በትራፊክ አደጋ መሞት ይብቃ!

ቴክኖሎጂ የሰው ልጆችን የእለት ተእለት ተግባርና እንቅስቃሴ የማቅለሉን ያህል፤ ፋይዳውን በልኩ ተገንዝቦ ከመጠቀም አኳያ የሚታዩ የእውቀት፣ የክሒሎት፣ የሥነምግባርና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት በሰው ልጆች ሕይወት ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖና ጉዳትም ቀላል አይደለም።

በዚህ ረገድ የተሽከርካሪ (መኪና) በሰው ልጆች የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ከማቅለል አኳያ ከፍ ያለ ሚናን እየተወጣ ይገኛል። በዚህም ሰዎች መድረስ የሚፈልጉበት ቦታ በፍጥነትና በምቾት እንዲደርሱ፤ ደኅንነታቸውና ንብረቶቻቸው ተጠብቆ ከቦታ ቦታ በቀላልና በቀለጠፈ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ፤ የሰው ልጆች እንቅስቃሴን የተሳለጠ አድርጓል።

ይሁን እንጂ ይሄንን የሰው ልጆች ኑሮ አቅላይ ተሽከርካሪ/መኪና፤ በእውቀት፣ በአቅም፣ በክሒሎት፣ በሕግና ሥርዓት እንዲሁም ሥነምግባርን ተላብሶ ካለመጠቀም አኳያ እያደረሰ ያለው ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ በትራፊክ አደጋ ምክንያት ዓለማችን ሚሊዮኖችን በየዓመቱ ታጣለች። ኢትዮጵያም በየዓመቱ የሺዎችን ሕይወት ትነጠቃለች፤ በቢሊዮን የሚገመት ንብረትም ታጣለች። ለምሳሌ፣ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ አንድ ሺህ 358 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ሁለት ሺህ 672 ሰዎች ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የመኪና አደጋ በሰው ሕይወት ላይ ብቻ ሳይሆን በንብረት ላይም ከፍ ያለ ዋጋን እያስከፈለ ያለ የሀገር ኢኮኖሚ አውዳሚ መሆኑ አልቀረም። በሀገራችን ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ በትራፊክ አደጋ ምክንያት ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ ንብረት ወድሟል። በዚህ ረገድ የተጠቀሰው ቁጥር ከአምናው አንጻር ሲታይ መቀነስ የታየበት ቢመስልም፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየታየ ያለው አሰቃቂ የመኪና አደጋ ግን ችግሩ አሁንም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለመሆኑ አመላካች ነው።

በዚህ መልኩ አሳሳቢ ሆኖ ለሚታየው የትራፊክ አደጋ በርካታ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላል። ለምሳሌ የአሽከርካሪዎች ቸልተኝነት፣ ሥነምግባር እና እውቀት ዋነኛው ጉዳይ ተደርጎ በተለያየ መልኩ ይገለጻል። ይሄ ደግሞ ከአሽከርካሪዎች የአሽከርካሪነት ፍቃድ (መንጃ ፈቃድ) አሰጣጥ ጋር አብሮ የሚቆራኝ ነው።

ምክንያቱም አንድ አሽከርካሪ የአሽከርካሪነት ፈቃድ ሲወስድ፤ ለወሰደው ደረጃ የሚመጥን የዕውቀት፣ የንቃትና ሥነምግባር አቅምን ጨብጧል ተብሎ ነው። ይሁን እንጂ በእኛ ሀገር ሁኔታ በአመዣኙ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሂደቱ በእጅጉ ለሙስና የተጋለጠ፤ አንዳንዴም “ከከፈሉ ቤት ድረስ ይሄዳል” የሚል ቅሬታ ጭምር የሚቀርብበት ነው።

