አዲስ አበባ፡- አሁን ያለው አመራር ሰብዓዊ መብትን የሚጋፉ አካላትን እንደማይታገስ መገንዘብ እንደሚያስፈልግ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የብሄራዊ ሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሐግብር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ገለፁ፡፡ለውጡ በታራሚዎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም ማስቻሉን የቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት ገለጸ፡፡
ኃላፊው አቶ ይበቃል ግዛው በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ የታራሚዎቹ ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ ጠቅላይ ዓቃቤ ህጉ ከማረሚያ ቤት አመራሮች ጋር ተቀራርቦ እየሰራ ነው፡፡ አመራሩም የታራሚውን ሰብዓዊ መብት የሚጥሱ አካላትን አይታገስም፡፡
ከለውጡ በኋላ የተደረገው ምዝና የማረሚያ ቤቶች የሰብአዊ መብት አያያዝ ከበፊቱ ጋር ሲተያይ ተጨባጭ ለውጥ የመጣበት መሆኑን እንደሚያመለክት ጠቅሰው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ታራሚዎቹም እውቅና መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡ ታራሚዎች ከግብዓት አቅርቦት፣ ከመኝታ፣ ከንፅህና፣ ከህክምና እና ከመሳሰሉት ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በእስር ቤት በሚያደርጉት ቆይታ ብዙ መሰረታዊ መብቶች እንዳሏቸው ተናግረው፣ይህ ለውጥ ተገኝቷል በሚል መዘናጋት እንደማያስፈልግ አቶ ይበቃል አስገንዝበዋል፡፡ በሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ በመጣው ለውጥ መኩራራት እንደማይገባና ቀሪ የቤት ስራዎች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡
አሁንም ታራሚዎችን ለመማታት የሚዳዳቸው የህግ አስከባሪ አባላት ሊኖሩ እንደሚችሉ የጠቀሱት ኃላፊው፤ ይህም ተገቢ ድርጊት ስለአለመሆኑ የጊዜው መምከር እንዲሁም በሰብዓዊ መብት መርሆዎች ላይ የጠለቀ እውቀት እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡
በሰብዓዊ መብት አያያዝ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን የተጠያቂነት ስርዓት እየተገነባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት ዋና አስተዳዳሪ ኮማንደር ተክሉ ለታ በማረሚያ ቤቱ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ሰዎች ይታሰሩ እንደነበር እንዲሁም የማረሚያ ቤት አባላት የማያውቋቸው ድብቅ በሆነ መልኩ የሚታሰሩ ሰዎችም እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡
‹‹በተጨማሪም ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዘ በርካታ የመብት ጥሰቶች በማረሚያ ቤቱ አባላት አማካይነት ይፈጸሙ ነበር፡፡ ማረሚያ ቤቱ ይታይ የነበረውም እንደ ማረሚያ ቤት ሳይሆን እንደ ምስጢር ጠባቂ ተቋም ነበር›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለውጡ እነዚህና መሰል የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳይኖሩ ማድረጉን ኮማንደሩ ጠቅሰው፣ አንድ ሰው ወደ ማረሚያ ቤት የሚላከውም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ስለታራሚውም ሆነ ስለተቋሙ መረጃ የሚፈልግ መገናኛ ብዙሃን በማንኛውም ሰዓት ተገኝቶ መረጃ የማግኘት ነፃነቱ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡
አንድ ታራሚ ሊታረም የመጣው አጥፍቶ ነው በሚል የታራሚውን መብት መጣስ አግባብ አለመሆኑን ጠቅሰው፣ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል ሁኔታ ታራሚውና ማረሚያ ቤቱ በአሁኑ ወቅት ያላቸው ቅርርብ መልካም የሚባል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት ያሉ ታራሚዎች ወደ ሶስት ሺ ያህል ሲሆኑ፣ የሴት ታራሚዎች ቁጥር ወደ 480፣ የወንዶች ደግሞ 2 ሺ 873 አካባቢ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2011
አስቴር ኤልያስ