በመሠረተ ልማት ጉድለት የነዋሪዎችን ኑሮ ያከበዱ የጋራ መኖሪያ ቤቶች

ነዋሪው በራሱ ጥረት አንድ ቧንቧ ከግለሰብ በመጥለፍ ለ88 ቤቶች እንዲደርስ ጥረት አድርጓል። ከዚህች ቧንቧ ውሃ ለመቅዳት የጀሪካን ሰልፉ ረጅም ነው። ሰው ውሃውን ለማግኘት “ቀኑን ለሠራዊት ሌቱን ለአራዊት” የሚለውን ሀገርኛ ብሂል ጥሶ ሌሊት ስምንት ሰዓት ጀሪካን አሰልፎ ውሃ ይቀዳል። ምክንያቱም አንድ ጀሪካን ለመሙላት ቢያንስ 20 ደቂቃ መጠበቅ ይኖርበታል።

የሕንጻ መወጣጫ አሳንሰሩ አልተገጠመም። ደረጃዎቹም ቢሆኑ በአግባቡ የተሠሩ አይደሉም። ለሕጻናት አስጊ ናቸው። ኮንትራክተሩ መሠል ሥራዎችን ጨርሶ እንዲሠራ ቢጠይቁትም ገንዘብ አልተለቀቀልኝም ብሎ መልስ እንደሚሰጣቸው ነው የቦሌ ቡልቡላ የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪዎች የተናገሩት። ይህ ችግር የአንድ ወይም ሁለት ሳይት ችግር አይደለም። ኢፕድ ተዘዋውሮ የተመለከታቸው በርካታ የጋራ መኖሪያ ቤት ሳይቶችም በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ይገኛሉ።

አቶ አበበ ባይነሳኝ በቦሌ ቡልቡላ ኮንዶሚኒየም የብሎክ 29፣ 30፣ 31 እና 32 ብሎክ አስተዳደር ሲሆኑ፤ ቤቶቹ የቆዩና በቅርብ ጊዜ የተሠሩ መሆናቸውን ያነሳሉ። ቆየት ያሉት ውሃ ሲኖራቸው መብራት ግን የላቸውም። አንዱ ብሎክ ግን ውሃም መብራትም እንደሌለው ይገልጻሉ። ወደ 180 ቤቶች የሚሆኑት ውሃ የሚያገኙት ከሌላ ቦታ በመጥለፍ እንደሆነም ይናገራሉ። “የሚመለከታቸውን አካላት ውሃና መብራት ስንጠይቅ መብራት ካልገባላችሁ ውሃ ማስገባት አንችልም ይሉናል። ይህንን ተመላልሰን ጠይቀን ምላሽ ባለማግኘታችን ተስፋ ቆርጠን ትተናል። የዚህ የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪ ከፍተኛ ለሆነ ምሬትና ብሶት ተጋልጧል” ይላሉ።

አቶ አበበ፤ “ቤቶች ስንሄድ መብራት ኃይል ሂዱ ይላሉ። መብራት ኃይል ስንደውል ደግሞ ብር አልተከፈለም ብለው ያጉላሉናል። በአሁን ወቅት መብራት ለማሰራጨት ቆጣሪ ተገጥሟል። ይህ አገልግሎት ሳይሰጥ ሦስት ወር አልፎታል። የጣሪያ ግድግዳ ግብር በመክፈል ግዴታችንን እየተወጣን ቢሆንም መብታችን የሚያስከብርልንን አጥተናል” ሲሉ ነው ቅሬታቸውን በምሬት የሚገልጹት።

መሠረተ ልማቱ ባለመሟላቱ ምክንያት ከ80 በላይ የጂ7 ቤቶች ውስጥ ወደ ቤታቸው የገቡት 30 ሰዎች ብቻ መሆናቸውን የሚጠቅሱት አቶ አበበ፤ የገቡትም መሠረተ ልማት ተሟልቶላቸው ሳይሆን የቤት ኪራይ የመክፈል አቅም ስለሌላቸው ከዚህ ችግር ለማምለጥ ሲሉ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ከደህና ቤታችን ለልማት በሚል ተነስተን መጥተን አሁን ላይ የውሃ ጥምና የመብራት ችግር እያሰቃየን ነው በማለት፤ የችግሩን አሳሳቢነት ለመግለጽ ብዙ ቦታ መሄዳቸውንና ምንም መፍትሔ ማግኘት አለመቻላቸውን ለኢፕድ አብራርተዋል። ባለሰባት ወለሉ ሕንጻ ሊፍት እንዳልተገጠመለትና ልጆች ጉድጓድ ውስጥ እንዳይገቡ በሚል ኅብረተሰቡ በቆርቆሮ እንደሸፈነውም የሚገልጹት አቶ አበበ፤ ይህ ግን ዘላቂ መፍትሔ ካላገኘ አደጋ ሊያደርስ እንደሚችልም ተናግረዋል።

