አዲስ አበባ፡- በሀገሪቱ ተንሰራፍቶ የቆየው ሙስና እና የሀብት ብክነት በመንግሥት መፍትሄ ባላገኘበትና ኢኮኖሚው በህግና ፖሊሲ መምራት ውስጥ ባልገባበት ሁኔታ ግዙፎቹ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ባለሀብቱ መዘዋወር እንደሌለባቸው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ (አብን) አስታወቀ።
የፓርቲው የኢኮኖሚ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ካሱ ኃይሉ ለጋዜጠኞች ትናንት በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ከመዛወራቸው በፊት ገዢው ፓርቲ ሀገር የሚመራበትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስር ነቀል ለውጥ የሚያመጣ ማድረግ፣ ለውድድር ክፍትና ጠንካራ ተፎካካሪ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መገንባት እንዲሁም ጠንካራ የማስተዳደር አቅምን መፍጠር አለበት።ተንሰራፍቶ የቆየውን ብልሹ አሰራርንም ሊያርም ይገባል።
‹‹የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም እያሽቆለቆለ ባለበት በዚህ ወቅት እነዚህ ተቋማት መዘዋወር አይገባቸውም፡፡›› ያሉት አቶ ካሱ፤ በተለይም እንደ ኢትዮ ቴሌኮም አይነቶችን በውድድርና በህግ አግባብ ሳይመሩ ለሽያጭ ማቅረብ ተገቢነትና ጊዜውን የጠበቀ እንደማይሆን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ይህ ከሆነ ግን በመንግሥት ሽፋን ባለፉት ጊዜያት ለግሉ ዘርፍ እንደተከፋፈሉት አይነት መሆኑ አይቀርም፡፡›› ብለዋል።
የፓርቲው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መልካሙ ሹምዬ በበኩላቸው፤ ‹‹መንግሥት ግዙፍ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ለማን ማስተላለፍ እንዳለበትም በሚገባ አላወቀም፡፡›› ብለዋል። ለአብነትም ‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድን ያለምንም ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ለማስተላለፍ መነሳቱ ተገቢነት የሌለውና ለዝርፊያ ራስን ማመቻቸት ነው፡፡›› ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ አቶ መልካሙ ማብራሪያ፤ እስካሁን ባለው ጊዜ ውስጥ አየር መንገዱ በአማካኝ ከስምንት በመቶ በላይ ትርፍ ያመጣል። ይህም አለም ላይ አሉ ከሚባሉ ሰባት የአሜሪካ አየር መንገዶች ከሚያስመዘግቡት 4 ነጥብ 9 በመቶ የትርፍ ህዳግ በእጥፍ የሚበልጥም ነው። ስለሆነም ለምን አይነት ትርፍ እንደሚሸጥና እንደሚተላለፍ አይታወቅም።
አየር መንገዱ በአንድ መንገደኛ የሚያገኘው የዶላር መጠን ከአውሮፓና አሜሪካ አየር መንገድ የበለጠ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ መልካሙ፤ የአየር መንገዱ እዳ ከጠቅላላ ሀብቱ የሚያንስ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ አየር መንገዱን ለመሸጥ የሚያስገድድ ነገር እንደሌለ ያደረጉትን ጥናት በመጥቀስ ተናግረዋል።
አየር መንገዱ ካለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባሻገር ወደብ አልባ ለሆነች አገር ብቸኛ ወደብ ሆኖ የሚያገለግል ሆኖ ሳለ አሳልፎ ለመሸጥ መሞከሩ ሉአላዊነትን የሚፈታተን መሆኑን ገልጸዋል።
የስትራቴጂክ ጉዳይ ዘርፍ ኃላፊው አቶ የሱፍ ኢብራሂም፤ በመንግሥት በኩል ምንም የተጠናከረ አመራርና አስተዳደር አለ ለማለት እንደማያስደፍር ጠቅሰው፤‹‹እነዚህን ግዙፍ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችና ፕሮጀክቶች ለግል ባለሀብቱ ማዘዋወር አገር ከመሸጥ አይተናነስምና መጀመሪያ ትክክለኛ አስተዳደር ይፈጠር፡፡›› ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው