-የአክሱም ሐውልቶችንም ጎበኙ
አዲስ አበባ (ኤፍ.ቢ.ሲ)፡– ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአክሱም ሀውልቶችን ጎበኙ፡ ፡ከጉብኝታቸው በኋላም ከአክሱም ከተማ ከተውጣጡ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ወጣቶች ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአክሱም ሐውልቶች ላይ የተጋረጠውን አደጋ በአካል መመልከት የቻሉ ሲሆን፣ በአክሱም ከተማ የሚገኙ ጥንታዊ መካነ መቃብርንም ጎብኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአክሱም ከተማ ከተውጣጡ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ወጣቶች ጋር ተወያይተዋል፡ ፡በውይይቱ ወቅትም ነዋሪዎቹ በአክሱም ሐውልቶች ላይ ለተጋረጠው አደጋ መንግስት መፍትሄ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የአክሱም ሐውልቶች የአገር ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ቅርሶች በመሆናቸው መንግስት ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባልም ሲሉም ነዋሪዎቹ አመልክተዋል፡፡
በከተማዋ ያለውን ስር የሰደደ የውሃ ችግር ለመቅረፍ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግም የጠየቁት ነዋሪዎቹ፣ አክሱም ከተማ የጎብኚዎች መዳረሻ ከመሆኗ አንጻር ምቹ መሰረተ ልማት እንዲሟላ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም የፌዴራል ስርዓቱ እና ህገ መንግስቱ ተግባራዊነት ላይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ያሉት ነዋሪዎቹ ፣ ስለ ክልል በጀት መቀነስ፣ ስለ ኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት፣ስለ ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ከሚስተዋለው የሰላም መደፍረስ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው የከተማዋ የውሃ ችግር በክልሉ መንግስት የሚመለስ መሆኑን ጠቅሰው፣ የፌዴራል መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ አንስተዋል።
ለአክሱም ሐውልቶች የሚደረገው የቅርስ ጥገና እና ጥበቃ ከጣሊያን መንግስት ጋር በተደረሰው ስምምነት መሰረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።ከገንዘብ ባለፈ ግን ዘለቄታዊ መፍትሄ ለመስጠት ባለሙያ ማሰባሰብ እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የክልል በጀት ቀንሷል በሚል ለተነሳው ጥያቄም በየአመቱ ጭማሪ እያሳየ መሆኑን በመጥቀስ፣ መረጃው የተሳሳተ ነው ብለዋል።ለዚህም በዘንድሮው በጀት አመት ለክልሎች ድጎማ 147 ቢሊዮን ብር መመደቡን ጠቅሰዋል።
ከምርጫው ጋር በተያያዘም እንደ ኢህአዴግ ምርጫው እንዲካሄድ ፍላጎት መኖሩን ጠቅሰው፣ በጉዳዩ ላይ መግባባት ላይ ለመድረስ ግን ከሁሉም ፓርቲዎች ጋር በጋራ መምከር እንደሚገባም አውስተዋል።ከዚህ ጋር በተያያዘም ቦርዱ እንደ አዲስ እየተዋቀረ በመሆኑ ውሳኔዎች በዛ በኩል እንደሚያልፉም ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው ህገ መንግስቱ የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆኑን እና ጥያቄ አለኝ የሚል አካል ማድመጥ ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል።በህገ መንግስቱ ላይ ጥያቄ አይነሳ ማለት ተገቢነት የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ ላይ ልዩነት ካለ መነጋገርና መከራከር አግባብ ነው ብለዋል ።
የኢትዮ ኤርትራን ግንኙነት በተመለከተም የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የበለጠ ለማሳደግ በጋራ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ነዋሪዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄያቸውን ተቀብለው ሐውልቱን በማደስ ዙሪያ ለመነጋገር መምጣታቸውን አድንቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ማለዳ አክሱም ከተማ ሲገቡ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል አቀባበል አድርገውላቸዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2011