትምህርት መለወጥ የሚያስችል ተግባር ሲከውኑ ቆይተው ነበር።ክቡር ዘበኛን በቅጥር ሲቀላቀሉ የትምህርት ደረጃቸውን ለማሻሻል ጥረት በማድረግ በሬዲዮ ቴክኒሻል ሙያ በዲፕሎማ ተመርቀዋል።

ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው ዳግመኛ በኮንጎ ዘመቻ ሊሳተፉ የቻሉት። ወታደር ላቀው እዚህ ሲሳተፉም ወኔያቸው አልበረደም።በኮርያው ዘመቻ፤ ከዘመቻው ቀደም ብሎ የወሰዱት የስምንት ወር ያህል ወታደራዊ ስልጠና ከወታደሩ አባታቸው ከወረሱት የጀግንነት ዕውቀት ጋር ተዳምሮ ለኮንጎው ዘመቻ በጥሩ ሁኔታ መቅረብ የሚያስችል ዝግጅት አስታጥቋቸውም ነበር። ይሄኔ ታድያ ወታደር ላቀው በዕድሜም ቢሆን ጎልብተዋል፡፤ አስተሳሰባቸውም የዚህኑ ያህል ጨምሯል።

እዚህም ዘመቻ ሲሄዱ ከአዲስ አበባ ኢትዮጵያ የተነሱት ከተመሳሳይ ቦታ ነው።ጅቡቲ ድረስም በመርከብ ወደ ኮንጎ መጓዛቸውን ያስታውሳሉ። ከመርከብ ተራግፈው ኮንጎ ሲገቡ ያረፉባት ቦታ ትዝ ባትላቸውም ከዚህች ሥፍራ ተነስተው ወደ ኮንጎ ዋና ከተማ ሌዎፓልድቪል መጓዛቸውን ያወሳሉ። ይሄ ከተማ ቀደም ብሎ ኮንጎ ኪንሻንሳ አሁን ደግሞ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ በመባል የተሰየመው ነው።እዚህ ከባድ የሚባል ጦርነት ባይኖርም አልፎ አልፎ በእርስ በእርስ ግጭት የሚቀሰቀሱና ወደ ከባድ ጦርነት ሊያመሩ የሚችሉ ችግሮች እንደነበሩ ይገልጻሉ።

አንዴ እንዴውም ይሄን የመሰለ ግጭት ተቀስቅሶ እሳቸውን ጨምሮ በሥፍራው የነበሩት ወታደሮች ግጭቱን በመቆጣጠር አብርደው ከተማይቱን ከጥፋት ያዳኑበት ሁኔታም እንደነበረ ያወሳሉ። ታድያ እዚህ ለእያንዳንዳቸው ድንኳን ተሰጥቷቸው ከዓመት በላይ ቆይተዋል። ሁለቱም ሀገራት ላይ በተሳተፉበት ዘመቻ እንደታዘቡት ፍራፍሬና አትክልት በደንብ በመኖሩ የሚበላ ነገር ችግር የለም። የታሸጉ ምግቦች በተለይም ሥጋ ነክ የሚቀርብላቸው ቢሆንም የፓስታና ሩዝ የምግብ አይነቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬ ነበር የሚያዘወትሩት። እሳቸው ባያጋጥማቸውም አንዳንድ ባልደረቦቻቸው በእረፍት ጊዜያቸውና በሥራ ምክንያት ኮንጎ ውስጥ ያሉ የተለያዩ አካባቢዎችን የማየት ዕድሉ ነበራቸው።እሳቸው የዘመቻ ግዳጃቸውን አጠናቅቀው የተመለሱት ከዛችው ከተመደቡባት ሌዎፓልድቪል ሳይወጡ ነው። ወንድማማቾቹ እነ መንግስቱ ነዋይና ግርማሜ ነዋይ በአፄ ኃይለስላሴ ላይ ክቡር ዘበኛ በስፋት የተሳተፈበት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ሲያደርጉ እሳቸው እዚህች ከተማ ነበሩ። ዜናውንም እዚሁ ሆነው ነው የሰሙት። መኮንኖቹ በሙሉ ታዲያ አፄ ኃይለስላሴን የሚቃወሙና የ18 ብር ደሞዝ መሻሻል አለበት የሚል ሀሳብ የሚያራምዱ ነበሩና ይሄን የሰሙ ሰሞን በር የሚከፍቱት ሁሉ በእግራቸው ነበር። እነሱ በበኩላቸው በተለይ የመገናኛ ሬዴዮ ኦፕሬተር ክፍሉ ለአፄ ኃይለስላሴ የሚያዝንበት ሁኔታ ነበር።

