የስልጤ ብሔረሰብ ባሕላዊ ምግቦች

በሀገራችን በተለያዩ ብሔረሰቦች ዘንድ የሚዘጋጁ ይዘታቸው በፕሮቲን የበለፀጉ ባሕላዊ ምግቦች አሉ። እነዚህ ምግቦች በመደበኛነት (ለእለት ተእለት) እና በልዩ ቀናቶች (በበዓላት፣ በደስታና በሀዘን) የሚዘጋጁ ናቸው። ይሁን እንጂ እነዚህ የምግብ ዓይነቶች በሌላው ብሔረሰብ ባሕላዊ አዘገጃጀት ወቅት በተመሳሳይ የሚገኝበት ሁኔታም በስፋት ይስተዋላል፡፡ ምግቦቹ የብሔረሰቦች ማንነት መገለጫም ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ባሕላዊ ምግቦች በሚገባ የተጠኑና አዘገጃጀታቸውም ተሰንዶ የተቀመጠ እንዳልሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በዚህ ምክንያት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉት ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾላቸው ትውልዱ እንዲያውቃቸውና እንዲማራቸው በማድረግ ሳይሆን በልማድ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እነዚህን ሀገራዊ የሆኑ ባሕላዊ ምግቦችን በማጥነት በመደበኛው የአመጋገብ ሥርዓት የማካተት እና ሌሎች ማህበረሰቦችም የማስተዋወቅ እንዲሁም ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ የሚገቡበትን ሁኔታ የማመቻቸት እንቅስቃሴዎች ይታያሉ።

ከዚህ አኳያ አንዱ ሊጠቀስ የሚገባው የስልጤ ብሔረሰብ ባሕላዊ ምግቦች፣ አዘገጃጀታቸውና የአመጋገብ ሥርዓታቸው ነው። ብሔረሰቡ በርካታ የራሱ የሆኑ መገለጫዎች ያሉት ሲሆን፣ ከእነዚህ መገለጫዎቹ መካከል ባሕላዊ ምግቦቹ ይጠቀሳሉ፡፡

ከስልጤ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መመሪያ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ብሔረሰቡ ከ135 በላይ የምግብና የመጠጥ ዓይነቶች አሉት። መረጃው እንደሚያመለክተው ምግቦቹና መጠጦቹ በሁለት ዘርፍ መድቦ መደበኛና መደበኛ ያልሆኑ ብሎ መመልከት ይቻላል፡፡

መደበኛ ምግቦችና መጠጦች ማለት ዘወትር ጥቅም ላይ የሚውሉትን የሚያቅፍ ነው። ይህም እንደ ቆጮ፣ ቡና፣ ቆሎ፣ ካሽትዬ የመሳሰሉትን ያካትታል። መደበኛ ያልሆኑ ምግቦች የሚባሉት ደግሞ በተለያዩ ሁኔታዎችና ክስተቶች እንዲሁም ወቅቶች ላይ የሚዘጋጁ ምግቦችን ይመለከታል። በዚህ ዘርፍ እንደ አተካኖ፣ ብላንብሎ፣ ሻሜታ፣ ዙብቆ የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡

ሀገር በቀል ባህላዊ ምግቦችን በመጠበቅ በሀገሪቱ የአመጋገብ ሥርዓት በማካተት ሂደት ሚናውን እየተወጣ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት፣ የሀገሪቱ ብሔረሰቦች መገለጫዎች የሆኑትን ባሕላዊ ምግቦችና የአመጋገብ እሴቶችን ጨምሮ የተለያዩ ጥናቶችን እያደረገ ይገኛል።

ኢንስቲትዩቱ መሰል ጥናቶችን ካደረገ በኋላም ሰነዱን ለዩኒቨርሲቲዎች፣ ለጤና ተቋማት፣ ለግብርና ቢሮዎችና ሌሎች ለሚመለከተው አካላት ያስረክባል። በቅርቡም ከስልጤ ዞን ባህልና ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ጋር በመሆን የተለያዩ ብሔረሰቦች ባሕሎች እንዲሁም የቱሪዝም መስህብ ቦታዎች እና ባሕላዊ ምግቦች ላይ ጥናት አድርጎ ለስልጤ ዞን አስተዳደር አስርክቧል።

የኢንስቲትዩቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር ተክሌ እንደሚናገሩት፤ ኢንስቲትዩቱ ከተሰጡት ተልዕኮዎች ጥናትና ምርምር ማድረግ፣ ሥልጠና መስጠት እና ማማከር የሚሉት ይጠቀሳሉ። በዚህም ከክልሎች ጋር በመሆን በባህላዊ የአመጋገብ ሥርዓቶች ላይ ያተኮሩ ጥናቶችን በማድረግ የምግቦቹን ዝርዝርና አዘገጃጀታቸው በምግብ ዝርዝር እንዲካተት እያደረገ ነው።

ኢትዮጵያ የምትታወቅባቸው ባሕላዊ የአመጋገብ ሥርዓቶቿ እንዳሉ ሆነው በየክልሎቹ በሚገኙ ብሔረሰቦች ዘንድም በርካታ ባሕላዊ የምግብ ዓይነቶች፣ አዘጋጃጀቶችና ሥርዓቶች ይገኛሉ። ከተማ ላይ የማይገኙ የምግብ ዓይነቶችንም በባለሙያ በማጥናት በምግብ ዝርዝር መቅረብ እንዲችሉ እየተደረገ መሆኑን ወይዘሮ አስቴር ተናግረዋል። ቀደም ሲልም 16 የሲዳማ ባህላዊ የምግብ ዓይነቶች በምግብ ዝርዝር ውስጥ እንዲቀርቡ በኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች ጥናት መደረጉንም ጠቅሰዋል።

ኢንስቲትዩቱ አሁን ያደረገው ጥናትም በስልጤ እና በሌሎች ብሔረሰቦችም ዘንድ በተወዳጅነቱ የሚታወቀውን “አተካኖ” የሚባለውን ከእንሰት የሚዘጋጅ ባህላዊ ምግብ በዞኑ ባሉ ደረጃቸውን በጠበቁ ሆቴሎች እና በሀገራችን በሚገኙ ሌሎች ሆቴሎች ጭምር አዘጋጅቶ ለማቅረብ የሚያግዝ ነው።

ምግቡ በማዘጋጀት በኩል እውቀቱ ያላቸው እናቶች በባሕላዊ መንገድ ሲያዘጋጁ ኢንስቲትዩቱም በዘመናዊ መንገድ በመመዘን እና በመለካት ምግቡን ማዘጋጀት የሚቻልበትን መንገድ በማሳየት ሰርቶ እያስረከበ ነው። ኢንስቲትዩቱ በስልጤ ማህበረሰብ ዘንድ በዋናነት ከሚታወቁ የምግብ ዓይነቶች መካከል አንዱ የሆነውን “አተካኖ”ን ጨምሮ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን በማጥናት ለምግብ ‹‹ሜኖ›› ለማቅረብ በሚመች መልኩ ሰርቶ በቅርቡ ወራቤ ከተማ ላይ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ላይ አስረክቧል።

ኢንስቲትዩቱ እነዚህን እና ሌሎች ባህላዊ ሁኔታዎችን በማጥናት ለቱሪስት መስህብ እንዲሆኑ አቅም መፍጠር ላይ ይሰራል። እቅም እንዲፈጠር ደግሞ በመረጃ የተደገፈ ጥናት ስለሚያስፈልግ ይሄንን እየሠራ መሆኑን ወይዘሮ አስቴር አመላከተዋል።

የጥናት ሰነዱን በመጠቀምም ህብረተሰቡ የአመጋገብ ባህሉን እንዲያስተዋውቅ እድል እንደሚሰጥ አስታውቀው፣ ክልሎችም የራሳቸውን እምቅ ሀብት ለማስተዋወቅ እድል ከማግኘታቸውም በላይ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውንም የሚያሳደ ጉበት መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ጁኒየር አሰልጣኝ አቶ ጌታሁን ደሳለኝ እንዳብራሩት፤ ሀገር በቀል የሆኑ የኢትዮጵያ ባሕላዊ የአመጋገብ ሥርዓቶችን በማጥናት ወደ ሰነድ የመቀየር ሥራዎች ይሰራሉ። በባህላዊ የምግብ ዝግጅቶችም ላይ ሰነድ በማዘጋጀት ለትውልድ እንዲተላለፉ ይደረጋሉ። በመቀጠልም በትምህርት ቤቶች በትምህርት አይነትነት እንዲሰጡ የሚያስችል ሥርዓተ ትምህርት ለማዘጋጀትም መረጃዎቹ ግብዓት ይሆናሉ። ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ የራሷ የሆኑ በርካታ ምግቦች ያሏት በመሆኑ እነዚህ ዝርዝር ላይ ሰፍረው በቀላሉ ወደ ገበያ ለማቅረብ እንደሚሰራ አመላክተዋል።

