በኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚካሄደው የሠራተኞች የበጋ ወራት የስፖርት ውድድር ዘንድሮ ከጥር 19/2016 ጀምሮ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በተደረገ የመክፈቻ ሥነሥርዓት መጀመሩ ይታወቃል፡፡ በጠንካራ ፉክክርም ቀጥሏል።
በአስር የስፖርት አይነቶች ከሰላሳ በላይ የሠራተኛ ስፖርት ማህበራትን እያፎካከረ የሚገኘው ይህ ውድድር ለስድስት ወራት ያህል የሚቆይ ሲሆን፤ ባለፉት ሳምንታት ጠንካራ ፉክክሮች ሲደረጉበት ቆይተል፡፡
ዘወትር በእረፍት ቀናት ቅዳሜና እሁድ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች በበርካታ የማዘውተሪያ ስፍራዎች የሚካሄደው የሠራተኞች የበጋ ወራት ውድድር ባለፈው ሳምንት መርሀ ግብሩ ጠንካራ ፉክክር እያስተናገደ መቀጠሉን የኢሰማኮ የስፖርት ክፍል ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ካሳ ተናግረዋል፡፡
በሠራተኛው ስፖርት አጓጊ ፉክክር ከሚደረግባቸው ስፖርቶች አንዱ የሆነው በወንዶች እግር ኳስ ባለፈው ሳምንት ስድስት ጨዋታዎች ተካሂደዋል፡፡ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ሰፊ በሆነ የ7ለ1 ውጤት የረታበት ጨዋታ አንዱ ሲሆን፤ መከላከያ ኮንስትራክሽን ሙገር ሲሚንቶን 5ለ1 ያሸነፈበት ጨዋታም በርካታ ግቦች የተመዘገቡበት የሳምንቱ መርሀ ግብር ነበር፡፡ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ከ ሞዔንኮ ኩባንያ ያደረጉት ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር በማስተናገድ ሰባት ግቦች ከመረብ ያረፉበት ሲሆን፤ባህር ትራንስፖርት 4ለ3 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችላል፡፡
ኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ከ ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ያደረጉት ጨዋታም ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበትና 2ለ2 በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ ደግሞ ኢትዮ ቴሌኮምን 4ለ1 ማሸነፍ ችሏል፡፡
በሠራተኛው ውድድር እንደ እግር ኳሱ ሁሉ ጥሩ ፉክክርና ጨዋታ የሚታይበት የቮሊቦል ውድድርም በሳምንቱ መርሀ ግብር በወንዶች ሁለት ጨዋታ አስተናግዷል፡፡ በዚህም አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ሙገር ሲሚንቶን 3ለ0 ሲያሸንፍ፤ አዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎችን 3ለ1 መርታት ችሏል፡፡ በሳምንቱ በቤት ውስጥ ውድድሮች ከተከናወኑ ፉክክሮች አንዱ በሆነው የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር በወንዶች ሦስት ጨዋታዎች ተካሂደዋል፡፡ ብራና ማተሚያ አዲስ አበባ አውቶቡስን 3ለ0 በሆነ የፎርፌ ውጤት አሸናፊ የሆነበትን ነጥብ ሲያገኝ፤ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 3ለ0 አሸንፏል፡፡
ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎችና የሞዔንኮ ጨዋታ በግብርና ሥራዎች 3ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ በተመሳሳይ ስፖርት በሴቶች መካከል በተካሄደው ብቸኛ ጨዋታም ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎችን 3ለ2 ያሸነፈበት ውጤት ተመዝግቧል፡፡
በሴቶች የዳርት ውድድር ኢትዮ ቴሌኮም ኢትዮጵያ ልማት ባንክን 2ለ0፣ ጂኦ ሴንቴቲክ ኢንዱስትሪያል አዲስ አበባ አውቶቡስን 2ለ1 ሲያሸንፉ በወንዶች ተመሳሳይ ውድድር አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካን በተመሳሳይ 2ለ1 ማሸነፍ ችሏል፡፡
በአዝናኝ ፉክክርና ትዕይንቶች የሚደምቀው የሠራተኛ የበጋ ወራት ውድድር ነገና ከነገ በስቲያ በሚከናወኑ የተለያዩ ውድድሮች የሚቀጥል ሲሆን፣ በሴቶች ቮሊቦል ኢትዮ ቴሌኮም ከመከላከያ ኮንስትራክሽን ነገ በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡ በተመሳሳይ ቦታ ኢትዮ ቴሌኮም በወንዶች ቮሊቦል ቃሊቲ ብረታብረትን ሲገጥም፤ ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ከፋፋ ምግብ ጋር ይጫወታል፡፡
ነገ ሜክሲኮ በሚገኘው የመብራት ኃይል ክበብ የሚካሄዱ አራት የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድሮችም ተጠባቂ ናቸው፡፡ በሴቶች አዲስ አበባ አውቶቡስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲገናኙ፣ በወንዶች ሞኤንኮ ከብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ፣ ኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ከፋፋ ምግብ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአዲስ አበባ አውቶቡስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡ ነገ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በሚካሄደው የከረንቦላ ውድድርም ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡
በሠራተኛው ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው የእግር ኳስ ውድድር ከነገ በስቲያ ሲደረግ በአንደኛ ዲቪዚዮን ሦስት ጨዋታዎች ተጠባቂ ናቸው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ከዮሐንስ ቢፍ፣ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያደርጉት ጨዋታ ከጠዋቱ 3፡00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ይካሄዳል፡፡ በተመሳሳይ ዲቪዚዮን አዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስን ከኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች የሚያገናኘው አንድ ጨዋታ ደግሞ በጎፋ ካፕ ይከናወናል፡፡ በተመሳሳይ ሜዳ በሁለተኛ ዲቪዚዮን አዋሽ ወይን ፋብሪካ ከፍል ውሃ አገልግሎት የሚያደርጉት ጨዋታም ይጠበቃል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም