ደጋግማ ትንጠራራለች፤ እንደ ማፋሸክም ያደርጋታል፡፡ ቀረብ ብለን ‹‹ምን ሆነሽ ነው?›› ስንላት የአስረኛ ክፍል የሂሳብ ፈተናን ለመፈተን ሶስት ሰዓት ሙሉ በመቀመጧ ደከሟት እንደሆነ ነገረችን – ተማሪ አበባ ኪሮስ።
ተማሪ አበባ፣ የኮከበ ጽባህ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የአስረኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ ሰሞኑን ስትዘጋጅ የሰነበተችበትን ፈተና እንዲህ ትገልጻለች። ‹‹ዓመቱን ሙሉ ሳጠና ብቆይም ይከብደኛል ብዬ ፈርቼ ነበር። ግን የሰጋሁትን ያህል አዳጋች ሆኖ አላገኘሁትም። በተለይ በትምህርት ቤታችን አማካይነት ስለፈተናው የተደረገልን አጠቃላይ ገለጻ ፈተናውን ቀለል አድርጌ እንድመለከት ረድቶኛል። መብራት መጥፋቱ ግን ችግር ነበር፡፡ በተለይ ከመስኮቱ ርቀን ለተቀመጥነው ደንገዝገዝ ያለ ብርሃን ሲሆን፣ የመስኮቱ ብርሃን ስለማይደርሰን ትንሽ አስቸግሮን ነበር፡፡›› ስትል ተናግራለች።
በተመሳሳይ የደንብ ልብሱን እያስተካከለ ሲወጣ ያገኘነው ተማሪ ደጀን ሀይሉ መብራት ቢጠፋም መምህራን መስኮትን እየከፈቱና ቦታ እያስተካከሉላቸው ስለተባበሯቸው በሰላም መፈተናቸውን ይናገራል። ‹‹ዘንድሮ ጥብቅ ነው፤ በጣም ይቆጣጠራሉ፡፡ ለመኮረጅ አስቦ የመጣ ካለ ከስሯል።
እኛ በትምህርት ላይ እያለን ዘንድሮ ጥብቅ ቁጥጥር ስለሚደረግ ተጠንቀቁ ብለው መምህራን ስለነገሩን አብዛኞቻችን ተዘጋጅተናል።›› ሲል ተናግሮ፤ ‹‹በዚህ መንገድ ፈተናው መቀጠል አለበት፤ ማንም ሰው በሰራው ልክ ነው ውጤት ማግኘት የሚገባው። የመጀመሪያውን ቀን በሰላም እንደጨረስን ሁሉ ለቀሪዎቹ ሁለቱም ቀናት በተመሳሳይ መልኩ በሰላም እናጠናቅቃለን፡፡›› ሲል ያለውን ተስፋ ተናግሯል።
የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር አቶ ዮሀንስ አሰፋ በበኩላቸው፤ አስፈላጊው ዝግጅት በቅድሚያ በመደረጉ ፈተናው በታቀደው መሰረት እየተከናወነ እንደሆነ ይናገራሉ። አክለውም፤ ትምህርት ቤቱ በትናንትናው እለት 846 ተማሪዎችን ሲፈትን እንደዋለ ያብራራሉ፡፡
እንደ ርዕሰ መምህሩ ገለፃ፤ ትምህርት ቤቱ አጠቃላይ በሁለቱም የአስረኛና አስራ ሁለተኛ ክፍል ፈተናዎች 1ሺ970 ተማሪዎችን የሚፈትን ይሆናል። በቂ ፈታኞችና የፈተና ክፍልም ተዘጋጅቷል። በእያንዳንዱ ከፍል አንድ ዋና እና አንድ ረዳት ፈታኝ ተመድቧል፡፡ ዘንድሮ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን መምህራንም ምንም አይነት ስልክና የሂሳብ መሳሪያ ማሽን ይዘው እንዳይገቡም በመደረጉ ኩረጃ የመፈጠሩ እድሉ በጣም ጠባብ ነው።
የእለቱን ዝግጅት የጀመርነው ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ነበር፤ አስራ አንድ ሰዓት ፈተናው ትምህርት ቤት እንዲገባ ተደርጎ ተቆልፎ አንግቷል። የየካ ክፍለ ከተማ ኮማንድ ፖስትና የትምህርት ቤቱ ኮማንድ ፖስት እንዲህም የጸጥታ ሀይል ባለበት ፈተናው ወጥቶ ክፍሉ ተመልሶ ታሽጎ በመሀከል ሁለት ፖሊሶች ሲጠብቁ ውለዋል። ቀጣዮቹም ፈተናዎች በተመሳሳይ የሚቀጥሉ ይሆናል።
