ቤተ- መጻሕፍትን ለማህበረሰብ መገናኛ

ድሮ ድሮ እንዲህ ቴክኖሎጂው እንደልብ ሳይስፋፋ በኢትዮጵያ አብዛኛዎቹ የሥነ ጽሑፍ ውጤቶች ለተደራሲያን የሚቀርቡት በጋዜጣ፣ በመጽሔትና በመጻሕፍት በኩል ነበር። ምን እንኳን ያኔ የነበረው የሕዝብ ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም ከነዚህ የሥነ ጽሑፍ ውጤቶች ተቋዳሽ የነበረው ሰው ቁጥር ቀላል የሚባል አልነበረም። በተለይ ደግሞ ተማሪው፣ መምህሩ፣ አርቲስቱና ሌላውም ኅብረተሰብ ክፍል ጥሩ የማንበብ ባህል ነበረው።

ይሁንና አሁን አሁን አብዛኛው ሰው እጁ ላይ ባለው ተንቀሳቃሽ ስልክ የሚመጡ መረጃዎችን የማየትና የማንበብ አጋጣሚ ያለው ቢሆንም እንደ ከዚህ ቀደሙ ጥልቀት ያለው ንባብ የማድረግ ዝንባሌ የለውም። ረጃጅም ጽሑፎችንና ወፍራም ደርዝ ያላቸውን መጻሕፍት የማንበብ ፍላጎቱ ሞቷል። ከዚህ ይልቅ ቁንጽል ጽሑፎችን ብቻ ማንበብን ይመርጣል። በዚህም አሁን ያለው መጻሕፍትን የማንበብ ባህል በእጅጉ እየቀነሰ ስለመምጣቱ በድፍረት መናገር ይቻላል።

ለዚህም ይመስላል የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ- መጻሕፍት አገልግሎት ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በተለያዩ መሪ ቃላት የንባብ ሳምንት ንቅናቄ በተለያዩ የክልል ከተሞች የጀመረው። በዚህ ዓመትም አገልግሎቱ ከሰሞኑ የንባብ ባህልን ለማሳደግ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን ተርጫ ከተማ ‹‹ንባብ ለሁለንተናዊ ስኬት›› በሚል መሪ ቃል የንባብ ሳምንት መርሃ ግብር አካሂዷል።

በኢትዮጵያ ቤተ- መዛግብትና ቤተ- መጻሕፍት አገልግሎት የአብያተ መዛግብት አገልግሎት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ያሬድ ተፈራ እንደሚናገሩት፣ በመርሃ ግብሩ አስራ አምስት ትምህርት ቤቶች፣ መምህራን፣ ተማሪዎችና በአካባቢው ላይ ያሉ በንባብ ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማት ተሳትፈዋል። ተማሪዎች የንባብ ባህልን እንዲሳድጉ ለማስቻል ከአዲስ አበባ የመጡና የክልሉ ተወላጅ የሆኑ ደራሲያንና ገጣሚያን ተሞክሯቸውን እንዲያቀርቡ ተደርጓል።

በመርሃ ግብሩ ለአስራ አምስት ትምህርት ቤቶች፣ ለአንድ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍትና ለአንድ ማረሚያ ቤት የሚያገለግሉ ከ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው 4 ሺ 600 የሚሆኑ መጻሕፍት በስጦታ ቀርበዋል። በተርጫ ከተማ በሚገኘው ማረሚያ ቤት ውስጥ ለሚገኙ ከ 1 ሺ 200 ለሚሆኑ ታራሚዎችና በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ለሚገኝ ትምህርት ቤት በተመሳሳይ የመጽሐፍ ስጦታ ተበርክቷል። ታራሚዎችም የዚሁ መርሃ ግብር አካል ሆነው ሥነ- ጽሑፍ አቅርበዋል። ይህም ታራሚዎች በማረሚያ ቤት በሚቆዩበት ጊዜ አንብበው ራሳቸውን እንዲቀይሩና ወደ ማህበረሰቡም ሲቀላቀሉ ብዙ ነገር እንዳያመልጣቸው ያስችላል።