በጥናቱ መሠረት ዶክመንት ከተዘጋጀላቸው ባህላዊ ምግቦች መካከል የሆነው የስልጤ ባህላዊ አመጋገብ ሥርዓት እና የምግብ ዓይነቶች ወደ 26 ይደርሳሉ። ከነዚህም መካከል አተካኖ፣ ሱልሶ፣ ሎሎሃድ፣ ፊንታፊንቶ ወይም ጨራጨራ፣ ኪልፋን፣ ጎሳ ጎሳ፣ የቆሊ ወይም ያቆቀሲ በሰር፣ የዳፓ ፊናንቾ የሚሉት ይገኙበታል። የዝግጅት ክፍላችን ከብሔረሰቡ ባህላዊ ምግቦች መካከል ጥቂቱን እንደሚከተለው በርዝር ይቃኛቸዋል፡፡

አተካኖ፦ ይህ የምግብ ዓይነት ከእንሰት የሚዘጋጅ ባሕላዊ ምግብ ሲሆን፣ በበዓላት ወቅት ከሚቀርቡት ምግቦች አንዱ መሠረታዊው ነው። በባሕላዊ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ወቅት በሚኖሩ የተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ላይ የሚቀርብ ሲሆን፣ በማንኛውም ወቅት ክብር የሚሰጣቸውን እንግዶች ለመቀበል ይቀርባል፡፡

አተካኖ ቀለል ያሉ ተብለው ከሚታወቁት የምግብ ዓይነቶች ሊመደብ ይችላል። ይህ ባህላዊ የምግብ ዓይነት ያለማባያ ሊበሉ ከሚችሉ ምግቦች መካከልም ይካተታል። በአመጋገብ ወቅትም የአፍ እንቅስቃሴን እምብዛም የማይፈልግና እንደ ገንፎ በቀላሉ ተላምጦ ሊዋጥ ይችላል። ሲዘጋጅም በዋናነት ቡላ፣ አይብ ፣ ቅቤ፣ ሚጥሚጣና ጨው በግብዓትነት በመጠቀም ነው። ከአዘገጃጀት ሂደት ቀላልነት ባሻገር አተካኖ በቀላሉ የሚበላና የሚፈጭ እንዲሁም ጤናማ የሆነ ሰውነት እንዲኖር ለማድረግ ጠቃሜታ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡

አሠራሩም፤ በቡላው ውስጡ የሚገኘውን እርጥበት እንዲያደርቅና የቡላው ጣዕም ከጥሬነት ወደ በሳልነት እንዲለወጥ እና የበለጠ እንዲፈረፈር ጥሬ ቡላውን በሰፊ ምጣድ ላይ መቁላት የመጀመሪያ ሥራው ይሆናል። በመቀጠልም የተፈረፈረውን ቡላ በተለምዶ ሳይራ ተብሎ በሚጠራ ሰፊ እቃ ላይ እንዲሰባሰብ ይደረጋል፤ ውሃ በላዩ ላይ በማርከፍከፍ ውሃውን ሲመጥ ጨው፣ ኮረሪማ፣ ቅቤ፣ አይብ፣ ሚጥሚጣ በመጨመር በደንብ ይፈረፈራል።

በመጨረሻም አይብ ተደርጎበት ከለሰለሰ በኋላ የመሃሉን ቦታ በደንብ በማጎድጎድ በቦታው ላይ በሥነ- ሥርዓት ተነጥሮ የተዘጋጀ ቅቤ በመጨመር ይዘጋጃል። ይህ ባሕላዊ ምግብ በትኩሱ የሚቀርብ ሲሆን፣ አካልን ለማዳበር እና የተጎዳ አካልን ለመጠገን እንደሚጠቅም ይገለጻል።

በአብዛኛው የሚዘጋጀው እንደ አረፋ በዓል፣ ሠርግ ባሉት ዝግጅቶች ላይ ነው፡፡ ከጨቅላ ሕፃናት በስተቀር ሁሉም ሰው የሚመገበው የስልጤ ባህላዊ ምግብ ሲሆን፣ ለጨቅላ ሕፃናት የማይሰጠው ምግቡን መፍጨት የሚችል አቅም እንደሌላቸው በማመን ነው።