ሌላኛው ምክንያት ተደርጎ የሚነሳው፣ የእግረኞች ያልተገባ የመንገድ አጠቃቀም፣ የተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ብቃት መጓደልና የመንገድ ሁኔታ ሲሆን፤ በዚህ ረገድ የሚነሱ ችግሮችም አንድም ከግንዛቤ ችግር፤ ካልሆነም ከቸልተኝነትና ሥነምግባር ጉድለት ጋር የሚተሳሰሩ ናቸው። ለምሳሌ፣ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ብቃት ችግር፤ ከዓመታዊ የተሽከርካሪ ቴክኒክ ፍተሻ እና ቦሎ አሰጣጥ ችግር ተነጥሎ የሚጠቀስ አይደለም።

የመንገድ ሁኔታም፣ መንገዶች ሲሠሩ መንገድ የሚፈልገውን ደረጃ እና ምልክቶች አሟልቶ ካለመሥራት ጋር የሚገናኙ ናቸው። እናም የተሽከርካሪ ቴክኒክ ብቃት ችግርም ሆኑ የመንገድ ሁኔታ በየዘርፉ ከተሠማሩ ተቋማትና ግለሰቦች የአቅም አልያም የሥነምግባር መጓደል ጋር ተገናዝበው የሚነሱ ናቸው።

ምክንያቱም አቅም ያለው እና መልካም ሥነምግባርን የተላበሰ ተቋምና ግለሰብ፤ የቴክኒክ ችግር ያለበትን ተሽከርካሪ ብቃት አለው ብሎ ቦሎ አይለጥፍለትም። በተመሳሳይ ለትራፊክ እንቅስቃሴ ምቹ ያልሆነ መንገድ ገንብቶም ለተሽከርካሪ ክፍት አያደርግም።

እዚህ ላይ ሊታሰብ የሚገባው ጉዳይ ችግሩ ምንም ይሁን፣ በማንም ምክንያት ይፈጠር፤ እየሆነ ያለው ጉዳይ በዜጎች ሕይወትና አካል ላይ፣ በሀገር ኢኮኖሚም ላይ እየፈጠረ ያለው ቀውስ በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑን መገንዘብ እና ችግሩን ለመሻገር የሚያስችሉ ርምጃዎች መውሰድ ላይ ማተኩር የሚገባ መሆኑን ነው።

ለዚህ ደግሞ ከመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ነቅሶ ማረምና ርምጃ መውሰድ፤ ከትራፊክ ተቆጣጣሪ አካላት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ተከታትሎ ማረምና ማነጽ፤ ከተሽከርካሪ የቴክኒክ ችግር ጋር የሚታየውን ጉድለትም በወጉ ፈትሾ ችግሩን ከምንጩ ለመግታት መጣር፤ ከመንገድ ሁኔታ ጋር ያሉ ጉድለቶችንም ተመልክቶ ማረም፤ የግንዛቤ ክፍተቱንም መሙላት ተገቢ ነው።

ይሄን ማድረግ ደግሞ የዜጎችን (የእናቶችን፣ የሕጻናትን፣ የወጣቶችን፣ የአረጋውያንን) ሕይወትም አካልም መታደግና የሀገር ኢኮኖሚንም መጠበቅ ነው። ለዚህ ደግሞ አይመለከተኝም የሚል አካል ሊኖር አይገባም። አሽከርካሪዎች፣ የትራፊክን ተቆጣጣሪዎች፣ መንገድ ገንቢዎች፣ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ብቃት አረጋጋጮች፣ እግረኞች፣… ሁሉም በኃላፊነት ስሜት ሊሠሩ ይገባል።

ይሄን ማድረግ ሲቻል የትራፊክ አደጋን መቀነስ፤ መኪናን የሰው ልጅ ሕይወት አቅላይ ማድረግ፤ በመኪና አደጋ ምክንያት የሚቀጠፈውን የሰው ሕይወት፤ የሚጎድለውን አካል፤ እና የሚወድመውን ንብረት ማዳን እንችላለን። በመሆኑም የትራፊክ/የመኪና አደጋ አሁን ላይ እያደረሰ ካለው ከፍ ያለ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት አንጻር አሳሳቢነቱን በመረዳት ተገቢውን እርምትና ርምጃ መውሰድም ዘርፉን ከሚመሩ ተቋማት ይጠበቃል!

አዲስ ዘመን መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You