መሪ ሥራ አስፈፃሚው እንደሚያስታውሱት ተቋሙ የንባብ ባህልን የማሳደግ ሥራ የጀመረው ከ2006 ዓ.ም ወዲህ ነው። ከ2011 ዓ.ም በኋላም በተጠናከረ መልኩ ሥራውን አስቀጥሏል። በአብዛኛው በኢትዮጵያ ያሉ ትልልቅ ከተሞች እንዲሁም የወረዳ ከተሞች ላይ ተቋሙ እየሠራ ይገኛል።

ከትግራይ ክልል መቀሌ ጀምሮ ጎንደር፣ ደብረ ታቦር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ባህርዳር፣ ሰመራ፣ አሶሳ እንዲሁም በቅርብ ዓመታት ደግሞ በዲላ፣ ሀዋሳ፣ ደብረ ብርሃንና በሌሎችም ክልሎች የንባብ ባህልን ለማሳደግ ሰፋፊ ሥራዎች ተሰርተዋል። በወረዳዎች በተለይ ተመሳሳይ ሥራ ተሰርቷል። ልዩ ቤተ መጻሕፍትን በአዲስ መልክ የማደራጀት ሥራም ተከናውኗል። በቀጣይም በባህር ዳር፣ ኮንሶ የሚገኙ ሌሎች ቤተ መጻሕፍትን በአዲስ መልክ ለማደራጀት እቅድ ተይዟል።

አገልግሎቱ በብዛት የሚሰራው ከትምህርት ቤቶች፣ ከማረሚያ ቤቶችና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ነው። መጻሕፍት የሚሰጣቸው ተቋማት በአደረጃጀት ውስጥ ያሉ ናቸው። ስለዚህ ቀድሞ የሚደረገው ትምህርት ቤቶች፣ ማረሚያ ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ምን እንደሚፈልጉ፣ ምን ያህል ሰዎች እንዳሉና በየትኛው ደረጃ እንደሆነ ጥናት ይደረጋል። ይህንን መነሻ በማድረግ ለእነርሱ የሚጠቅም በአብዛኛው የመማር ማስተማሩን ሂደት የሚያግዝና የጠቅላላ እውቀታቸውን የሚሳድግ መጻሕፍት ተገዝቶ እንዲሰጣቸው ይደረጋል።

በኋላ ላይ ደግሞ ተቋሙ መጻሕፍቶቹ በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋሉ ስለመሆናቸው ተመልሶ የሚያይበት መንገድ አለ። ከየክፍሉ የተዋቀረ የባለሙያዎች ቡድን ወጥተው ከዚህ በፊት የተሠሩ ሥራዎችን በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ያያሉ። ችግሮች ካሉ በመለየት እንዴት መስተካከል እንዳለባቸው መፍትሔ ይፈልጋሉ። ይህም ሥራ የቁጥጥርና በቀጣይ ለመሥራት የታሰበውን ሥራ ለማየትና ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የሚያስችል ነው።

መሪ ሥራ አስፈፃሚው እንደሚገልፁት፣ የንባብ ባህልን ለማዳበር ሰፊና ብዙ ሥራዎችን መሥራት ይጠይቃል። የበርካታ ተቋማትን ቅንጅትም ያስፈልገዋል። ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ከባህል፣ ስፖርትና ቱሪዝም ቢሮዎችና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር እየሠራ ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ ተቋሙ በተለያዩ ክልሎች ተዘዋውሮ በሚሰራቸው ሥራዎች ትምህርት ቤቶች፣ ማረሚያ ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት ሥራውን የራሳቸው አድርገው እንዲያስቀጠሉ የማድረግ ሥራም ይሠራል።

