አዲስ አበባ፡- ኢትዮ ቴሌኮም በቅርቡ ያደረገውን የዋጋ ማሻሻያ ተከትሎ ሶስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዜጎች የኢንተርኔት ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታወቀ።
በኢትዮ ቴሌኮም የዋና ስራ አስፈፃሚ ጽህፈት ቤት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሪት ጨረራ አክሊሉ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ የህዝቡን አጠቃላይ አቅም ከግምት በማስገባት በተደረገው የታሪፍ ማስተካከያ ሶስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዜጎች የኢንተርኔት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። በአሁኑ ወቅትም በሀገሪቱ በአጠቃላይ ሃያ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዜጎች የኢንተርኔት አገልግሎትን እየተጠቀሙ ይገኛሉ።
‹‹ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዝቅተኛ የኢንተርኔት አገልግሎት ከሚያቀርቡ ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡›› ያሉት ኃላፊዋ ‹‹በቅርቡ የአፍሪካ ሀገራትን የኢንተርኔት አቅርቦት በተመለከተ የወጣ ሪፖርት አገራቱን በሶስት ደረጃ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በመካከለኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡›› ብለዋል። ይህም ሆኖ ተቋሙ ከአርባ እስከ ሀምሳ በመቶ የሚደርስ የታሪፍ ማሻሻያና በአለም አቀፍ ጥሪዎች እንዲሁም ፓኬጅ ገዝተው ለሚጠቀሙም ማስተካከያ ካደረገ አመት የማይሞላው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እንደ ኃላፊዋ ገለፃ፤ በአፍሪካ እንደ ሱዳን ያሉ ዝቅተኛ ክፍያ የሚያስከፍሉ ሀገራት ቢኖሩም፤ እነሱ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚያቀርቡት በራሳቸው ነው። ኢትዮጵያ ግን የኢንተርኔት አገልግሎት የምታገኘው ከጅቡቲና ኬንያ ነው፤ በመሆኑም ለቀጣይ የሚስተካከሉ ነገሮች ካሉ ለመፍታት ከሀገራቱ ጋር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አሉ። ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም ዋጋውን ተመጣጣኝ በማድረግ ተደራሽነትና ጥራቱን ለማስተካከል አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ማስተካከያ መደረግ ካለበት የሚታይ ይሆናል።
ተቋሙ በበጀት አመቱ ከሰበሰበው ገቢ የትርፍ ትርፍ አራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን፤ ግብር ደግሞ ሰባት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ለመንግስት ገቢ ማድረጉንም ወይዘሪት ጨረራ ጨምረው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