ዓባይ ከቁጭት እስከ ድል

ዓባይ ረጅም ነው ከቁጭት እስከ ድል ድረስ።የዛሬ 13 ዓመት በወርሀ መጋቢት በ24ኛው ቀን በኢትዮጵያውያን ጽኑ ተጋድሎ ዓባይ መሰረቱን ጣለ።የዘመናት ቁጭት መልስ ያገኘበት የኢትዮጵያውያን የህብረትና የጽናት ሀውልት ሆኖ እንሆ ዛሬ ላይ ደረሰ።አባቶቻችን ዓባይን ለመገደብ ምን ያክል ጥረት እንዳደረጉ የሚታወቅ ሲሆን ይሄኛው ትውልድ እልህንና ቁጭትን ለመጪው ትውልድ አላስተላልፍም ሲል በዓባይ ላይ ባለታሪክ በመሆን አሻራውን አሳርፏል፡፡

ዓባይ በሁለት የተለያዩ ፍቺዎች ዋና እና ዓባይ ሆኖ ለብዙኃን የእርግማንና የምስጋና ስንኝነት አገልግሏል።በደጃችን ሲያገድም በቁጭት ቆመን የምናይበት ዘመን አብቅቶ ከእርግማን ወደምርቃት፣ ከወቀሳ ወደሙገሳ ተላልፈን ዓባይ አባታችን ማለት ጀምረናል።አንድነትና መተባበርን ባህል ላደረገ ማህበረሰብ የትኛውም ችግር ከአቅሙ በላይ አይሆንበትም።በዘመናት የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከሰው ልጅ አቅም በላይ ሆነው ያለፉ ችግሮች ሁሉ በአንድነትና በተባበረ ክንድ ስላልተመከቱ ነው የሚለው ሀሳብ ሚዛን ደፍቶ እናገኘዋለን፡፡

ግብጽ ዓባይ ለዘመናት ለብቻዋ ስትጠቀምበት የነበረው ዘመን አልፎ ህቅ እያላትም ቢሆን ወደትውልድ ሀገሩ ተመልሶ የከዳውን ህዝብ ሊክስ ትንሳኤው ላይ ደርሷል።ፈረኦኖቼ የኢትዮጵያንና የዓባይን ተፈጥሮአዊ ትስስር ለመበጠስ የዓባይን ስም ከመቀየር ጀምሮ መነሻው ሰከላ ሳይሆን ሜዲትሪሊያን ባህር ነው ወደሚል ራስ ተኮር እሳቤ ስር ወድቀው ግራ ገብቷቸው ግራ ሲያጋቡ ሰንብተዋል።ይሄ ራስን ብቻ የመጥቀም አካሄድ ሳያዋጣቸው ዓባይ ከነስሙ፣ ከነክብሩ በትውልድ መንደሩ ላይ ተሞሽሮ ሀይሎጋ እየተባለለት ነው፡፡

ግብጽ ውስጥ ከዋና ከተማዋ ካይሮ በተጨማሪ ለዋና ከተማነት የቀረቡ የተለያዩ ከተማዎች አሉ።እነዚህ ከተማዎች ካሸበረቁበትና በቱሪስት መስህብነትም ሆነ በውብ ከተማነት የደረጁት የዓባይን ውሀ እየጠጡ፣ በዓባይ የብርሀን ምንጭነት እንደሆነ የማይታበይ እውነታ ነው።ከዚህ በተጨማሪ በኢኮኖሚና በታዳሽ ሀይል ከአፍሪካ ገና ከፊት በመቀመጥም የአባይን ውለታ ማንሳት ይቻላል፡፡

በአጠቃላይ ሀገራዊ ምርትና በነፍስ ወከፍ ክፍያም መልህቋን ዓባይ ላይ ለጣለችው ግብጽ መልካም ዜና ነበር።በ235 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ምርትና በ2440 ዶላር የነፍስ ወከፍ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ውስጥ ራሷን አስቀምጣለች።ወደእኛ ስንመጣ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ያልደረስን ራሳችንን በምግብ ለመቻል የምንደፋድ፣ የህዝብ ቁጥራችንን ከፍላጎት ጋር ለማጣጣት እየሰራን ያለን ባጠቃላይ ከድህነት ወጥተን ወደመካከለኛነ እንቅስቃሴ እያደረግን ያለን ህዝቦች ነው።አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርታችን 164 ቢሊዮን ገደማ ሲሰላ በነፍስ ወከፍ ደግሞ በ1500 ዶላር እንጠራለን፡፡

ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ድህነትና ኋላቀርነትን እንዲወክሉ የተቀመጡ ይመስል ለምንም ነገር ጣት የሚቀሰርባቸው ናቸው።ደግሞም እውነት ነው በአለም ላይ ሁሉንም አይነት ክፉ ነገር ያስተናገዱ ሀገራት ናቸው።ሀገራችን የዚህ አንዷ መሆኗ ጉዳዩን በአንክሮ እንድናነሳው ያስገድደናል።በታዳሽ ሀይልና በኤሌክትሪክ አቅርቦት ዙሪያ በአለም ባንክ መሪነት በተደረገ ግምገማ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት አናሳውን ኮታ መያዛቸው ተገልጿል፡፡

በታዳሽ ሀይል ሽፋን ከ15 በመቶ በታች ሲሸፍኑ እንደዋነኛ ምክንያት የተነሳው ድርቅና፣ የእርስ በርስ ግጭቶች፣ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ እንዲሁም በአንዳንድ ጣልቃ ገብ ሀገራት ተፈጥሮ ሀብታቸውን እንዳይጠቀሙ በሚደረግ ሴራ መሆኑ እንደምክንያት ተጠቅሷል።በአባይ ግድብ ዙሪያ ለዘመናት ንትርክ ውስጥ የገቡትና የሶስትዮሽ ስምምነቱ እንዳይሳካ እክል ሲፈጥሩ የነበሩ እንደግብጽና ሱዳን ያሉ ሀገራት በታዳሽ ሀይልም ሆነ በኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት የተሻለ ደረጃ ላይ መሆናቸው በግምገማው ተረጋግጧል፡፡

ለንጽጽር እንዲሆነን መመልከት ካለብን ኢትዮጵያ ሀገራችን 3.5፣ ሱዳን 41.3%፣ ግብጽ 97.6% የታዳሽ ሀይል ሽፋንን ይዘዋል።ይሄ ንጽጽር የአባይ ውሀ በግብጽ ላይ የነበረውን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጽዕኖ የሚያሳይ ነው።በኤሌክትሪክ አቅርቦትም ቢሆን ግብጽ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ህብረሰተሰቧን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ስታደርግ ሱዳን የ57 ከመቶ ተደራሽነትን ይዛለች።ወደሀገራችን ስንመጣ አሀዙ በአርባና በሀምሳ መሀል የሚገኝ ብዙሀኑን የማህበረሰብ ክፍል ያላዳረሰ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን እናገኛለን።በዚህ ዘመናዊ አለም ላይ ገጠር ያለች የኢትዮጵያ እናት በእሳት ጭስ የምትተዳደር ናት።ከተማ ላይም ያለው የሀይል መቅራረጥም ለዚህ አንዱ ምስክር ነው፡፤

ዓባይን ለልማት፣ ለሀይል፣ ለኢኮኖሚ ግንባታና ለስልጣኔ ለመጠቀም መነሳታችን በብዙ ምክንያት ቢሆንም የሀይል አቀርቦት የሚለው ግን ቀዳሚው ነው። ዓባይን አመንጭታ ወደግብጽና ሱዳን ወደተፋሰስ ሀገራቱ የምትልከው ሀገራችን በድህነትና በኋላቀርነት ከፍ ሲልም በኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት በዚህ ልክ መውረዷ ቁጭትን የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ ለምን የሚያስብልም ነው። ዓባይን የሚያክል በአፍሪካ ትልቁን ወንዝ ይዘን፣ በብዙ ሀይቆችና ወንዞች ተከበን በአፍሪካ የውሀ ማማ የሚል ስምን ይዘን መራብና መጠማታችን ሌላ ምርምር የሚያሻው ጉዳይ ቢሆንም ዓባይን በተመለከተ ያለን የባለቤትነት መብት ግን ከሌሎቹ ሀገራት የገዘፈ እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይችላል።

ኢትዮጵያ ሀገራችን በአመት ሁለት ጊዜ በሚከሰት ከፍተኛ ድርቅና በየእለቱ በሚጨምር የህዝብ ቁጥርና የፍላጎት መናር ውስጥ ናት።የታዳሽ ሀይል አሀዟንና የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦቷን ብንመለከት አሁን ላለው የህዝብ ቁጥርና ፍላጎት መጣጣም አይደለም መቀራረብ የማይችል ነው።ይሄን ችግር የምንቀርፍበት አንዱና ዋነኛው መንገድ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን ያለማንም ጣልቃገብነት በነጻነትና በፍትሀዊነት ስንጠቀም ነው።በብዙ ተግዳሮት ውስጥ አልፈን ታላቁን የህዳሴ ግድብ እውን አድርገናል።ሂደቱ ምን ያክል አሰልቺና አድካሚ እንደነበር፣ ምን ያክል የጦርነት ነጋሪት የተጎሰሙበት፣ ምን ያክል የአሉባልታና የዛቻ ሂደቶች እንደነበሩት የሚታወስ ነው፡፡

የሆነው ሆኖ ባይ ተገድቦ በትንሳኤው ማግስት ላይ ይገኛል።አጠቃላይ ሂደቱም 95 ከመቶ የደረሰ ሲሆን ሰባት ወራትን የሚሸፍን እስከሚቀጥለው አመት መጀመሪያ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተጠቁሟል።አንዳንድ ሂደቶቹ ቀድመው በመጠናቀቃቸው ተስፋችንን፣ ድካማችንን፣ መጠበቃችንን በብዙ ሙላት ሊክሱት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል።ቀንና ለሊት በሚሰሩ ብርቱ ሰራተኞች ከፍጻሜ የደረሰው ዓባይ ተስፋና ብርሀንን ይዞልን እየመጣ ነው፡፡

የግድቡ የሲቪል ስራ 99% ተጠናቋል፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካል የተርባይንና ጄኔሬተር ተከላ 78% ደርሷል፣ የግድቡ የውሀ ማስተላለፊያ አሸንዳ ከ85 ከመቶ በላይ መድረሱ አጠቃላይ የግድቡን ሂደት 95 ከመቶ አድርሶታል።ዋናው የግድቡ ክፍል 107 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የኮንክሬት ሙሌት እንደሚይዝ ተያይዞ የተነሳ ጉዳይ ነው።ግድቡ በቀን እስከ 6 ሺህ ሜጋ ዋት ሲያመነጭ፣ በአመት 15 ሺህ 130 ጊጋ ዋት ሀይል ሲያመነጭ የሚመጣው ለውጥ እንደሀገር የማደግ ጥያቄአችንን ከመመለሱ ጎን ለጎን ለተራመድንው ረጅም የድካም ጉዞ ካሳ የሚሆንም ነው፡፡

አባይ መነሻው ከትራስጌአችን ሆኖ 86 ከመቶ ያህሉን እያዋጣን፣ በተፈጥሮ ሀብታችን ላይ እንዳንጠቀም፣ ጭራሽ የማይመለከታቸው ሀገራት ሲያዙንና ሲፈቅዱልን ብቻ እንድንጠቀም የነበረው ሁኔታ ተቀይሮ በራሳችን ከራሳችን ለራሳችን በሆነ ህዝባዊ መርህ በአዲስ ተሀድሶ ስር እንገኛለን።ሁሉን ትተን የህልውና ጉዳይ ከሆነው ከዚህ እውነታ ብንነሳ እንኳን አባይን በፍትሀዊነት ለመጠቀም ሙሉ መብት እንዳለን መረዳት ይቻላል፡፡

ይሄ አይነቱ ሁኔታ አሁን ያለውን መንግስትና ህዝብ ትውልዱ ላይም ቅሬታ በመፍጠር ካለማንም እርዳታ በራስ ገንዘብ፣ በራስ እውቀት፣ በራስ ጉልበት አይችሉም በተባለ በብዙሀን ጩኸት እና ስላቅ ውስጥ አባይን ገድበናል።በብዙ አይችሉም ውስጥ አባይን ለዚህ ደረጃ ማድረስ አድዋ ለራቀበትና ታሪክ መበርበር ለማይወዱ ነጪች የመቻላችን እና የጽናታችን ማሳያ ሆኗል፡፡

አባይ ለዚህ ትውልድ ምኑ ነው? በሚል እጅግ በጠለቀ ሀሳብና ንቃት ውስጥ ነኝ።አባይ ለዚህ ትውልድ መልኩ ነው።ከሌለው ላይ ቆርሶ፣ በትጋትና በጽናት የቆመው የህብረብሄራዊነት ሀውልቱ ነው።ካለልዩነት ስለአንድነት በፈሰሰ ላብ፣ በተዋጣ ገንዘብ፣ በታሰበ ሀሳብ፣ በተቆመ ጽናት የጸና የተጋድሎ ሰነድ ነው።ዳር በሌለው፣ ድንበር አልባ ፍቅርና ኢትዮጵያዊነት መሀል የቆመ የመቶ ሀያ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ሰንደቅ ነው፡፡

