መክሊቷን ዘግይታ የተረዳችው ድምፃዊት

ከፒያሳ ተነሰቶ ወደ አዲስ አበባ ሰሜናዊ ክፍል የሚገሰግሱት ኮስትር አውቶብሶች ለመድረሻቸው የናፈቁ ይመስላሉ። በፍጥነት ተከታትለው ጥቁሩን አስፓልት ሲገምሱ ለተመለከታቸው ዓይን ይስባሉ። በአግባቡ አሸብርቆ የተሠራው መንገድ የእንጦጦ ጋራን አሳምሮታል። ከዳር ዳር ተራራውን በሸፈነው ዛፍ መካከል እያቆራረጥን የኩሪፍቱ እንጦጦ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ደርሰናል።

አዳራሹ መግቢያ ላይ ቀያይ አበባን ይዘው የቆሙት ወጣት ሴቶች ቀኑ እውነትም የሴቶች ነው የሚያስብሉ ናቸው። አሚጎስ የተባለ የቁጠባና የብድር ህብረት ሥራ ማህበር ለሴቶች ቀን ባዘጋጀው መድረክ ላይ ነበር የተገኘው። በእለቱ የቁጠባ ማህበሩ አባላት፤ የተቋሙ ሠራተኞችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተው ነበር። በእለቱ የሕይወት ልምዳቸውን ካከፈሉን ጠንካራ ሴቶች መካከል አንዷን ለሴቶች ዓምድ እንግዳ አድርጌ ይዤላችሁ ቀርቤያለሁ። መልካም ቆይታ።

እናት መሆን ከሰጣት የእናትነት ውበት በስተቀር በመገናኛ ብዙኃን እንደምትታየው ዓይነት ናት። ደስ የምትል ተግባቢ ‹‹የኛ›› የተባለው ድራማ ላይ እንዳለችው ገፀ ባህሪ ሳይሆን ደርበብ ያለች እናት የምትመስል ቆንጆ ቅልብጭ ያለች ሴት ናት። በእለቱ ለተገኙት ታዳሚዎች የሕይወት ልምዷን ስታካፍል የተመልከትኳት ሴት ለምለም ኃይለሚካኤል ትባላለች። በእለቱ የማህበሩ አባላት ለሆኑና በተለያዩ አጋጣሚዎች ተጋብዘው በእንጦጦ ኩሪፍቱ ለተገኙት ሰዎች ስለራሷ እና በሕይወቷ ስላሳለፈቻችው ውጣ ውረዶች በዚህ መልኩ ተናግራ ነበር።

በተወለደችባት ትንሽዬ የገጠር ከተማ ውስጥ ነው የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው። የአስረኛ ክፍል ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች ወደ መሰናዶ የመግቢያ ውጤት ብታገኝም በአጋጣሚ ቤታቸው የተገኘች ቆንጆ ዘናጭ የጤና ባለሙያን ስትመለከት እንደ እሷ ተቀጥሮ የመሥራት ፍላጎት ያድርባታል። በዚህም የመሰናዶ ትምህርቷን ትታ የግብርና ኮሌጅ ገብታ በእንስሳት ሳይንስ ተመረቀች። ምንም እንኳን የግብርና ባለሙያ ለመሆን ብትማርም የነፍሷ ጥሪ አላስቀምጥ ያላት ወጣት ተነስታ አዲስ አበባ መጣች።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ከተቀላቀለች በኋላ በቲያትሪካል አርት የመጀመሪያ ዲግሪ ሁለተኛ ዲግሪዋን ደግሞ ትያትር ፎር ዴቨሎፕመንት የሚል ትምህርት ተማረች። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከወጣች በኋላ የኛ የተባለውን የሙዚቃ ቡድን ተቀላቀለች።

ከሙዚቃ ቡድኑ በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ መድረክ ላይ የታየችው ሀገር ማለት ሰው ነው የሚል ሀገርን የወከለች ሴት ገፀ ባህሪን ወክላ ለብሔር ብሔረሰቦች ቀን የቀረበ ትያትር ተጫውታ ነበር። ከዚህኛው መድረክ በኋላ የኛ የሚል ለሰባት ዓመታት በሬዲዮ የተላለፈ ሙዚቃዊ ድራማ ላይ ተጫውታለች። በወቅቱ የጎዳና ልጅ ሆና ወንዳ ወንድ ገፀ ባህሪ ተላብሳ ለሰባት ዓመታት ያህል ሰርታለች።

ሁሉም ሰው በሕይወቱ የተሰመረለትን መስመር እንደሚጓዝ የምትናገረው ለምለም ስትወልድ በጣም ገጠር ከተባለች መብራት ከማታገኝ ከተማ መውጣቷ፤ ልጅነቷን እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የገጠር ልጅ ማደጓ፤ ከዛም በኋላ የሞከረቻቸው የሄደችባቸው የሕይወት መስመሮች አንዱ ለአንዱ ድልድይ እየሆነ በስተመጨረሻ መክሊቷን አግኝታ በዛ ሙያ ውስጥ ተሰማርታ ትገኛለች።

በሕይወታችን የምንፈለገውን ባለማወቅ ሕይወታችን ትርጉም እንዳይኖረው እናደርጋለን የምትለው ለምለም እሷ አስረኛ ክፍል ጨርሳ በግብርና ትምህርት ዘርፍ የእንስሳት ሳይንስ ስትማር ዓላማዋ የነበረው ዘጠነኛ ክፍል እያለች በጣም ቆንጆ ወጣት ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በግብርና ሙያ ተመርቃ በሥራው የተሰማራች ሴትን በማየቷ እንደ እሷ የመሆን ፍላጎት እንዳደረባት ትናገራለች።

ከዛ በፊት አትሌት ለመሆን ፈልጋ ሞከራ ያልተሳካላት ጊዜ የነበረ ቢሆንም በእንግድነት ቤታቸው የመጣችውን ወጣት ስታይ ግን እንደሷ መልበስ፤ እንደሷ ፀጉሯን ማስያዝ መፈለግ ጀመረች። ተመርቃ እንደወጣች በጣም ገጠር ውስጥ ስትመደብ መሥራት እንደማትችል ቤተሰቧን አስረድታ መክሊቷን ፍለጋ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት መጣች።

በወቅቱ ቲያትር መማር የፈለገችው በፊልም ስታያት የነበረችው አክሽን ፊልም የምትሰራውን አንጀሊና ጁሊ ለመሆን ነበር። አክተር የሚለውን ስም ትርጉም እንኳን በአማርኛ ሳታውቅ ነበር አክተር ለመሆን ትምህርት ቤት የገባችው። ሳይንሱን ስታወቅ ግን ትወና ሌላ ዓለም መሆኑን ተረዳች። በዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ዲግሪ አራት ዓመታትን ስትማር ቆይታ ስትጨርስ ሥራ የምትይዝ መስሏት የነበረ ቢሆንም ሥራ በቀላሉ እንደማይገኝ የተረዳችው ተመርቃ ሥራ መፈለግ ስትጀምር ነው። ሥራ ለማግኘት የተለያዩ ሙከራዎች ብታደርግም ለቲያትር ተማሪ የሚሆን ሥራ ማግኘት አልቻለችም ነበር።

ዘፈን እንደምትችል ወይም ዘፋኝ መሆን እንደምትችል አንድም ቀን አስባ አታውቅም ነበር። በልጅነቷ ሰንበት ትምህርት ቤት ከመዘመርዋ ውጭ ምንም ዘፈን ሞክራ አታውቅም ነበር። የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ላይ የአንድ ኮርስ ማሟያ ላይ ስትዘፍን የተመለከታት መምህር ዘፋኝ መሆን እንደምትችል ይነግራታል። እሷ ግን አንድም ቀን ዘፋኝ የመሆን ህልም ኖራት እንደማያውቅ ትናጋራ ችላ ብላ ታልፈዋለች።

ከዚህ ሁሉ በኋላ የተቀላቀለችው የኛ የተሰኘው ሙዚቃዊ ድራማ ላይ ትልቅ ደመወዝ እየተከፈላት መሥራት ጀመረች። ግብርናን፤ ትያትር፤ ተምራ የኛ ሙዚቃዊ ድራማ ላይ ለስባት ዓመት ስትሠራ ሕዝቡ ልብ ውስጥ ለመግባት በርካታ ጥረት አድርጋለች። ከገፀ ባህሪዋ ጋር ለመዋሃድ ጎዳና ላይ ወጥታ የጎዳና ልጆች ሁኔታን እስከማጥናት ደርሳ እንደነበር ትናገራለች። ከሰባት ዓመታት በኋላ በእድሜም እየበሰለች ስትሄድ ራሷን ለመሆን ህልሟን ለማግኘት የተለያዩ ራስን ማሳደጊያ ሥልጠናዎች ትወስድ ነበር።

“ሴትነት የሚኖርበት መንገድ፤ ሴትነት የሚቀነቀንበት መንገድ ሁሉ ጥያቄ ይፈጥርብኛል” የምትለው ለምለም ሴትነት ከመጽሐፍ ቅዱሰ እይታ፤ ሴትነት ከሰዎች አስተሳሰበ አንፃር፤ በአጠቃላይ ከተለያዩ እይታዎች አንፃር ሲቃኝ በርካታ አተካራዎች ውስጥ ከውስጧ ጋር ብትገባም ሴት ወንድ ከሚል አስተሳሰብ ወጥታ ሰው መሆን በሚል አስተሳሰብ ራሷን ለመረዳት መታገል ጀመረች። የለምለምን የሕይወት ጥሪ ማወቅ፤ ለምለም ምን መክሊት እንዳላት ለመረዳት ጥረት ማድረግ ጀመረች። እራሷ ምን እንደምትፈልግ የእሷ መስመር የቱ እንደሆነ ለማጣራት ቆማ ውስጧን መመልከት ጀመረች።

በዚህ መካከል የኛ የተባለው ሙዚቃዊ ድራማ ለቀጣይ ሶስት ዓመታት ይቀጥላል እየተባለ ባልታሰበ ሁኔታ ፕሮጀክቱ ሲቋረጥ አስደንጋጭ ሁኔታ ውስጥ ገባች። በወቅቱ ዴይሊ ሜል የሚባል የእንግሊዝ ሀገር ጋዜጣ አምስት እስፓይስ ገርሎችን ለማቋቋም አምስት ሚሊየን ፓውንድ ወጣ ብሎ ዜና በመሥራቱ የተነሳ ምንም ቅድመ ሁኔታ ያልነበራቸው፤ የተሻለ ሕይወትን የተለማመዱ ወጣቶች እንዲበተኑ ሆነ።

በዚህም ምክንያት ከነበረችበት የሕይወት ደረጃ ዝቅ ማለት የግድ የሚል ወቅት መጣ። ከጥሩ ደመወዝ በድንገት የተነቀለችው ወጣት ኑሮን ዝቅ አድርጎ ለመኖር መልመድን እየሞከረች ነበር እናት የሆነችው። የመጀመሪያ ልጇን ከወለደች በኋላ ምንም ዓይነት ገቢ ሳይኖራት አጋሯ በሚያገኘው ገንዘብ ልጇንና እሷ በአነስተኛ ገቢ ለመኖር መታገል ጀመሩ። በወቅቱ አዲስ የእናትነት ልምምድ ውስጥ ገባች። እናት መሆን ብርቅ የሆነባት ወጣት ለአንድ ዓመት ከአምስት ወር ልጇን ብቻ እየተመለከተች አቅፋ መዋል ሥራዋ ሆነ።

ሙሉ ጊዜዋን ያለ ምንም እንቅስቃሴ ከልጇ ጋር የነበረችው ለምለም ክብደቷ ሰማንያ አራት ኪሎ ላይ ደረሰ፤ ከአዲስ እናትነት ጋር የሚመጣ ድባቴ ውስጥ ገብታ ደጅ መውጣት እስኪያሰጨንቃት ድረስ ቆይታ ነበር። ከዛ የሥነ ልቦና ባለሙያ በማነጋገር እራሷን በመቀበል ነገሮችን ማስተካከል እንደምትችል አመነች። ከሰማንያ አራት ኪሎ ወደ ሰባ ሁለት ለመውረድ ሁለት ወራትን ብቻ ነበር የፈጀባት። በመቀጠል የነበረቻትን መኪና ፍቃድ በማውጣት የትራንስፖርት አገልግሎት እንድትሰጥ አደረገቻት። የኢኮኖሚ ችግሮቿን በመቀነስ ቀስ በቀስ ወደ ቀደሞ አቋሟ መመለሷን ትናገራለች።

ከዛ በኋላ ገዳም የሚለውን ሙዚቃ ከአምስት ዓመታት በፊት ለቀቀች። በወቅቱ የየኛ ቡድን አባላት አብዛኞቹ ነጠላ ዜማቸውን ለቀው ስለነበር ያለምንም ችግር ገበያው ውስጥ ለመግባት አስችሏት ነበር። ነጠላ ዜማውም በወቅቱ ከፍተኛ የሚባል ሽያጭ ነበር ያስመዘገበው። ከእናትነት በኋላ ከዜሮ ተነስታ ከፍ ያለ ቦታ ደርሳለች።

ከነጠላ ዜማው በተጨማሪም ከጓደኞቿ አብሮ የሚሰራ ሥራ ላይ ትሳተፍ እንደነበርም ታስታውሳለች። ከነጠላ ዜማዎች ጎን ለጎን አልበም ለመሥራት ከኤሊያስ መልካ ጋር የተገናኘችበትም አጋጣሚ የሙዚቃ መስመሮች እንደዘረጋላት ትናገራለች። አሁን አልበም ጀምራ ዘጠኝ ዜማዎችን ሰርታለች። በቅርቡም ሙሉ አልበም እንደምታስመርቅ ትናግራለች።

“የሕይወት መስመሬን ባለማወቄ በተቀደደልኝ ቦይ ነበር የምፈሰው። አንድም ቀን የራሴን ግብ አስቀምጬ አላወቅም ነበር። የሕይወት ግቤ ጠፍቶ ራሴን ጥዬ የነበረም ሲሆን አሁን በሙዚቃ መስመር ውስጥ ተደላደዬ እየኖርኩ ነው።”

ሁለተኛ ልጄን ከወለደኩ በኋላ በርካታ ጫናዎች ላይ በነበርኩበት፤ ብዙ ነገር ሳልችል ቀርቼ የሚያስችል አምላክ እንዳለ ያየሁባት ቆንጆዋን ልጄን ማያ ብያታለሁ። ልጆች የራሳቸውን በረከት ይዘው ይመጣሉ የሚባለው እውነት ነው፤ ልጆች በረከቶች ናቸው። ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው።

የልጆቼ እናት ለመሆን አልበም አቁሜ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አስተዋዋቂ ለመሆን አስቤም ነበር። ሁለተኛ ልጄን ስወልድ ሙዚቃ መስማት አቁሜም ነበር። ግን ሁሌ ሙያ መቀያየር መፈለግ ውስጥ ተጠምጄ ቢሆንም እኔ የምችለው መዝፈን ነው። መክሊቴን ያወኩት በሰላሳ ምናምን ዓመት እድሜዬ ላይ ነው።

“ባህር ዳር ለመሄድ የሀዋሳ መኪና ተሳፍሬ የተንገላታሁ ሰው ነበርኩ። አሁን ግን ስኬታማ የሆኑ ሰዎችን መመልከት ማየት ማዳመጥ ጀመርኩ። ሰዎች ሙዚቃዬን ይወዱታል ሙዚቃዬ ለሰዎች ተደራሽ ይሆናል። የተሰጠኝ መክሊት ሙዚቃ ነው ብዬ አሁን አልበሜን ሰርቼ ለመጨረስ በቃሁ” ብላለች።

“እኔ የሄድኩበት መንገድ ከባድ የነበረ ቢሆንም፤ መወለዴ ከብዶኝ ነበረ ቢሆንም የእናትነት ኃላፊነት ከባድ ቢሆንም አልፈዋለሁ። እናትነትን በተገቢው መንገድ ችዬበታለሁ። እስከዛሬ ህልሜን ሳለውቅ ቆይቻለሁ፤ አሁን ህልሜን አውቄ ላሳይ ነው። አልበሜም በቅርቡ ይደርሳል፤ በእኔ ሕይወት መስመር ላይ ቆም ብዬ ስመለከት ካርጎዬን ስቼ ነበር። አሁን ሁሉ አልፏል ሙሉ ሴት ነኝ” ብላለች።

ዛሬ ስኬታም ዘፋኝ የሆነችው ይህች ሴት በበርካታ የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ማለፏን ስትናገር ማንም ሰው የሚወደውንና የሚፈልገውን መሥራት ከቻለ ለስኬት ቅርብ ነው የሚል መልእክት አስተላልፋለች እኛም በዚሁ መልእክቷ ተሰናብተናል። ቸር ይግጠመን።

አስመረት ብስራት

 አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You