ለምሳሌ ደብረ ታቦርና መቀሌ ይህን የንባብ ሳምንት ሃሳብ በመውሰድ በየዓመቱ ማከናወን ጀምረው ነበር። የዚህ ንባብ ሳምንት ሁሌም በየዓመቱ መካሄድ ትልቁ ፋይዳ የሚሆነውም ሃሳቡን ተረድተው እንዲተገብሩት ነው። በዛውም ለቤተ መጻሕፍት ያላቸው እውቀትና አያያዝ እንዲጎለበት ነው። መጽሐፍ ሻጮች የሚሳተፉበት የመጽሐፍ አውደ ርዕይም አለ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፓናል ውይይቶች ይካሄዳሉ። እነዚህ የፓናል ውይይቶች በቤተ መጻሕፍት፣ በቤተ መዛግብት፣ በዲጂታል ላይብረሪ ያሉትን ሁሉ በተቋሙ በኩል የሚሰሩ ሥራዎችና የሌሎችም ተቋማት ተሞክሮ ይቀርባሉ።

በጥቅሉ ፋይዳው ሲታይ ደግሞ በሀገሪቱ የንባብ ባህል እንዲጎለብት ማድረግ ነው። የንባብ ባህልን ለማሳደግ ደግሞ ቤተ መጻሕፍት በሚገባ መደራጀት ይኖርባቸዋል። በተለይ ደግሞ ማህበረሰቡ ቤተ-መጻሕፍትን የራሱ እንዲያደርገው፣ የውይይትና ንግግር ቦታ እንዲሆን ማድረግና ማነቃቃት ነው የተቋሙ ዋነኛ ፍላጎት። ይህንን ሥራ ደግሞ ደራሲያን በሶስትና አራት ወራት ውስጥ ማከናወን ይችላሉ።

በሌላው ዓለም ያሉ ቤተ መጻሕፍት የፀጥታው ንባብ እንዳለ ሆኖ የማኅበረሰብ የመሰባሰቢያ ቦታ እየሆኑ መጥተዋል። ለምሳሌ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ደራሲዎች በቤተ መጻሕፍት ውስጥ ባሉ ካፍቴሪያዎች ስለሚበሉትና ስለሚጠጡት ሳይጨነቁ እየተዝናኑ ከወጣቶች ጋር እንዲገናኙ እድል ይፈጥርላቸዋል። እነርሱ ቤተ መጻሕፍትን የማኅበረሰቡ መገናኛ ማእከል አድርገዋቸዋል። ቤተ መጻሕፍት የመረጃ፣ የመዝናኛ፣ የእውቀትና የሥራ ቦታ ሆነዋል። ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ግቢ ውስጥም እየታየ ነው። ይህን ማሳደግ ይገባል። ያኔ ቤተ መጻሕፍት የመገናኛ ቦታ ይሆናል።

መሪ ሥራ አስፈፃሚው እንደሚያብራሩት ባጠቃላይ የቤተ መጻሕፍት ጉዳይ በሀገር ደረጃ ትልቅ ትኩረት አግኝቶ እየተሠራበት አይደለም። እንዲያውም ‹‹አብርሆት›› የተሰኘው ቤተ መጻሕፍት በአዲስ አበባ ከተከፈተ ወዲህ ነው ቤተ መጻሕፍት በዚህ ደረጃ መታነፅ ይችላል ወይ? የሚለውን ያሳየውና ተነሳሽነትን የፈጠረው እንጂ ከዛ በፊት በነበረው ሁኔታ የንባብ ባህል በኢትዮጵያ በእጅጉ ቀንሶ ቆይቷል። ስለዚህ በበርካታ አካባቢዎች ላይ ቤተ መጻሕፍቶችን በአግባቡ ማነፅ ላይ ክፍተት ይታያል።

በሌላ በኩል ደግሞ በቤተ መጻሕፍት ሙያ ዩኒቨርሲቲዎች በትክክለኛው ደረጃ ምሁራንን እያፈሩ አይደሉም። ይህም የንባብ ባህልን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት እያጋጠሙ ካሉ ችግሮች ውስጥ አንዱ ነው። ምክንያቱም ቤተ መጻሕፍት ሲገነቡ ትክክለኛ ባለሙያዎች በቦታው መመደብ ስላለባቸው ነው። በቤተ መጻሕፍት ሙያ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች በደንብ መጠቀም እንዲችሉ መደረግ ያለበት ሥራም አለ።