ሱልሶ፦ ይህ ባሕላዊ የስልጤ ምግብ በትኩሱ የሚቀርብ ሲሆን፣ ይህ የምግብ ዓይነት አካልን ለማዳበር እና የተጎዳ አካል እንዲጠግን ጠቀሜታ እንዳለው በስልጤ ብሔረሰብ ዘንድ ይታመናል። የአረፋ በዓልን፣ የሠርግ ድግስን ምክንያት በማድረግ ይቀርባል። ጨቅላ ሕፃናት በስተቀር ሁሉም ሰው የሚመገበው የስልጤ ባሕላዊ የምግብ ነው።

ሎሎሃድ፦ ሰውነትን የሚጠግን የስልጤ ባሕላዊ ምግብ ሲሆን፣ ይህ የምግብ ዓይነትም ብዙ ጊዜ የሚዘጋጀው የአረፋ በዓልን ፣ የሠርግ ድግስን ምክንያት በማድረግ ነው። ከጨቅላ ሕፃናት በስተቀር ለሁሉም ሰው ይቀርባል። ለጨቅላ ሕፃናት የማይሰጠው ምግቡን መፍጨት የሚችል አቅም እንደሌላቸው በማመን ነው።

ፊንታፊንቶ ወይም ጨራጨራ፦ ይህ የምግብ ዓይነት ከሱልሶ፣ ጉመረ ቄሰ፣ አዝማሞጃት ወይም ጎመን እርስ በርስ ሳይቀላቀሉ ለየብቻ ረግተው የሚቀርቡበት ነው፡፡ በአረፋ በዓል፣ በሠርግ ጊዜ ይቀርባል። ይህም ምግብ ከጨቅላ ሕፃናት በስተቀር በሁሉም ሰው ለምግብነት ይውላል፡፡

ኪልፋን፦ በምግቡ ውስጥ ከንጥረ ምግቦች አኳያ ፕሮቲን፣ ቅባቶችና ማዕድናት ይገኙበታል። በመሆኑም አካልን ያዳብራል፣ የተጎዳ አካልን ይጠግናል። የሚዘጋጀውም የአረፋ በዓልን፣ የሠርግ ድግስን ምክንያት በማድረግ ነው። በሁለት ዓይነት መንገድ ይዘጋጃል፡፡ ከሥጋ እና ከጎመን በቅቤ ተለውሶ በቅጠል እየተደረገ በእጅ ይሰጣል።

ጎሳ ጎሳ፦ ከተለያዩ የምግብ ዓይነቶች ምግቦች ማለትም ቡላ፣ ቅንጬ፣ ጎመን፣ ሱልሶ፣ አይብ፣ ምስር፣ የአተር ክክ የሚቀርብ ነው፤ ጎሳጎሰ ብዙ ጊዜ በአመትባል እና በሠርግ ጊዜ በሸክላ ለተመጋቢዎች ቀርቦ በባሕላዊ ማንኪያ ወይም ቀርሼ ይበላል።

የቆሊ /ያቆቀሲ በሰር፦ አካልን የሚጠግን የስልጤ ባሕላዊ ምግብ ነው። ለተከበሩ ሰዎች ማለትም ለአማች፣ ቤተዘመድ አባላት እና ለሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓል ማለትም ለረመዳን ጾም ፍች ፣ ለሸዋል ጾም ፍች፣ በመውሊድ፣ በዱአ ቦታ ላይ ይቀርባል። ጨቅላ ሕፃናት ሲቀሩ ሁሉም ሰው የሚመገበው የምግብ ዓይነት ነው። ለጨቅላ ሕፃናት የማይሰጠው ምግቡን መፍጨት የሚችል አቅም እንደሌላቸው በማመን ነው።

የጄሪ አንገብሶ/ ቅቅል ፍሪምባ፦ ይህ የክብር ምግብ ማህበራዊ ትስስርን ለመፍጠር ከቤተዘመድ እና ጎረቤት ጋር በአንድ ላይ በመሆን በሽማግሌዎች ወይም በሃይማኖት አባቶች ተባርኮ ለቡና ሥነ-ሥርዓት በተሰበሰቡ ሰዎች ለምግብነት ይውላል። ለአማች፣ ለረመዳን ጾም ፍች ፣ ለሸዋል ጾም ፍች፣ በእርድ ቦታ ላይ የሚዘጋጅ፣ በመውሊድ፣ በዱአ ቦታ በተገኘ ጊዜ ሁሉ ፣ በአረፋ በዓል ሰሞን፣ በጾም ፍች ሰሞን፣ በመውሊድ የሚዘጋጅ ሲሆን፣ ሁሉም ሰው የሚመገበው የስልጤ ባሕላዊ የምግብ ዓይነት ነው።

