• ከፍትሐዊ ድልድልና ቀመር አኳያም ጥያቄዎች ተነስተውበታል
አዲስ አበባ፡– የ2012 ዓ.ም የገንዘብ ሚኒስቴር ረቂቅ በጀት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ለውይይት በቀረበበት ወቅት አጠቃላይ የፌዴራል መንግሥት የወጪ በጀት 387 ቢሊዮን ብር እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን፤ ከፍትሃዊ ድልድልና ቀመር አኳያ ሰፊ ጥያቄዎች ተነስተውበታል፡፡
ረቂቅ በጀቱን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ያቀረቡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ለ2012 ዓ.ም የተደለደለው አጠቃላይ የፌዴራል መንግሥት የወጪ በጀት 387 ቢሊዮን ብር መሆኑን የገለፁ ሲሆን፤ ይህም በ2011 በጀት አመት ከፀደቀው በብር ስድስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ጭማሪ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
ከአጠቃላይ ከተያዘው በጀት ውስጥ ለመደበኛ ወጪ 109 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር፣ ለካፒታል 130 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር፤ እንዲሁም ለክልል መንግሥታት ድጋፍ ብር 140 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈፀሚያ ስድስት ቢሊዮን ብር ተደግፎ መቅረቡን ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
ተደግፎ ከቀረበው ውስጥ 38 በመቶ የሚሆነው ድርሻ የዘላቂ ልማት ግቦችን ድጋፍ ጨምሮ ለክልል መንግሥታት የተመደበው የበጀት ድጋፍ መሆኑን ሚኒስትሩ የጠቀሱ ሲሆን፤ የመደበኛ 28 በመቶ እንዲሁም የካፒታል ድርሻ 34 በመቶ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የካፒታል በጀት ወጪ አሸፋፈኑ ከአገር ውስጥ ከሚሰበሰብ ገቢና ከውጪ አገር ከሚገኝ እርዳታና ብድር መሆኑንም ሚኒስትሩ አንስተው፤ ከመንግሥት ትሬዠሪ 94 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር፤ ከእርዳታ 18 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እና ከብድር 17 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የካፒታል ወጪ በጀት መያዙን አስታውቀዋል፡፡
ለመደበኛ ወጪ ከተደለደለው 109 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ውስጥ 34 በመቶ የሚሆነው ለደመወዝ፣ አበልና ልዩ ልዩ ክፍያዎች የሚውል መሆኑንም ሚኒስትሩ አያይዘው የገለፁ ሲሆን፤ ቀሪው 66 በመቶው ለአላቂና ቋሚ እቃዎች፣ ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች፣ ለብድር ክፍያና ለመሳሰሉት የሥራ ማስኬጃ ወጪዎች የሚውል መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ከአጠቃላይ የ2012 መደበኛና ካፒታል በጀት ውስጥ 63 በመቶ የተመደበው ቅድሚያ ትኩረት ለተሰጣቸው ትምህርት፣ መንገድ፣ ግብርና፣ ውሃ፣ ጤናና ከተማ ልማት ወጪዎች መሆናቸውንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
በ2012 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ከአገር ውስጥ የገቢ ምንጮች፤ እንዲሁም ከውጪ ሀገር እርዳታ፤ ባጠቃላይ 289 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ በእቅድ መያዙን ሚኒስትሩ ጨምረው የገለፁ ሲሆን፤ ለመደበኛ፣ ለካፒታልና ለብሄራዊ ክልላዊ መንግሥታት የበጀት ድጋፍና የዘላቂ ልማት ግቦች ማጠናከሪያ ወጪ በድምሩ 387 ቢሊዮን ብር በጀት ተደግፎ መቅረቡንም ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሰረት በታቀደው የፌዴራል ገቢና ተደግፎ በቀረበው የወጪ በጀት መካከል የሰባት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ጉድለት መታየቱን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ ይህንኑ የበጀት ጉድለት በቀጥታ በጀት ድጋፍና በፕሮጀክት ከሚገኝ ብድር በ40 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር እና ከአገር ውስጥ ከሚገኝ ብድር 56 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለመሸፈን በእቅድ መያዙን ገልፀዋል፡፡
በረቂቅ በጀቱ ላይ ከፍትሃዊ የበጀት ድልድልና ከበጀት ቀመር ጋር በተያያዘ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሰፊ ጥያቄዎች ተነስተዋል። በዚህም መሰረት፤ ከቀመር ጋር በተያያዘ ሚኒስትሩ ለክልሎች የሚመደበው የበጀት ድጎማ በነባሩ ቀመር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይ ቀመሩ ሲሻሻልም በጀቱ የሚመደበው በተሻሻለው መሰረት መሆኑን ጠቁመዋል። የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የጋራ ገቢ ላይ ግን ገና እንዳልተወሰነ ሚኒስትሩ የጠቀሱ ሲሆን፤ በቀጣዩ በጀት ዓመት አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ታሳቢዎችና የገቢ ግምት ከተሰራና ሙሉ በሙሉ የበጀት ቅድመ ዝግጅት ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ የመጣ ስለሆነ በዚያ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ መፈጠር ስላለበት በትንሹ የአንድ ዓመት ቅድመ ዝግጅት ይፈልጋል ብለዋል፡፡
የጋራ ገቢዎች ላይ ለውጥ ማምጣት የሚቻል ከሆነ ድጎማ ላይም በተመሳሳይ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። ይህም ከፍትሃዊነት ጋር የሚያያዝ ነገር እንደሌለው አስምረውበታል፡፡
ከፍትሃዊ የበጀት ድልድል ጋር በተያያዘ ሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በእኩል መልኩ መልማት እንዳለባቸው ሚኒስትሩ ያስገነዘቡ ሲሆን ይህን ለማሳካት ግን በየአካባቢው ያሉ ህዝቦችን በማስተባበርና አቅማቸውን በመጠቀም መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ክልሎችም በጀታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ በልማት ሥራዎች ላይ ማዋል እንደሚኖርባቸው ገልፀው፤ በፌዴራል ካፒታል በጀት ብቻ የሚፈታ ችግር እንደሌለ አመልክተዋል፡፡
የፌዴራል ካፒታል በጀት ሲበጀት ፍትሃዊ መሆኑ ተገቢ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የዘንድሮው በጀትም ጥንቃቄና ፍትሃዊነትን በተላበሰ መልኩ እንደተዘጋጀ ገልፀዋል፡፡ በተለይም በጀት አቅራቢ መስሪያ ቤቶች የፍትሃዊነትን ጉዳይ ከክልሎች ጋር ውይይት በማድረግ እንዲያቀርቡ ከተደረገ በኋላ በጀቱ ተደገፎ እንዲመጣ መደረጉን ሚኒስትሩ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፤ ረቂቅ በጀቱ ለዝርዝር እይታ ለገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2011
አስናቀ ፀጋዬ