አቶ አበበ እንደሚሉት፤ ባዶ ቤቶችን ማንም ሰው እንዳሻው እየተጫወተባቸው ነው። ቤት እየሰበሩ የሚገቡ አሉ። አንዳንዶቹን ቤቶችም ወደ መፀዳጃ ቤትነት የቀየሩ አሉ። በሚመለከተው የመንግሥት አካላት ቁጥጥር እየተደረገበት አይደለም።

ወይዘሮ ማርታ ሽመልስ ቦሌ ቡልቡላ ብሎክ 31 ነዋሪ ሲሆኑ፤ ወደ ቤታቸው ከገቡ ሦስት ዓመታትን አስቆጥረዋል። ሆኖም መብራትና ውሃ መሠረታዊ ችግር መሆኑን ይናገራሉ። እርሳቸው ያሉበት ብሎክ ውሃ በሳምንት ጥቂት ቀናት ብቻ በተቆራረጠ መንገድ ቢመጣላቸውም፤ መብራት ግን እስካሁን እንደሌለ ነው የሚገልጹት። ግቢው ጭምር ለኑሮ ምቹ ሆኖ ባለመሠራቱ በራሳቸው ወጪ እያሠሩ እንዳለም ጠቅሰዋል።

ግብር በመክፈል ግዴታችንን እየተወጣን ቢሆንም ውሃና መብራት የማግኘት መብታችን ተነፍጎናል የሚሉት ወይዘሮ ማርታ፤ “መሐል ከተማ ሊባል በሚችል ቦታ ላይ ተቀምጠን መብራት ማጣታችን ተገቢ አይደለም። ይህም ሕዝብን በእጅጉ እያማረረ ነው” ሲሉ ይገልጻሉ።

በብሎክ 32 የጂ7 ሕንጻ ላይ መጀመሪያ ብቻቸውን እንደገቡ የሚጠቅሱት ወይዘሮ አበባ ግርማይ በበኩላቸው፤ የጋራ መኖሪያ ቤቱ ውሃ ስለሌለው ላለፉት ሁለት ዓመታት ሙሉ በደካማ አቅማቸው በጀሪካን እየተሸከሙ ገንዘባቸውንም ጉልበታቸውንም እያባከኑ ስለመሆናቸው ይናገራሉ። መብራት ከግለሰብ ቀጥለው እየተጠቀሙ እንደሆነም ገልጸዋል። አንድ ጀሪካን ውሃ እስከ 30 ብር በመግዛት፣ ለተሸካሚ የሚከፈለውን ጨምሮ በቀን ብዙ ገንዘብ እያወጡ እንዳለም ጠቅሰዋል። ይህንን ችግር ሲያመለክቱ ከእሺታ ውጪ ገቢራዊ የሆነ ተጨባጭ መልስ ማግኘት ባለመቻላቸው ተስፋ ቆርጠው በችግር ውስጥ ሆነው እየኖሩ መሆናቸውንም ገልጸውልናል።

ልጅ ይዞ ልብስ ማጠብ፣ ፅዳት መጠበቅ አለ። ይህ ኮንዶሚኒየም ነዋሪ ለሆነ ደግሞ ችግሩ ይብሳል። ለዚህ ነው ኑሮው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነባቸው። “በመንግሥት በኩል የሚወርዱ ማናቸውንም ትዕዛዞች እያከበርን ግብርም እየከፈልን ነው። የኛ መብት ግን አልተጠበቀልንም፤ የሚመለከተው አካል ይህንን ችግር በአፋጣኝ እንዲፈታለን እንፈልጋለን” ሲሉ ጠይቀዋል። ሕይወት ተሾመ በቦሌ በሻሌ ሳይት የጋራ መኖሪያ ብሎክ 37 ነዋሪ ናቸው። ዕጣው የወጣላቸው በ2011 ዓ.ም ሲሆን እስካሁን በሳይቱ የመብራትና ውሃ እንዲሁም የአሳንሰር መሠረተ ልማት እንዳልተሟላ ይገልጻሉ።

የሦስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ሕይወት፤ የጋራ መኖሪያ ቤቱ ውሃ ስለሌለው ሕጻናቱን መፀዳጃ ለማስጠቀም ሁልጊዜ ከሦስተኛ ወለል ላይ ወደ ታች መውረድ የግድ እንደሚላቸው ይናገራሉ። ውሃ የሚጠቀሙት በጋሪ ከሚያዞሩት ሰዎች ላይ በመግዛት ሲሆን ለአንድ ጀሪካን 25 ብር እየገዙ ለተሸካሚው ደግሞ ተጨማሪ ክፍያ እንደሚፈጽሙ ነው የሚገልጹት። ይህም ለአንድ ጀሪካን ውሃ 50 ብር ድረስ ወጪ ያስወጣል ነው ያሉት። ብዙ ልጅ ያለው ቤተሰብ 10 ጀሪካን ቢጠቀም በቀን እስከ 600 ያህል ብር ወጪ ሊያወጣ እንደሚችልም ነው የሚጠቅሱት፤ ይህ ደግሞ ተከራይቶ ከመኖር የሚተናነስ አይደለም ነው ያሉት። በዚህ ሳይት መብራት ለነዋሪው ስላልገባ ሳይቱን ሲሠራ ከቆየው ኮንትራክተር የኤሌክትሪክ ኃይል የጠለፉ ብሎኮች እንዳሉና ለዚህም አንድ ቤተሰብ በወር 800 ብር እንደሚከፍል ገልጸዋል።

እርሳቸው ባሉበት ብሎክ ላይ ከ100 በላይ ቤቶች ቢኖሩም እስካሁን የገቡት ግን ስምንት ብቻ ናቸው። አብዛኞቹ ያልገቡት መሠረተ ልማቱ ባለመሟላቱ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል። ቤቶቹ የንግድ ቤቶች ታሳቢ ተደርገው የተሠሩ ቢሆንም ሥራ ባለመጀመራቸው ሱቆችን በቅርብ ርቀት በበቂ ሁኔታ አለማግኘትም አንዱ ችግር ነው ብለዋል። የሚመለከተው አካል የገባውን ውል ፈጽሞ የነዋሪውን ኑሮ ለማስተካከል ጥረት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በዚህ ሳይት፤ ታማሚዎች ሕንጻው ላይ በደረጃ መመላለስ ስለማይችሉ ምግብና መሰል ግብዓቶች ከታችኛው ወለል ላይ ካለው ሱቅ በገመድ እየተጎተት እንደሚደርስላቸው የኢፕድ ሪፖርተሮች መመልከት ችለዋል። አብርሐም ለላንጎ ቦሌ በሻሌ ሳይት የጋራ መኖሪያ ብሎክ 28 ነዋሪ ሲሆን፤ የ2011 የሁለተኛው ዙር 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ዕድለኛ ነው። የጊቢው ኮሚቴ አስተባባሪም ነው። በቦሌ በሻሌ ሳይት 58 ያህል ብሎኮች ያሉ ሲሆን፤ 40/60 ከያዛቸው ሳይቶች ትልቁ እንደሆነም ጠቅሷል።

እንደ ነዋሪው ገለጻ፤ በ2011 የወጡት 31 ብሎኮች ናቸው። ቀሪ 27 ብሎኮች በ2015 የወጡ ናቸው። ባለ 9፣ ባለ13 እና ባለ 15 ወለል ያላቸው ናቸው። ወደ ኋላ የቀረ ሳይት ነው። ዕጣው ላይ ለመድረስ ባለው ጊዜ አምስት ዓመት ያህል ወስዷል። ዕጣው ከወጣ በኋላም ሰው መግባት የጀመረው ከአምስት ዓመት በኋላ ነው።

በሳይቱ የፍሳሽ ሥራው ባለፈው ሁለት ወር ገደማ መጠናቀቁን በመጥቀስ፤ መብራትና ውሃውም በተመሳሳይ ቢገቡና ችግሩ ቢፈታ በመሠረተ ልማት አለመሟላት ምክንያት ወደ ቤቱ ያልገባው ነዋሪ ወደ ቤቱ እንደሚገባ ይጠቅሳል። ይህም ከተማ ውስጥ ያለውን የቤት ችግር ይቀንሳል ይላል።

በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የቅርንጫፍ ሦስት ሥራ አስኪያጅ አቶ አየነው ዓለሙ፤ በቦሌ በሻሌ 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች 6 ሺህ 509 ቤቶች መኖራቸውን፤ ከዚህ ውስጥ 5 ሺህ 374 የመኖሪያ እንዲሁም 1 ሺህ 135 የንግድ ቤቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዕጣው የወጣው በ2011 እና 2015 ዓ.ም በሁለት ዙር እንደሆነ በመጥቀስ፤ እስካሁን የገቡት እስከ ሁለት መቶ የሚደርሱ ናቸው ብለዋል። አብዛኛው ሰው በመሠረተ ልማት አለመሟላት ምክንያት እንደሚቸገርና የመሠረተ ልማት ተቋማት የግብዓት አቅርቦትን ጨምሮ የተለያየ ምክንያት ሊኖራቸው እንደሚችሉ ተናግረዋል። የመብራትና የውሃውን የሲቪል ሥራ የሚያከናውነው የመንገዶች ባለሥልጣን እንደሆነና ይህ እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን የግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ስጦታው አካለ፤ ነዋሪዎች ዕጣ ካወጡባቸው ጊዜያት ጀምሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ቤታቸው እንዲገቡ በከተማ አስተዳደሩ በኩል ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም፤ አሁንም ድረስ ያልገቡ እንዳሉ ገልጸዋል። ለመኖር የሚያስችሉ ዋና ዋና መሠረተ ልማት አውታሮች መዘርጋት ስላለባቸው ይህን በመጠበቅ ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል።

