አዲስ አበባ፡-የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ከአክሱም ከተማ ነዋሪዎች ጋር ያደረጉት ውይይት በነዋሪዎቹ ሲነሳ የነበረውን የአክሱም ሐውልት ጥገና ጥያቄ የሚመልስ እንደነበር የትግራይ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሊያ ካሳ ተናገሩ፡፡
ኃላፊዋ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ለአክሱም ሐውልት ጥገና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩት እንቅስቃሴ መኖሩንና ለዚህም ከኢጣሊያ መንግሥት ጋር በመሆን ጥገናው እንደሚፋጠን በውይይቱ ወቅት መናገራቸውን ገልፀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነዋሪዎቹ ጋር ባደረጉት ውይይትም ከህገመንግሥት ጥሰትና ፌዴራሊዝም ስርዓት አለመከበር ጋር በተያያዘ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ እንደሰጡ የገለፁት ወይዘሮ ሊያ፤ የክልሉ ነዋሪዎች ከተለያዩ አካባቢዎች እየተፈናቀሉ ስለመሆናቸው፣ ስለመጪው ምርጫ፣ የአክሱም ከተማ የውሃ አቅርቦት ችግር እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች በተደረገው የግማሽ ቀን ውይይት እንደተዳሰሱ ተናግረዋል፡፡
የአክሱም ከተማን የውሃ አቅርቦት ችግር በተመለከተ በነዋሪዎቹ የተጠየቀው ጥያቄ ከክልሉ አቅም በላይ ነው ያሉት ወይዘሮ ሊያ በሂደት ግን ሊታይ እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ወደ አክሱም ከተማ የመጡት የአክሱም ከተማ ነዋሪዎች ማህበር የአክሱም ሐውልት የተጋረጠበትን አደጋ በአካል ተመልክተው መፍትሄ እንዲሰጧቸው ባደረጉላቸው ጥሪ መሰረት ብቻ መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ ሊያ፤ በተለያዩ ሚዲያዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር ሊወያዩ ነው በሚል የተናፈሰው ወሬ መሰረተ ቢስ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተገኘ መረጃ መሰረት፤ ሰኔ 3 ቀን 2011 ከአክሱም ከተማ ነዋሪዎች ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ ጠ/ ሚር አቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ከሆኑት አርቱሮ ሉዚ ጋር በትናንትናው እለት ተገናኝተዉ የእድሳት ስራውን ስለማስጀመር ተወያይተዋል። በጣሊያን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሚመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድንም በአክሱም ሐውልት እድሳት ዙሪያ ለመምከር በመጪው ሳምንት አዲስ አበባ ይገባል፤ ተብሏል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2011
ድልነሳ ምንውየለት