ወታደሩ በዚህ ሁኔታ ግዳጃቸውን ጨርሰው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የክቡር ዘበኛ ቤት እንደ ፊቱ አልሆነላቸውም። የኮንጎ ዘማቾችና በመፈንቅለ መንግሥቱ ምክንያት ብዙ ሰዎች ተቀይረዋል። ስለዚህ በሬዴዮ ኦፕሬተር ሙያቸው ያገኙትን ዲፕሎማ ይዘው ፕሊፕስ ሬዴዮና ቴሌቪዥን ካምፓኒ ተቀጠሩ። ከ18 ብር ወደ 1ሺህ 200 ብር ያደገ ለውጥ ማየት በራሱ ለእሳቸው አስደሳች ነበር።

በዚህ ላይ የራሳቸው መኪና ተሰጥቷቸው በየሰው ቤት በመላካቸው እየዞሩ ሬዴዮና ቴሌቪዥን ይሰራሉ። እዚህ ካንፓኒ ለ17 ዓመታት ሰርተው ነው ጡረታ የወጡት። በዚሁ መካከል ትዳር መስርተው ለ17 ዓመት ቆይተዋል፡፤ ሆኖም የእግዚአብገሄር ፈቃድ ሳይሆን ቀርቶ ልጅ ማፍራት አልቻሉም። እና በ17ዓመታቸው በቃሽኝ በቃኸኝ ተባብለው በሰላም ተለያዩ። እሳቸው ከትዳር ውጪ የወለዷቸው ሁለት ሴቶች ልጆች አሏቸው። ቢሆንም ኮርያ በመዝመታቸው የተባበሩት መንግሥታት ከሰጣቸው ከፍተኛ ብር በ2ሺህ ብር በገዙት 900 ካሬ ቦታ ላይ የተገነባ ቤት ልጆቻቸው ዶክመንቱን ከሳቸው በመውሰድ በማያውቁት ሁኔታ በራሳቸው ስም ስላዛወሩባቸው ከ300 ብር ጡረታ ውጪ ምንም ሌላ ገቢ የላቸውም። ልጆቹ በአራት ወርና ቆይቶ አንድ ሺህ ብር ሁለት ሺህ ብር በአካወንታቸው ያስገቡላቸዋል። አሁን ላይ ፍቺ ከፈፀሙ በኋላ ካገቧቸው ባለቤታቸው ጋር ጀሞ ኮሚናል ቤት ከሦስት ሺህ ብር በላይ ተከራይተው ነው ሕይወታቸውን እየገፉ የሚገኙት። 300 ብሩን የጡረታ አበላቸውን ጨምረው የቤት ኪራይና የቀለብ ወጪዎቻቸውን ለመደጎም በ87 ዓመታቸው አቅም ኖሯቸው የሚሰሩት ሥራ ባይኖርም የኮርያ መንግሥት አፍንጮ በር ናይጄሪያ ኤምባሲ አጠገብ የሚገኘውና “የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ብሔራዊ ፓርክ “ተብሎ የተሰየመው ማህበር ጥሎ አልጣላቸውም። ይዘው የሚንቀሳቀሱትንና ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ልግዛ ቢባል ከ10ሺህ ብር በላይ የሚጠየቅበትን ከዘራ ከመስጠት ጀምሮ በተለያየ ነገር እየደገፋቸው ይገኛል። ግን በቂና ቋሚ ስላልሆነ እየተቸገሩ ነው።

አሁን ላይ እሳቸው በሕይወት ቢቆዩም አብረዋቸው ኮርያ እና ኮንጎ የዘመቱት አብዛኞቹ በህይወት አለመኖራቸውን ነው የገለጹት። በህይወት ያሉትም ጥቂቶቹም ቢሆኑ በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኙት። በተለይ ኮንጎ የዘመቱት ማህበር ባለመመስረታቸው ስለሌላቸው ሕይወታቸውን እንኳን የሚያቆዩበት ዕድል ሳይኖር አስታዋሸ አጥተው በመጠለያና በምግብ እንኳን በመቸገር ይሰቃያሉ። እንዲህ ለሀገር ውለታ የዋሉ ጀግኖችን በመንከባከብ ውለታቸውን መመለስ ይጠበቃል።

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን መጋቢት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You