‹‹ያረፈደም የቀረም ፈታኝ አልገጠመንም። አንድ ተማሪ ምክንያቱ ባይታወቅም በፈተና ገበታው ላይ አልተገኘም። በሚቀጥሉትም ቀን በዚህ ሁኔታ ለመቀጠል አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል›› ሲሉም ርዕሰ መምህሩ ተናግረዋል። አንዲት ልጅ ራሷን መሳት ገጥሟት ወድቃ የነበረ ቢሆንም፤ ለዚህ ተዘጋጅቶ በነበረው አንድ አምቦላንስና ሁለት የጤና ባለሙያዎች ህክምና ተደርጎላት ፈተናዋን ለመቀጠል በቅታለች።
የቦሌ መሰናዶ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር አቶ ዳንኤል መኮንን በበኩላቸው፤ በትናንትናው እለት የግል ተፈታኞችና ከግል ትምህርት ቤት እንዲሁም የቦሌ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ጨምሮ ከአንድ ሺ 153 በላይ ተማሪዎችን በሰላም ሲፈትን መዋሉን ይናገራሉ።
ከሶስት ቀን በኋላ የመሰናዶ ፈተናን የሚፈተኑ ከ1ሺ 400 በላይ ተማሪዎች ያሉ ሲሆን፣ ለእነሱም በቂ ዝግጅት እንደተደረገ ገልጸዋል። ‹‹ከቀናት በፊት ከተማሪዎች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ አስፈላጊው ፍተሻና ጥበቃም እየተደረገ ነው፡፡›› ያሉት ርእሰ መምህሩ፣ አንዲት አራስ ከነሞግዚቷ በመምጣት ለብቻ እንድትፈተን መደረጉን በመግለጽ፤ የመብራቱ ነገር ግን ያው ተፅዕኖ በመፍጠሩ ጨልሞ ውሏል፡፡ ለሁሉም የሚበቃ ጀነሬተር የለም፤ ቢኖርም ጀነሬተር ከፍቶ ፈተና መፈተን አስቸጋሪ ነው፡፡›› ሲሉ የዕለቱን የፈተና ውሎ ተናግረዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ ሀረጓ ማሞ በበኩላቸው፤ ትምህርት ሚኒስቴር ከአገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ ጋር በመሆን በፌዴራል በኩል የተለያዩ አደረጃጀቶች ፈጥረው በጋራ ሲዘጋጁ መቆየታቸውን ይናገራሉ።በዛሬው እለትም መስቃን ወረዳ መሰረተ ወገራ በምትባል የፈተና ጣቢያ አርባ ሶስት ተማሪዎች ከወቅታዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ፈተና ገበታ ላይ ካለመቀመጣቸው ውጪ ከሌላው ጊዜ በተሻለ በሁሉም ጣቢያ ተማሪዎች የዕለቱን ፈተና በሰላም ተፈትነው መጨረሳቸውን ያመለክታሉ፡፡ ቀሪዎቹም ቀናት በዚሁ መሰረት የሚሄዱ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
‹‹ክረምት ከመሆኑና ሀገር አቀፍ ችግር እንደመሆኑ የመብራት መቆራረጥ ሊገጥም ይችላል፤ ይሄ ግን በጣም ችግር ያለባቸው ተማሪዎች ካሉ እዛው በፈታኞች አስፈላጊው ድጋፍ ስለሚደረግ ያን ያህል አሳሳቢ አይደለም፡፡›› ያሉት ዳይሬክተሯ፤ የፈተና ሂደቱን በየወቅቱ የሚከታተሉ እንደሆነ በመግለጽ በትናንትናው እለትም ሚኒስትሩ ባሉበት የመንግስት ትምህርት ቤትና የግል ተፈታኞች የሚፈተኑበት ጣቢያ ጎብኝት መደረጉን ጠቁመዋል። በዘንድሮ አመት አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ሀገር አቀፍ ፈተናውን እንደሚወስዱም ዳይሬክተሯ ጨምረው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