የጄሪ ፎለ /ቅቅል ሻኛ ከነ ሳልገኝ፦ ይህ የምግብ ዓይነትም የክብር ምግብ ተብሎ ይታወቃል፡፡ ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክር ነው ይባላል። በጦርነት ወቅት ጀብድ ለፈጸሙ የጦር አበጋዞች፣ በታላልቅ ሰዎች ተባርኮ ይሰጣል። ይህ ምግብ ለጦር አበጋዞች ወይም ጀብዱ ለፈጸሙ የሚቀርብ ቢሆንም፣ ሁልጊዜ በታላላቅ ሰዎች ወይም የሃይማኖት አባቶች ተባርኮ የጦር ጀብዱ የፈጸሙትን በማስቀደም በረመዳን ጾም ፍች እና በሸዋል ጾም ፍች ጊዜ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ጎረቤትና ቤተዘመድን ጨምሮ እንደየደረጃቸው ተካፋፍሎ የሚሰጥ የስልጤ ባሕላዊ የምግብ ዓይነት ነው።

ዪንጫቆ ጉገ/በቅቤ የተለወሰ የዶሮ ቅቅል፦ ለረመዳንና ለሸዋል ኢዶች አንዳንዴም መድኃኒት ለሚጠቀሙ ሰዎች እንዳይጎዱ ተብሎ፣ ይጠግናቸዋል በሚል ታስቦ የሚዘጋጅ ምግብ ነው ። በምግቡ ውስጥ ከንጥረ ምግቦች አኳያ ፕሮቲን፣ ቅባቶችና ማዕድናትን ይገኛሉ። ይህ በመሆኑም አካልን ያዳብራል፣ የተጎዳ አካልን ይጠግናል። የሚዘጋጀውም ለአማች፣ ቤተዘመድ፣ ለረመዳን ጾም ፍች ፣ ለሸዋል ጾም ፍች ነው፤ በእርድ ቦታ ላይም ይዘጋጃል፣ ስብራት የገጠመው ሰው ሲኖር፣ መድኃኒት የሚወስዱ ሲኖሩ ይዘጋጃል። ሁሉም ሰው የሚመገበው የስልጤ ባሕላዊ የምግብ ዓይነት ነው።

የማህበረሰቡ ባሕላዊ መጠጦች፦ የስልጤ ማህበረሰብ ባሕላዊ መጠጦች ከሆኑት መካከል “ኡቡሽቡሽት” የሚባለው ይገኝበታል። ኡቡሽቡሽቱ የስልጤ የባሕል መጠጥ ሲሆን፣ በጾም ጊዜ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ሻሜት ሌላው የስልጤ የባሕል መጠጥ ሲሆን፣ በሠርግ ጊዜ፣ በደቦ ሥራ፣ ቤት ሥራ፣ እርሻ ሥራ፣ እንሰት ተከላ፣ አጨዳ፣ አውድማ እና የመሳሰሉት የህብረት ሥራዎች ሲኖሩ ሠራተኛውን ለማጠናከር የሚቀርብ መሆኑን የጥናት ሰነዱ አመላክቷል።

የስልጤ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ መረጃ እንዳመለከተው፤ በስልጤ ማህበረሰብ ዘንድ የተለዩና በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ አገልግሎት ላይ የሚውሉ ከ135 በላይ የምግብ ዓይነቶች ይገኛሉ። ከእነዚህ ምግቦች ውስጥ 18ቱ የምግብ ዓይነቶች በስልጤ ማህበረሰብ ዘንድ ብቻ የተለመዱና የሚዘወተሩ ናቸው። በስልጤ ማህበረሰብ ውስጥ ብቻ ከሚታወቁት የምግብ ዓይነቶች ውስጥ አተካኖን ጨምሮ ቢያንስ ሁለትና ከዚያ በላይ የምግብ ዓይነቶች በሚገባ ታውቀውና ተለምደው በሀገሪቱ በሚገኙ ዋና ዋና ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ውስጥ እንዲሁም በሁሉም የምግብ መገበያያ ሥፍራዎች በሚቀርቡ የዘወትር ምግብ ዝርዝሮች እንዲካተቱ እየተሠራ ነው።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You