በ2015 በጀት ዓመት እስከ ሰኔ 30 ባለው ብቻ እስከ 130 ሺህ የሚሆን ሕዝብ ወደ ቤቱ ማስገባት ተችሏል። ከ2015 በጀት ዓመት ያደሩ ሥራዎች ከአቅም በላይ ሆነው የተላለፉ ናቸው። ሆኖም እስካሁን ዕጣ ከወጣላቸው 139 ሺህ ነዋሪዎች ውስጥ ወደ 7 ሺህ ገደማው ወደ ቤታቸው አልገቡም።

“እነዚህን ቤቶች በ2016 እቅዳችን አድርገን እስካሁን ሰዓት ድረስ እየሠራን እንገኛለን። ስለዚህ ችግሩ እንዳለ እናምናለን። ነገር ግን ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው” ብለዋል። ከምክንያቶቹ አንዱና ዋነኛው የፋይናንስ ችግር እንደሆነም ኢንጂነር ስጦታው ገልጸዋል። የኅብረተሰቡ ቁጠባ ሙሉ ቤቱን ስለማይሠራ ዛሬ ላይ ኮንስትራክሽን በምን ያህል ብር እንደሚገነባ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከመንግሥት ወይም በባንክ ብድር ተበድረን ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ እዳ ውስጥ ገብተን ነው ቤት እየገነባን ያለነው ያሉት ኢንጂነር ስጦታው፤ አሁን ካለው የኮንስትራክሽን ዋጋ አንጻር ኅብረተሰቡ ምንም እንኳን የሚጠበቅበትን መቆጠብ ቢችልም በእጅጉ እንደሚያንስ አስታውቀዋል። በቂ ባለመሆኑ ምክንያት የፋይናንስ እጥረት መግጠሙንና እጥረቱን ለመሙላት የፋይናንስ ምንጭ እየተፈለገ መሠረተ ልማት እንዲሟላና ቤቶቹ ምቹ እንዲሆኑ የቀሩት ቤቶች እንዲጠናቀቁ የማድረግ ሥራ እየተሠራ እንዳለ ገልጸዋል። ችግር ያለባቸው ቤቶችን በየሳይቱ ምን እንደጎደላቸው ተለይተው ችግሩን ለመፍታት እየተሠራ ነው ብለዋል።

ሌላው ችግር የተቋራጮች አቅም ውስንነት መሆኑን የገለጹት ኢንጂነር ስጦታው፤ “በጦርነት ውስጥ የቆየን ስለሆነ ተቋራጮች በቂ ሥራ እየሠሩ ስላልሆነ ለሠሩት ሥራ ጭምር የፋይናንስ ጥያቄ ሲጠይቁ ምላሽ መስጠት ባለመቻላችን ምክንያት በሙሉ አቅማቸው ሥራ እየሠሩ አይደለም” ብለዋል። የፋይናንስ እጥረቱ በተቋራጮች አቅም ላይ ጫና መፍጠሩንም ነው የጠቀሱት። በኅብረተሰብ ተሳትፎ የሚሠሩ ሥራዎች እንዳሉና ሁሉም ሥራ በመንግሥት የሚሠራና የሚጠናቀቅ ባለመሆኑ ኅብረተሰቡ ራሱ ቤቱ ከተሠራለት ገብቶ ማልማት በጋራና በትብብር መሠራትን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

እንደ ኢንጂነር ስጦታው ገለጻ፤ የቦሌ በሻሌ ሳይት የጎደሉት ነገሮች አሉት። ከእነዚህም መካከል አንዱ ሊፍት ሲሆን በቀጣይ የሚስተካከል ይሆናል። አሁን ካለው የዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ ትልቅ በጀት የሚጠይቅ ነው። ከውጭ የሚገባ በመሆኑ ጊዜ ወስዷል። ነገር ግን አሁን ላይ አቅራቢዎቹ ውል ገብተው ባስቸኳይ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ስለሆነ በቀጣይ አንድ ወይም ሁለት ወር ውስጥ የሊፍት ገጠማ ሥራ ይከናወናል። ከውሃ ችግር ጋር ተያይዞም ፓምፕ ጨረታ ላይ ስለሆነ በጥቂት ወራት እንደሚገጠም ጠቅሰዋል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2016 ዓ.ም

Recommended For You