ዓባይ ብለን ዓድዋ፣ ዓድዋ ብለን አባይ ማለት የማንችልበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል።ሁለቱም ኢትዮጵያዊነትን ያደመቁ የዛኛውና የዚህኛው ዘመን ድልብ ታሪኮች ናቸው።አባይ ከግድብ ባለፈ እችላለሁ ብሎ ለተነሳ ሀገርና ህዝብ የማይቻል ነገር እንደሌለ ማሳያም ጭምር ነው።በምድር ላይ ያሉ ታላላቅ ቁምነገሮች ላመል በሚመስል ግን ደግሞ ባይደለ የእችላለሁ መንፈስ ተጀምረው ያለቁ ናቸው።በአባይ ላይ እንችላለን ብለን ስንነሳ ይችላሉ ያለን ማን ነበር? የአባይና የኢትዮጵያውያን ቁርኝት ከታሪክነት ባለፈ የታላቅ ስነልቦና መገንቢያና ማስተማሪም ጭምር የሚሆን ነው፡፡

ሌላው ዓባይን ሳስብ የተገለጠልኝ እውነታ የሚከተለው ነው..አባይ ለእኛ ግድብ ብቻ ሳይሆን መለያየታችንን ሊሽር በመካከላችን ለእርቅ የገባ ሽማግሌ ነው የሚመስለኝ።በብዙ ነገር ተለያይተን በዓባይ ጉዳይ ላይ አንድ ሆነን ከአስር አመታት ለዘለጉ ጊዜአቶች አብረን ተጉዘናል።ተኮራርፈን ያስታረቀን፣ ተራርቀን ያጠጋጋን የአንድነትና የወንድማማችነት ምልክትም ነው እላለው።በአባቶቻችን ልብ ውስጥ የነበረ ባለ ብዙ ውበት፣ ባለ ብዙ ቁንጅና አባይ ለዚህኛው ትውልድ ታሪክና ገድል ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡

አባይ ውሀ ብቻ አይደለም ከልባችን የሚፈልቅ የቁጭት እንባም ነው።አባይ እያንዳንዳችንን ነው።ለዘመናት ከደጃችን እየፈለቀ የእትብቱ ማደሪያ የሆነውን ቀዬ ግን ውሀ እያስጠማ ባዕድ ሀገራትን ሲያረሰርስ ነበር።የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና እያልን በዜማና ግጥም በወቀሳና በሙገሳ አዚመንለታል።ያ ሁሉ አልፎ ዛሬ ላይ እንደተመኘንው ብርሀን ሊሆነን፣ ከድህነት ሊያወጣን እንሆ ክብርን አለን፡፡

በአንድ ልብ፣ በአንድ ሀሳብ ስለ ዓባይ እያዜምን አስራ ሶስት አመታትን ተጉዘናል።ከመጣንበት ይልቅ የምንሄድበት ቅርብ ነውና ከእንግዲህም ለሚገጥሙን ማናችውም ችግሮች እጅ መስጠት የማይታሰብ ነው።ዓባይ ለዚህ ክብር የበቃው በአንድነት ስም ነው።አንድነትና ወንድማማችነት ምን ያክል ሀይል እንዳለው በተለያዩ ጊዜአቶች ለማስተዋል ችለናል።እንደሀገር የተደቀኑብንን ችግሮች ዓባይን ባጸና፣ ዓድዋን ባቀና ኢትዮጵያዊነት ካልሆነ በምንም አንፈታቸውም።ችግሮቻችን እዛና እዚህ በቆም ሳይሆን በመጠጋጋት፣ በመነካካት በመተቃቀፍ የሚስተካከሉ ናቸው።

የታሪኮቻችን ደማቅ ጸዳሎች በጋራ ሸራ በጋራ ብሩሽ የተሳሉ እንደሆኑ እየገባን ለመለያየት መንገድ መክፈታችን፣ ለማይጠቅሙን ነገሮች ዋጋ መክፈላችን ያሳዝናል።ከፊት ለፊታችን የተጎለተው ዓባይ በተጣመሩ እጆች፣ በተጉ ልቦች ክብር እንዳገኘ እያወቅን እንኳን ችግሮቻችንን ለውይይት ለመፍታት ስንተጋ አንታይም።ዓባይ ብቻውን ውርስና ቅርስ አይሆነንም።በዓባይ ላይ ያሳየንው አንድነት ዋጋ የሚኖረው አንድነታችን በቀጣይ ዋስትና ሲኖረው ነው። በአንድነት ዓባይን እንዳጸናን ቀጣይ ጉዟችን በፍቅር ቤትታችንን በመስራት ነው !፡፡

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You