መምህር ሀ/ሚካኤል ጸዳለማርያም ይባላሉ። በከሳቴ ብርሀን ሰላማ መንፈሳዊ ኮሌጅ የእብራይስጥና ሂብሩ መምህር ናቸው።
መምህሩ ከእለታት አንድ ቀን ከታደሙበት ትዕይንት ከወዳደቁ ብረቶች ተሰርቶ ድምፅ የሚያወጣ መሳሪያ ድንቃ ድንቅ ተብሎ ለእይታ ሲቀርብ ‘‘ከዚህ የበለጠ ድንቅ ሀብት አለን’’ በማለት የጥንት አባቶች እና ካህናት ለስብሰባ መጥሪያ፣ ለፀሎት ማንቂያ፣ ለቀብር ስነ-ስርዓት ማስፈፀሚያ፣ ለዋዜማ መቆሚያ እና መሰል ተግባራት ይጠቀሙባቸው የነበሩ ድንጋዮችን ለመሰብሰብ መነሳታቸውንና በዚህም ስራ በርካታ አመታትን ማሳለፋቸውን ይናገራሉ።
ድንጋዮቹ እንደማንኛውም አይነት ድንጋይ በቀላሉ የማይገኙና የተለየ ድምፅ የሚያወጡ ስለመሆናቸው የሚናገሩት መምህር ሀ/ሚካኤል ድንጋዮቹን ለመሰብሰብ ከብዙ አመታት በፊት ሀሳቡ ቢኖራቸውም ስራውን የጀመሩት ግን ከ15 አመታት ወዲህ መሆኑን ይገልፃሉ።
ድንጋዮቹን በመሰብሰብ ስራው የሌሎች የቤተክርስቲያን አባቶች እገዛም እንደነበር የሚናገሩት መምህሩ በተለይም ድንጋቹን ከቆላ ተምቤን እና ሳምሬ ገጠራማ አካባቢዎች ወደ አስፋልት መንገድ በማውጣት ለትራንስፖርት ምቹ ከማድረግ አንፃር የእነዚህ አባቶች ድርሻ ከፍተኛ ነበር ይላሉ።
ድንጋዮቹን ለመምረጥ ካህናቱ የእያንዳንዱን ድንጋይ ድምፅ በጥልቀት እንደመረመሩና በዚህም 60 ገደማ ድንጋዮች ተገኝተው ተሰብስበው ሀብቶቹ የበለጠ ስራ እንዲሰራባውና ምርምሮች እንዲደረጉባቸው በማሰብ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተነጋግረው ወደ ዩኒቨርሲቲው እንዲመጡ ተደርገዋል።
በዩኒቨርሲቲው አምስት አመታትን ያስቆጠሩት እነዚህ ድንጋዮች ድምጻቸውን መሰረት ያደረገ ቅኝት እና ቅንብር ያስፈልጋቸው ስለነበር ይህንን ስራ ሊሰራ የሚችል ባለሙያ ማግኘት ደግሞ ፈተና ይሆናል።
ይሁን እንጂ እነዚህ ድንቅ ድንጋዮች የሚያወጡትን ድምፅ ዲያቆን ይስሀቅ ሀ/ማርያም ከመምህር ሀ/ሚካኤል እና ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ መምህራን ጋር በመሆን በወጉ ደርድሮ ከዜማ አዋዶ ለጆሮ እንዲጥም አድርጎ ቃኝቷቸዋል።
አምስተኛው ሀገር አቀፍ የግዕዝ ጉባኤ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ከሰኔ 1-2/2011 ዓ.ም በተካሄደበት ወቅት እነዚህ ድንቅ ድንጋዮች በወግ ተሰድረው በዋናነት የአንቺ ሆየ ቅኝትን በዜማ ለመጀመሪያ ጊዜ ለታዳሚያን በማስደመጥ አግራሞትን ፈጥረዋል።
ድንጋዮቹ ለጊዜው ለአንቺ ሆዬ ቅኝት እንዲሆኑ ተደርገው ይደርደሩ እንጂ ሁሉንም የኢትዮጵያ የዜማ ቅኝቶች ጨምሮ በባለሙያዎች አጠራር ‘‘ፔንታቶኒክ’’ እና ‘‘ዳያቶኒክ’’ የሚባሉትን የውጪ ቅኝቶችንም መጫወት እንደሚያስችሉ ዲያቆን ይስሀቅ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል።
ድንጋዮቹ ሌሎች ምርምሮች ተጨምሮባቸውና የሚመለከታቸው አካላትም ተሳትፈውበት ትልቅ አገራዊ ሀብት እንዲሆኑና በአለም አቀፍ ደረጃ እንዲተዋወቁ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን በመጥቀስም፣ ለዚህም ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋርም በጋራ ለመስራት ስራዎች መጀመራቸውን ዲያቆን ይስሀቅ ይገልጻል።
የድንጋዮቹን ክብደት በመቀነስና ወጥ ቅርፅ እንዲኖራቸው በማድረግ ለመንፈሳዊ እና ዘመናዊ ሙዚቃ መሳሪያነት እንዲያገለግሉ፣ እውቅና እንዲያገኙና በንብረትነትም እንዲመዘገቡ ለማድረግ በቅርቡ ስራ እንደሚጀመርም ለማወቅ ችለናል።
እስከአሁን በየትኛውም የአለም ክፍል እነዚህን ድንጋዮች የመሰለ ሀብት አለመኖሩ የሚነገር ሲሆን በዘመናዊ መልክ ተሰርተው ለአለም ቢተዋወቁ የሀገራችንን የሙዚቃ ታሪክ ይበልጥ የሚያስተዋውቁና ትኩረት መሳብ የሚችሉበት እድል ስለሚኖር የሚመለከተው አካል ሁሉ በዚህ ስራ እንዲሳተፍ መምህር ሀ/ሚካኤል እና ዲያቆን ይስሀቅ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2011
በድልነሳ ምንውየለት