የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ገነት ደጉ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ የሚታዩ ግጭቶች መነሻቸው ቀላል እንደሆነ ጠቅሰው፣ወደ ከፋ ግጭት የሚያመሩ መሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡
ቀደም ሲል ከሚታዩ የተለመዱ የተማሪዎች ግርግሮችና ጩኸቶችም የተለየ ገፅታ መላበሳቸውን ነው የሚናገሩት፡፡ እንዲህ አይነቱን ግጭት ለሚፈልጉ የውጪ ሃይሎች ደግሞ ብሄር ተኮር ግጭትም ይመስላሉ፡፡ ከዚህ አኳያ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ግጭትና ሁከት እንዲፈጠሩ የሚፈልጉ ሃይሎች እንዳሉ ይታሰባል፡፡
ባለፈው ህዳር ወር በዩኒቨርሲቲው ግጭት መከሰቱን አስታውሰው፣ ግጭቱን በቀላሉ ለማብረድ መቻሉንም ነው የተናገሩት፡፡ በቅርቡ በዩኒቨርሲቲው የተከሰተውን ግጭት ለማስቆም የፀጥታ ሃይል እንዲገባ በማድረግ የሌሎች ተማሪዎች ደህንነት እንዲጠበቅ ማድረግ ተችሏል ይላሉ። በተመሳሳይም የከተማ አስተዳደሩ የሃይማኖት አባቶች፣ሽማግሌዎችና የከተማው ህዝብ በጋራ ድርጊቱን በማውገዝ ሌሎች ተማሪዎች ያለስጋት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማድረግ መሰራቱን ይጠቅሳሉ፡፡
ከግጭቱ በኋላ መረጋጋት በመፈጠሩ በአሁኑ ወቅት ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እየተከታተሉ እንደሚገኙ የሚገልፁት ፕሬዚዳንቷ፤ በቀጣይ ተመሳሳይ ግጭቶች እንዳይፈጠሩ በዩኒቨርሲቲው በኩል ከወዲሁ በርካታ ስራዎች መሰራት ይኖርባቸዋል ይላሉ፡፡
እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቷ ገለጻ፤ለውጡን ተከትሎ ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ የተለያዩ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖችና አክቲቪስቶች ተማሪዎችን በክረምት ወቅት እንደልብ ስለሚያገኟቸው ተማሪዎች ወደግጭት እንዳይገቡ ሰብስቦ መምከር ይገባል፡፡
እንደ ሃገርም በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በጥልቀት መሰራትይኖርበታል የሚሉት ምክትል ፕሬዚዳንቷ፣ ተማሪዎችም በክረምት ወቅት በበጎ ፍቃድና በማህበራዊ አገልግሎት ስራዎች ላይ ተሳታፊ በመሆን ከማህበረሰቡ ጋር ቅርርብ መፍጠር እንደሚገባቸው ይጠቁማሉ። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም አገልግሎት አሰጣጣቸውን በየጊዜው ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል ይላሉ፡፡
የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ወሮታው ሞትባይኖር፤ በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲው ለሚታዩ ግጭቶች መንስኤዎቻቸው የዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ብቻ ሳይሆኑ ከግቢ ውጪ ያሉ ሀይሎችም መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡እነዚህ ሀይሎች ተማሪዎችን ለግጭት መሳሪያነት በቀላሉ ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉ ጠቅሰው፣በዚህ የተነሳም ግጭቶች በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ በብዛት ይፈጠራሉ ይላሉ፡፡
አቶ ወረታው እንደሚሉት ፤በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ግጭቶች እንዳይከሰቱ ተማሪዎች እርስበርስ ተቀራርበው ውይይት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህም ተማሪዎች ችግሮቻቸውን በማንሳት ለችግሮቻቸው መፍትሄ እንዲያበጁ ያስችላቸዋል፡፡ ጥፋተኛ ተማሪዎች ካሉም ጥፋታቸውን አምነው ዳግም ስህተት እንዳይሰሩ ይገድባቸዋል፡፡ ፀጥታ የማስከበርና የማረጋጋት ስራው እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያዊነት ላይ የሚያቀነቅኑና የተሻለ ተቀባይነት ያላቸውን ሰዎች በመጋበዝ ተማሪዎች ወደ ግጭት እንዳያመሩ ውይይት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
መጪው ክረምት በመሆኑና ተማሪዎች እረፍት የሚወጡበት ጊዜ በመቃረቡ በተለይ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ሊመክሩ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት። የአክሱም ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኪሮስ ጉኡሽ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ የሚታዩ ግጭቶች በአሁኑ ወቅት የሚታየው የአገራዊ አለመረጋጋት ነፅብራቅ ናቸው፤ ለብቻቸው ተነጥለው የሚታዩ አይደሉም ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ግጭቶቹን ለብቻቸው ማስቀረት የማይቻል መሆኑን ጠቅሰው፣ ሀገራዊ ችግሮቹን መፍታት እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ፡፡
በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የተከሰተውን ግጭት ለማርገብ ከተማሪዎች፣ከተለያዩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ውይይቶች መካሄዳቸውን ጠቅሰው፣በዚህም ተማሪዎችም ትምህርታቸውን በተረጋጋ መልኩ መከታተል እንደጀመሩ ነው የገለጹት፡፡ በቀጣይም ተመሳሳይ ውይይቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው፣ አጥፊዎችንም ለህግ የማቅረብ ስራዎች ጎን ለጎን መከናወናቸውን ይጠቁማሉ፡፡ ከአጥፊዎች ጎን በመሆን እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ ተማሪዎችንም የመምከር ስራዎች ተሰርተዋል ይላሉ፡፡
እንደ ዶክተር ኪሮስ ገለጻ፤ዩኒቨርሲቲዎች የእውቀትና የሃሳብ ማእከል እንደመሆናቸው መጠን ተማሪዎች ወደተሳሳተ አቅጣጫ እንዳይሄዱ ማስረዳትና ግንዛቤ መስጠት ይጠበቅባቸዋል። ግጭትን በግጭት መፍታት የማይገባ በመሆኑ እንደሃገር ውይይቶችን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ተማሪዎች ፍላጎታቸውን በሃይል ከመጠየቅ ይልቅ በሃሳብና በምርምር መጠየቅ እንደሚኖርባቸው ጠቅሰው፣መንግስትም ፀጥታ የማስከበር አቅሙን ከፍ ማድረግና የህግ የበላይነትን ማስከበር እንደሚጠበቅበት፣ ዩኒቨርሲቲዎችም ተማሪዎቻቸውን በሚገባ ማነፅና ማስተማር እንደሚኖርባቸው ያስገነዝባሉ፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2011
አስናቀ ፀጋዬ