በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን ገጽታ የሚቀይሩና ማራኪ ውበትን ማላበስ የሚችሉ የልማት ሥራዎች በስፋት በመሠራት ላይ ይገኛሉ። ከነዚህም መካከል ፓርኮች፣ ሙዝየሞችና ለኅብረተሰቡ የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት የሚችሉ ስፍራዎች ዋነኞቹ ናቸው። እነዚህ ቦታዎች በከተማዋ የሚስተዋለውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ፍላጎት መጨመርን ተከትሎ፣ ግንባታ ሲያካሂዱ ፍላጎቶቹን ያገናዘበና እነሱን ያካተተ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት ምክር ቤት አስታውቋል።
የስፖርት ምክር ቤቱ ሰሞኑን 14ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዶ በከተማዋ የተሠሩና መሠራት የሚገባቸውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታና ሌሎች ጉዳዮችን ገምግሟል። በዚህም መሠረት የ2015 ዓ.ም እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2016 ዓ.ም እቅድ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት ሊፀድቅ ችሏል። ከቀረቡትና ውይይት ከተደረገባቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል የስፖርት ትምህርትና ስልጣና፣ የማህበረሰብ ስፖርት፣ የስፖርት ማህበራት፣ የስፖርት ውድድሮች፣ ከስፖርት ቤተሰቡ ጋር ለመሥራት የተደረገው ጥረትና የማዘውተሪያ ስፍራዎች ይገኙበታል።
በምክር ቤቱ ቀረበው ውይይት ከተደረገባቸው ነጥቦች መካከል በከተማዋ የሚገኙ ማዘውተሪያዎች ቀዳሚውን ቦታ ይይዛሉ። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በጥቅሉ 1236 የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን 741 ቦታዎች ባለፉት 5 ዓመታት የተሠሩ እንደሆነም ተመላክቷል። ከነዚህም ውስጥ በ2015 ዓ.ም ከመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ ከተገኘው ገቢ 13 የወጣቶች ስፖርት ማዘውተሪያና የሕፃናት መጫወቻ ስፍራዎች ሊገነቡ ችለዋል። ይህ ዘንድሮም ተጠናክሮ በመቀጠል በተጋመሰው የበጀት ዓመት 38 የሚደርሱ የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ስፖርት ምክር ቤት ተቀዳሚ ዓላማ ለኅብረተሰቡ ምቹ፣ በቂና ሁሉን ያማከለ የስፖርት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ በመሆኑ፣ ይህን እውን ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እንደተሠሩና ተጨማሪ ሥራዎችን ለመሥራትም እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ተጠቁሟል። የኅብረተሰቡ የስፖርት ጠቀሜታ ግንዛቤ እየጨመረ በመምጣቱ ያለው የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራና ፍላጎቱ ሊጣጣም ባለመቻሉ፤ ይህን ከፍተት ለመድፈን በመንግሥት፣ በስፖርት ምክር ቤቱና በበጎ ፍቃደኛ ባለሀብቶች ትብብር እነዚህን ስፍራዎች ገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ሊደረጉ ችለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ትላልቅና ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ያሏቸው፣ የከተማዋ ፕሮጀክቶች የሚታየውን ከፍተኛ ፍላጎት በተወሰነ መልኩ ለመቅረፍ የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራን አካተው እየተገነቡ እንደሆነም ተጠቅሷል። የዓድዋ መታሰቢያ ሙዝየምና የሴቶች ተሀድሶና አእምሮ ማበልጸጊያ ማዕከል ለማሳያነት ቀርበዋል። እነዚህ ቦታዎች በውስጣቸው ጂምናዝየሞችንና የተለያዩ መጠን ያላቸውን ሜዳዎች በመያዝ ተሠርተው ሊጠናቀቁ ችለዋል። ይህንኑ ጅምር በማስቀጠል በቀጣይ የሚሠሩ የከተማዋ ፕሮጀክቶች የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራን አካተው እንዲገነቡ ምክር ቤቱ በልዩ ሁኔታ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የሚሠሩ የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎች ሁሉንም ስፖርት ፌዴሬሽንና አሶሴሽን ያማከለ ሆነውና ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርጉ ስፖርቶች የሚገኙባቸውን ክፍለ ከተሞች መሠረት በማድረግ ሲሆን፤ ይህም ቀጣይነት እንዳለው ተጠቁሟል።
የስፖርት ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ በላይ ደጀን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን የማስፋፋት፣ የማልማት፣ ተጀምሮ የነበሩትን ማጠናቀቅና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በጊዜው ማጠናቀቅ የምክር ቤቱ ተቀዳሚ ሥራ መሆኑን ጠቁመዋል። ለዚህም በከተማዋ እየተሠሩና ተሠርተው የተጠናቀቁ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል። መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ውስጥ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በማልማት የወጣቶችንና የስፖርት ቤተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ላይ በስፋት እየተሠራ እንደሆነም አስረድተዋል።
የሚገነቡት ትልልቅ ፕሮጀክቶች፣ አዳዲስ ሆቴሎችና የመዝናኛ ስፍራዎችም የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎችን አካተው እንዲገነቡ እየተደረገ መሆኑን አክለዋል። ሰፊውን የኅብረተሰብ ፍላጎት ለማሟላት በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ከትምህርት ሰዓት ውጪ ለአካባቢው ኅብረተሰብ አገልግሎት እንዲሰጡም እየተሠራ ነው።
በከተማዋ የሚገኙ የተለያዩ ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች ውድድርና ስልጠና የሚሰጡበት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተሠርተው ሊጠናቀቁ እንደቻሉ የተገለጸ ሲሆን፤ በከተማ አስተዳደሩና በመንግሥት ድጋፍ በተለያዩ የከተማዋ ስፍራዎች ጥራታቸውን የጠበቁና ሁሉንም ያማከሉ ማዘውተሪያዎች ተገንብተው የማረጋገጫ ካርታንም ማግኘት እንደቻሉ አቶ በላይ ጠቁመዋል።
ካለው ከፍተኛ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ፍላጎት አኳያ መንግሥት ብቻውን ፍላጎቱን ሊያሟላ የማይችል በመሆኑ የሌሎች አካላት እገዛና ድጋፍን ይፈልጋል። በዚህም ላይ ለውጦች እንዳሉና ባለሀብቶች እገዛዎችን በማድረግ ብዙ ማዘውተሪያዎችን እየገነቡና እያደሱ እንደሆነ ተገልጿል። በዚህም 30 የሚደርሱ የማዘውተሪያ ስፍራዎች በበጎ ፍቃደኞችና ባለሀብቶች ትብብር ሊገነቡ ችለዋል። በተጨማሪም ሁለት ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟሉ የማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማሻሻያ በማድረግ ለአገልግሎት ክፍት ሊደረጉ ችለዋል። 10 የማዘውተሪያ ስፍራዎች ሀገር አቀፍ ደርጃን የጠበቁ እንዲሆኑ ተደርገው መሻሻላቸውም ተጠቅሷል።
ዓለማሁ ግዛው
አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2016 ዓ.ም