ቅጥር ግቢው ሰፊ ነው፤ወደስፍራው የደረስነው ከምሳ በፊት ባለው የሻይ ሰዓት እንደመሆኑ ሰዎች ወዲህና ወዲያ ይላሉ፡፡ከእነዚህ ሰዎች መካከል የፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ ይገኛሉ፡ ፡ከሁሉም ጎልተው የሚታዩት ግን ቀያይ ልብስ የለበሱት ናቸው፤ታራሚዎች፡፡እነርሱም ከርቀት የሚመለከታቸውን አካል ትኩረት ይስባሉ፡፡
በታራሚዎቹና በማረሚያ ቤቱ ፖሊስ መካከል በጎሪጥ የመተያየት ነገር አለመኖሩን እንዲሁ አይቶ መረዳት ይቻላል፡፡አንዷን ታራሚ ልናነጋግራቸው ተጠጋን፡፡ለምን እንደታሰሩ በቅድሚያ ጠየቅናቸው፡ ፡ከገጽታቸው ላይ አንዳች መከፋት እንዳለባቸው መረዳት ይቻላል፡፡
እኚህ እናት ወይዘሮ ሰናይት መገርሳ ይባላሉ፡ ፡እምባ ባቆረዘዙ አይናቸው ‹‹ስንቅ የሌለው ቼክ በመፈረም ጥፋተኛ ነሽ ተብዬ 25 ዓመት ተፈርዶብኝ እዚህ እገኛለሁ›› አሉ፡፡ በቼክ ማጭበርበር ወንጀል 25 ዓመት በእስራት መቀጣት ተሰምቶም ታይቶም አይታወቅም›› ሲሉ አብራሩልኝ፡፡
‹‹አባታቸውን በሞት ከተነጠቁትና ሳላውቃቸው ካደጉት ልጆቼ ጎን እንድሆን ምኞቴ ነው ›› ያሉት ወይዘሮ ሰናይት፣‹‹ብዙ እህቶቼ በእስር ላይ በመቆየታቸው ሳቢያ የመውለድ ጊዜያቸው እያለፈ በመሆኑ ተስፋ ቆርጠው ተቀምጠዋል፡፡››ሲሉም ሌሎች ታራሚዎችም ያላቸውን ተቆርቋሪነት ይናገራሉ፡፡
‹‹ሰብዓዊ መብት ረገጣ ሲባል ጭንገፋም ሰብዓዊ መብት ረገጣ ነው፡፡ወደ ማረሚያ ቤቱ የገቡ ሴቶች በአሁኑ ወቅት የማግቢያና የመውለጃ ጊዜ እያለፈባቸው ይገኛል፡፡››ያሉት ወይዘሮ ሰናይት፣በእርግጥ ሴት ስታጠፋ አትታረም፤አትቀጣ ማለት አይደለም ይላሉ፡፡
ቅጣቱ ተፈጥሮን ያገናዘበ ቢሆን መልካም እንደሆነም ጠቅሰው፣ ሴት የመውለጃ ጊዜዋ ሳይተላለፍ ዘር መተካት የምትችልበት እድል ይኖራት ዘንድ የእስር ቅጣቷ ተፈጥሮን ያገናዘበ ሊሆን ይገባል ሲሉም ያስገነዝባሉ፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት የሚዲያ ነፃነት አለ፤ተቋሙ ለሚዲያ ክፍት ነው፤ከአመራር ጋር በግልፅ መነጋገር ተችሏል፡፡ መቶ በመቶ በሚያስብል ሁኔታ ነፃነቱ አለ፡፡›› የሚሉት ታራሚዋ፣አንድ ታራሚ ኮማንደሯን ላነጋግርሽ እፈልጋለሁ ብሎ ካላት ያለአንዳች ማንገራገር ታነጋግራለች፡፡ ሲሉም ይገልጻሉ፡፡
‹‹የመማር ነፃነቱ በሰፊው አለ፤ቀደም ሲል የሞት ፍርደኞች፣የፖለቲካ እስረኞች እንዲሁም እድሜ ልክ ፍርደኞች ወጥተው የመማር ፈቃድ አያገኙም ነበር፡፡አሁን እየተማሩ ናቸው ፡፡ይህ የለውጡ አካል ነው፡፡ይላሉ፡፡
ሌላዋ ታራሚ ወይዘሮ አንቺቱ ፍትህአወቅ ማረሚያ ቤት የገቡት ወደ ውጭ አገር በህገ ወጥ መንገድ ከላኳቸው ልጆች መካከል አንዷ የባለቤታቸው አክስት ልጅ በመጥፋቷ ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡የቀረበባቸው ክስ ሊያስፈርድ የሚገባው ጣራው አምስት ዓመት መሆኑን የሚጠቅሱት ታራሚዋ፣ፍርድ ቤቱ 17 ዓመት ከሰባት ወር እንደፈረደባቸውም ይገልጻሉ፡፡
‹‹እስር ለሴት ልጅ በጣም ይከብዳል፡፡››የሚሉት ወይዘሮ አንቺቱ፣‹‹እኔስ ወደ ማረፊያ ቤቱ ወልጄ ነው የገባሁት፤ከእኔ በፊት የገቡና 16 ዓመትና ከዛ በላይ ጊዜያቸውን በእስር እያቃጠሉ ያሉ እህቶቻችን ግን ዙሪያው ገደል ሆኖባቸዋል፡፡››ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡ እነዚህ ታራሚዎች ሳያገቡና ሳይወልዱ ወዘናቸውን በማረሚያ ቤቱ ያሟጠጡ በመሆናቸውም ተስፋቸው ተሟጧል፤ አንደበታቸውንም የሞላው ምሬት ሆኗልና ወዴት አቤት ይባል፡፡›› ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡
ታራሚዋ እንደሚሉት፤በነፍስ ማጥፋትም ሆነ በሌላ ምክንያት ወንጀል ድንገት ሊከሰት ይችላል፡፡ይሁንና በማረሚያ ቤት ረጅም ጊዜ በሚደረግ ቆይታ ብቻ ሳይሆን በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ሰው ሊታረም ይችላልና በተለይ ለሴቶች ተፈጥሮን ያገናዘበ የእስር ጊዜ እንዲኖር ቢደረግ በማረሚያ ቤቱ እየታረሙ ያሉ ተስፋ የቆረጡ ሴቶችን መታደግ ይቻላል፡፡
‹‹እኔ የወለድኩ፣አያት መሆንም የቻልኩ እንደመሆኔ መተካካት ቢኖር ኖሮ እኔ ታስሬ ያላገቡና ያልወለዱ ታራሚዎች ቢወጡ ያለማቅማማት እተካቸው ነበር፡፡›› ሲሉም የችግሩን ግዝፈት ገልጸውታል፡፡
የማረሚያ ቤቱ የታራሚዎች አያያዝ መልካም መሆኑን ጠቅሰው፣የተለያዩ ሙያዎችንም መማራቸውን ይገልጻሉ፡፡ከማረሚያ ቤቱ አመራሮች ጋርም ቤተሰባዊ ቀረቤታ እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡
የቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት አስተዳዳሪ ኮማንደር ተክሉ ለታ የሴቶች ማረሚያ ቤት ራሱን የቻለ አስተዳደር እንዳለው ጠቅሰው፤ከመውለድ እድሜያቸው ጋር ተያይዞ ሴት ታራሚዎች ይህን ጥያቄ ደጋግመው እንደሚያነሱ ይገልጻሉ፡፡ በቅርቡ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ማረሚያ ቤቱን በጎበኙበት ወቅትም ጥያቄውን ሴት ታራሚዎች ማንሳታቸውን ተናግረዋል፡፡
ኮማንደር ተክሉ፣በዚህ ዙሪያ እድሜን ያገናዘበ እስር በሚል ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፤የችግሩን ግዝፈት በመረዳት ደግሞ ማረሚያ ቤት እያሉ የትዳር አጋሮቻቸውን የሚያገኙበት ሁኔታ ቢመቻች የሚል ሰፊ ውይይት እንደተደረገም ያስታውሳሉ፡፡ይሁንና ይህ አይነቱ አካሄድ በሚወለደው ልጅ ላይ የስነ ልቦና ጫና ያሳድራል የሚልም አስተያየት እንደተነሳም ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ጉዳዩን በተመለከተ በጠቅላይ ዓቃቤ በኩል የሚካሄድ ጥናት እንዳለ አመልክተው፣ የመጨረሻ ውሳኔ አለማግኘቱን ግን ይጠቅሳሉ፡፡
በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የብሄራዊ ሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሐግብር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይበቃል ግዛው፣‹‹ሴቶችን በተመለከተ ተፈጥሮን ያገናዘ የእስር ጊዜ ቢኖር ተብሎ የተነሳው ጉዳይ አወዛጋቢ ነገር ነው፡፡››ይላሉ፡፡ ማረሚያ ቤቶች ሴቶች በሚታሰሩበት ወቅትም ህጉ ነፃነታቸውን ነው እንጂ ዘር የመተካትና ትውልድ እንዲቀጥል የማድረግ መብታቸውን የመቀማት ፍላጎት የለውም፡፡ ነገር ግን በተለይ ከባድ በሆኑ ወንጀሎች ማረሚያ ቤት የሚገቡ ሴት ታራሚዎች እንዲህ አይነት ነገር ያጋጥማቸዋል፡፡››ይላሉ፡፡
‹‹ይህን ችግር እንዴት አድርገን እንፍታው የሚለውን በተመለከተ የጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ጥናት በማካሄድ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡››የሚሉት ኃላፊው፣‹‹በሁለተኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐግብር ሰነድ ይህ ጉዳይ እንዴትና በምን መልኩ ነው ሊካሄድ የሚችለው እየተከናወነ ነው፡፡››ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እርሳቸው እንዳሉት፤አንዳንድ ጊዜ ማረሚያ ቤት ልጆች እንዲወለዱ መፍቀድና የልጆች አስተዳደግ በተመለከተ በራሳቸው በልጆቹና በማረሚያ ቤቱ ላይ የሚፈጥረው ጫና በጣም ውስብስብ ሲሆን፣ጉዳዩን ማጤን የሚጠይቅና ጥያቄም ያስነሳል፡፡ ስለዚህ ጥናት እንዲካሄድበት ተቀመጧል፡፡ በመሆኑም ያ ጥናት እንደተጠናቀቀ የራሱን ውሳኔ ያገኛል ማለት ነው፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2011
አስቴር ኤልያስ