ስለዚህ እነዚህ የንባብ ባህልን ለማሳደግ ማነቆ ከሆኑ ምክንያቶች ውስጥ በዋናነት ይጠቀሳሉ። ማነቆዎቹን መፍታት የሚቻል ከሆነ ግን የሚፈለገውን የንባብ ባህል በማዳበር የዜጎችን እውቀት መጨመርና አመለካከታቸውን ማሳደግ ይቻላል። ለዚህ ደግሞ ራሱን የቻለ ፖለሲ መቀረጽ ይኖርበታል። በተለይ ቤተ መጻሕፍት በሀገር አቀፍ ደረጃ በስፋት እንዲሰራበት የሚያስችል ፖሊሲ ያስፈልጋል። ዩኒቨርሲቲዎችም በቤተ መጻሕፍት የትምህርት ዘርፍ በሁሉም ደረጃ ማፍራት ይጠበቅባቸዋል። በዚህ የሙያ ዘርፍ ያሉ ሙያተኞችም ከሙያቸው ተጠቃሚ የሚሆኑባቸው ሁኔታዎች በልዩ ልዩ መልኩ መመቻቸት ይኖርባቸዋል።

የቤተ- መጻሕፍት ባለሙያዎችን ከማፍራት አኳያ ዩኒቨርሲቲዎች ትልቅ ድርሻ ያላቸው ቢሆንም የኢትዮጵያ ቤተ- መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት በቤተ መጻሕፍት ደረጃ የአንድ ወር የሥራ ላይ ሥልጠና ዓመቱን ሙሉ ይሰጣል። ሥልጠናው በሁለት መልኩ የሚሰጥ ሲሆን አንደኛው ከየክልሉ ለሚመጡ ሲሆን ሁለተኛው በዛ ያሉ ሰልጣኞች ካሉ እዛው ክልሉ ድረስ በመሄድ የሚሰጥ ሥልጠና ነው።

ይህም በአብዛኛዎቹ ዩኒቨርሲቲዎችና የባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ተዳርሷል። ሥልጠናው ሰልጣኞች መሠረታዊ የቤተ መጻሕፍት እውቀት ኖሯቸው መጻሕፍት እንዲያሰባስቡና ቤተ መጻሕፍት እንዲያደራጁ ያስችላቸዋል። ሆኖም ከዚህ ላቅ ያሉ ሥልጠናዎችን መስጠት ይፈልጋል። ይህም ከዲፕሎማ እስከ ፒ ኤች ዲ ደረጃ ከፍ እያለ ሲሄድ የቤተ መጻሕፍት ባለሙያዎችን ቁጥር ያሳድገዋል።

ዲጂታል ቴክኖሎጂውም ቢሆን የንባብ ባህል እንዲቀንስ በማድረግ ረገድ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅእኖ ቢኖረውም ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ሲታይ በኢትዮጵያ የዲጂታል ነገር ብዙ የተስፋፋ አይደለም። ነገር ግን ዲጂታል ቴክኖሎጂውን እንደ እድል መጠቀም ይቻላል። የኤሌክትሮኒክ ቤተ መጻሕፍቶችን በመገንባት ለተጠቃሚው ማቅረብ ይቻላል። ከዚህ ውጭ ግን ጥልቀት ያለው የንባብ ባህል እንዲመጣና ቁንፅል የሆነው የፌስ ቡክና የሌሎችም ማህበራዊ ሚዲያዎች ጽሑፎች ብቻ እንዳይነበቡ ትልቁና በዋናነት መሠራት ያለበት እውቀት ያላቸውን ሰዎች ከወጣቱና ከሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች አንባቢያን ጋር ማገናኘት ነው።

ደራሲዎች ስለህትመት ሳይጨነቁ እንዲፅፉ ማበረታታትና መሸለም ያስፈልጋል። ንባብ ሊያድግ የሚችለው ከቤተሰብ ጀምሮ ወደ ትምህርት ቤትና ወደ ማህበረሰብ እያለ ነው። ስለዚህ በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በትምህርት ቤትና በማህበረሰብና በተቋም ደረጃ ትልቅ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። እነዚህን ሁሉ ማድረግ ሲቻል ነው የንባብ ባህልን በኢትዮጵያ ማሳደግ የሚቻለው።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2016 ዓ.ም

Recommended For You