“በአካባቢያችን በጉጂ ዞን ሰፊ መሬት አለ። የሚታ ረሰው በባህላዊ መንገድ በመሆኑ ለከፍተኛ የምርት ብክነት የተጋለጠ ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም የአብዛኛው የአካባቢው አርሶ አደር ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ሆኖ ቀጥ ሏል” ይላል በምዕራብ ጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ ነዋሪው ወጣት ኤቢሳ ዳንኤል ዱቤ።
ይህ በሁሉም አካባቢ ያለ ችግር መሆኑንና አሠራሩ ካልተቀየረ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የምርት እጥረት መቀየር እንደማይቻል ይጠቁምና፤ አሁን እኛ ወደ ግብርናው የምንሰማራው በዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ ታግዘን በመሆኑ የምርት ብክነት አይኖርም፡፡ ሰፊ የሰው ሃይል በስራው ስለሚሰማራና በዝናብ ላይ ባለመ መስረታችን የምርት ዕድገት ይኖራል ይላል፡፡
ወጣት ኤቢሳ በወተር ሳፕላይ የተመረቀው በ2009 ዓ.ም ሲሆን፤ ዕድል ባለማግኘቱ ሥራ አጥ ሆኖ ቆይቷል። ምንም እንኳን በንድፈ ሃሳብ ያካበተው የመስኖ እርሻ ዕውቀት ቢኖረውም የመስኖ እርሻ ሞክሮ አያውቅም። በክረምት ቤተሰቦቹን በባህላዊ የግብርና ሥራ ያግዝ ነበር። “አሁን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በግብርናና ተያያዥ ሙያዎች የተማሩ ወጣቶች በመስኖ ልማት እንዲሰማሩ ዕድሉን ማመቻቸቱ ትልቅ ተስፋ እንድሰንቅ አድርጎኛል፡፡ ወደ ሥራው ለመሰማራትም በከፍተኛ ቁርጠኝነት ነው የተነሳሳሁት፤” ሲልም ይገል ጻል።
ለራሱ ካገኘው የሥራ ዕድል ባሻገር፤ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን የሚጠቁመው ወጣት ኤቢሳ፤ ተመርቀው ሥራ ላጡ ወጣቶች አማራጭ የስራ ዕድሎች መከፈታቸው ተስፋ እንዲሰንቁ ያደርጋል ባይ ነው፡፡ በስራ አጥነት ወደ ተለያዩ ሱሶች ከመግባት ታቅበው የራሳቸውን ገቢ እንዲፈጥሩ በር ይከፍታል። ተተኪዎች የታላላቆቻቸውን ፈለግ በመከተል ለለውጥ ይነሳሳሉ፤ የተሻለ ትውልድ እንዲፈጠር አጋዥ ነው ሲልም ያመለክታል፡፡
የባሌ ሮቤዋ ወጣት እታሌ ፍቃዱ ከሀዋሳ ዮኒቨርሲቲ በአግሮ ፎርስተሪ የተመረቀችው በ2008 ዓ.ም ቢሆንም እስካሁን ሥራ አልጀመረችም፡፡ አሁን ይህ አጋጣሚ መፈጠሩ ትልቅ ዕድል መሆኑንና የሥራ ዕድል ከማስገኘት ባሻገር፣ ቤተሰቦቿን ለመደገፍና ኢኮኖሚን በማሳደግ ድርብ ጥቅም ያለው መሆኑን ትገልጻለች፡፡ የአርሶ አደር ልጅ እንደመሆኔ ግብርናው ብዙ አያስቸግረኝም። ልዩነቱ አሁን የምንሰማራው በዘመናዊ መንገድ በመታገዝ መሆኑ ነው፤ ይህ ደግም ስራውን ያቀልልናል ብላለች፡፡
ወጣት ኤቢሳንና ወጣት እታሌን ያገኘኋቸው ሰሞኑን ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልሎች የተውጣጡ 943 የተማሩ ወጣቶች የመጀመሪያ ዙር የስልጠና መክፈቻ በተካሄደበት መርሐ ግብር በአዳማ ከተማ ነው፡፡ በመክፈቻው ዕለት የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ፤ ለስራው የተመለመሉ ወጣቶች ከስድስት የተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች ማለትም፤ ከጉጂ፣ ከምዕራብ ጉጂ፣ ከአርሲ፣ ከምዕራብ አርሲ፣ ከባሌና ከቦረና፤ የተውጣጡ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ መንግስት ይህንን የወሰነው ወደ ኢንዱስትሪ መር ለሚደረገው ሽግግር ግብርናው መጠናከር እንዳለበት በማመኑ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡
80 በመቶ የሚገመተው ህብረተሰብ የሚኖረው በገጠር በመሆኑና ኑሮው የተመሰረተውም በግብርና ላይ በመሆኑ ግብርናውን ማዘመን ግድ ይላል ባይ ናቸው፡፡ የገጠሩ ኢኮኖሚ ሳይሻሻል የከተማውን ብቻ በመቀየር የሚፈለገው ለውጥ እንደማይመጣም አቶ ዳባ ይናገራሉ፡፡ የለውጥ አመራሩ ወደ ኃላፊነት ከመጣ በኋላ ለግብርና ዘርፍ ትኩረት የሰጠው ይህንኑ በመረዳት መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ ለወጣቶቹ አስፈላጊው ቴክኖሎጂ በመንግሥት እንደሚቀርብም ይጠቅሳሉ፡፡
ግብርናን ለማዘመን የተማረ የሰው ሃይል ወሳኝ መሆኑን በመጠቆምም፤ ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡት ሰልጣኞች በዘርፉ የተማሩ በመሆናቸው ትልቅ ኃላፊነት እንደሚጠበቅባቸውም ነው የሚገልጹት፤ “በተለይ እርሻውን ከዝናብ ጥገኝነት ለማውጣትና በዓመት ሁለትና ሦስት ጊዜ ለማምረት የመስኖ እርሻ ወሳኝ ነው፡፡ በዘርፉም ዕውቀት ያለው ሃይል ማግኘት መታደል ነው፤” ይላሉ፡ ፡ በተለይ በአርሲና በባሌ በዘመነ መንገድ ከተመረተ ከአካባቢው ኅብረተሰብ አልፎ ለአገሪቱና ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚቻልም አቶ ዳባ ይጠቅሳሉ፡፡
“ድህነትን ታሪክ፤ ብልጽግናን ዕውን ለማድረግ መስራት አለባችሁ” ያሉት ኃላፊው፤ ከዓመታት በፊት ያደረጋችሁት ትግል ይህንን ዕድል ይዞላችሁ መጥቷል፤ ተጠቀሙበት ብለዋል፡፡ በቀጣይም መርሐ ግብሩ የአርጆ ደዴሳን ግድብ በመጠቀም የመስኖ ልማቱን የማስፋፋት፣ ለተማሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩ ይቀጥላል፣ ሰፋፊ እርሻዎች ላይ ትኩረት ይደረጋልም ብለዋል፡፡ ጉደር ወልመሊና ጨልጨል ግድብ ላይ አዲስ ፕሮጀክት እንደሚጀመርና በዚህም ወጣቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ይጠቁማሉ፡፡
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፤ ምርታማነትን የሚጨምርና ሥራ አጥነትን ሊቀንስ የሚችል ለመስኖ የሚሆን አምስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ቢኖርም፤ ከዚህ ውስጥ የለማው ከ20 በመቶ እንደማይበልጥ ይጠቁማሉ፡፡
በ2017 ዓ.ም ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣት መንግሥት ለመስኖ ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ይጠቁሙና፤ መርሐ ግብሩ ይህንን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚደግፍ ይናገራሉ፡፡ ምርትን በማሳደግ ከራስ አልፎ ለውጭ ገበያ ለማምረት የተቀየሰ መሆኑንም ያብራራሉ፡፡ ለዚህም በአጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ በጥቅሉ 30 ሺህ ወጣቶች በመስኖ ልማት እንዲሰማሩ በማገዝ 124 ሺህ ሄክታር መሬት የመስኖ እርሻዎች እንዲለሙ የማድረግ ግብ መያዙንም ያስረዳሉ፡፡ በሶማሌና በጋምቤላ ክልሎች አንድ ሺህ 200 የሚደርሱ የተማሩ ወጣቶች ተመዝግበው ለመሰልጠን እየተዘጋጁ መሆናቸውንም ይጠቁማሉ፡ ፡ ከኦሮሚያ ግድብ ተውጣጥተው ስልጠና የጀመሩት ወጣቶች በጊዳቦ ግድብ ስድስት ሺህ ሄክታር የሚገመት መሬት በመስኖ እንደሚያለሙ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2011
ዘላለም ግዛው