አዲስ አበባ፡- በሰኔ ወር በአብዛኛዉ የአገሪቱ ክፍል መደበኛና ከመደበኛ በላይ የክረምት ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የኢ ትዮጵያ ብሄራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
ኤጀንሲው በላከው መግለጫ እንዳመ ለከተው፤ በሰኔ ወር የክረምት ዝናብ ቀደም ብሎ በምዕራብ አጋማሽ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚጀምር ሲሆን፤ የተቀሩት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ስርጭቱ እየሰፋ እንደሚሄድ የሚቲዎሮሎጂ ትንበያዎች ያሳያሉ፡፡
በሰኔ ወርም ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ፣ አርሲና ባሌ ዞኖች፣ አዲስ አበባ፣ ከአማራ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም፣ አዊ ዞን፣ የሰሜንና የደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ የባህርዳር ዙሪያ፣ ከትግራይ ክልል የምዕራብና የመካከለኛው ዞኖች፤ የጋንቤላና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ዞኖች፤ እንዲሁም የደቡብ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ክልል አብዛኛዎቹ ቦታዎቻቸው ላይም ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ ዝናብ ያገኛሉ ያለው መግለጫው፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይም ከመደበኛው በላይ ዝናብ ይኖራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል።
በአንጻሩ ከኦሮሚያ ክልል የቦረናና ጉጂ፤ ከአማራ ክልል የደቡብና ሰሜን ወሎ፤ እንዲሁም ዋግ ህምራ ከአፋር ክልል ዞን 3ና 5፤ ከሶማሌ ክልል የጅግጅጋ እና የሲቲ ዞኖች በአንዳንድ ቦታዎቻቸው ላይ ዝናብ እንደሚያገኙ የሚጠበቅ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የተቀሩት የአገሪቱ ዞኖች ግን ደረቅ ሆነው ይሰነብታሉ ብሏል ትንበያው፡፡
የክረምት ዝናብ ከምዕራብ አጋማሽ የአገሪቱ አካባቢዎች ጀምሮ ወደ ሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚስፋፋ በመሆኑ ለግብርና እንቅስቃሴ ምቹ እንደሚሆን መግለጫው ጠቁሞ፤ ለማሳ ዝግጅትና ለዘር መዝራት ተግባራት ውጤታማነት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጿል፡፡
በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሚኖረው ከባድ ዝናብ የጎርፍ ተጋላጭነት፣ የአፈር መሸርሸርና የመሬት መንሸራተት ሊያስከትል ስለሚችል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ኤጀንሲው በመግለጫው አስጠንቅቋል፡፡
በመጠን ዝቅተኛ ቢሆንም በተለያዩ የሰሜን ምስራቅና የምስራቅ የአርብቶ አደር አካባቢዎች በወሩ ከሚጠበቀው እርጥበት ተጠቃሚ እንደሚሆኑና የመጠጥ ውሃና የግጦሽ ሳር አቅርቦታቸው በተወሰነ መልኩ እንደሚሻሻልም ተመልክቷል፡፡
ባለፉት 11 ቀናት የዘነበው የዝናብ መጠን ከመደበኛው ጋር ሲነጻጸር ከቆራሄና ዋርዴር፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዞኖችና ከአፋር ክልል ዞን 1 እና 2 በስተቀር በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠን እንደነበራቸው ማወቅ ተችሏል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2011
ጌትነት ምህረቴ