ለሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ ሥዕሉን ያዋሰው- ጥበበኛ

በልጅነቱ አፈር ፈጭቶ ያደገው ዱከም ነው፡፡ አባቱ ጽሑፋቸው የሚያምር የቁም ፀሐፊ ደግሞም በየዓመቱ ሦስት ወንድ ልጆቻቸው ወዳጅ ዘመዶችን እንኳን አደረሳችሁ የሚሉበት የአዲስ ዓመት አበባን ግሩም አድርገው የሚስሉ የግሩም ተሰጥኦ ባለቤት ናቸው። እሱም የአባቱን ወርሶ ሳይሆን አይቀርም ከወንድሞቹ እኩል ድርሻህ ተብሎ የተሰጠውን ሥዕል በድጋሚ እየሠራ ከወንድሞቹ በበለጠ በርካታ ወዳጆችን እንኳን አደረሳችሁ የሚል ሠዓሊ ወጣው፡፡

የአሁኑ ሠዓሊ የያኔው ታዳጊ ወንደሰን ከበደ ሀገር ወዳድ ነው፤ የዚህ መንስኤውም ከወታደሮች ጋር በማደጉ ነው፡፡ ባደገበት አካባቢ አራት የወታደሮች ካምፕ ነበር፡፡ ለዚህም ይመስላል አብዛኛው የአካባቢው ሰው ወታደሮች ናቸው። የወታደሮች ካምፕ እንደልብ የመግባትና የመውጣት ዕድል ነበራቸው፡፡ በቅርበት የሚያገኟቸው ወታደሮች ሁሌ ስለድልና ስለኢትዮጵያ ታሪክ እየነገሩና አንድ ሕዝብ አንድ ባንዲራ እያሉ ነው ያሳደጉን ይላል፡፡ በወታደሮቹ ጦር ሜዳ ስለነበረው ጀብድና ስለገጠመኞቻቸው እየተተረከለት በኢትዮጵያዊነት ስሜት ተቃኝቶ አድጓል፡፡ በ1992 በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃል በተነሳው ጦርነት ለመዝመት ተመዝግቦ ወታደራዊ ሥልጠናም ወስዶ ነበር፡፡ ዘመቻው ላይ ግን አልተሳተፈም፡፡

ከዋናው ሥራቸው ጎን የቁም ፀሐፊ የሆኑ አባት ቢኖሩትም የእጅ ጽሑፉ የማያምር ተማሪ ማለት ወንደሰን ከበደ ነው፡፡ በትምህርት ጎበዝ ከሚባሉት ተርታ ቢመድብም የእጅ ጽሑፉ ወላጅ አምጣ እስከመባል አድርሶታል፡፡ የእጅ ጽሑፉ አላምር ብሎ ያስቸገራቸው መምህር ግራ ቢገባቸው ጽሑፉን ያስተካክል ዘንድ እጁ እስኪያብጥ ገርፈውታል፡፡ የእጅ ጽሑፉ ወቀሳ የበዛባት ወላጅ እናቱ በዚሁ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ መፍትሔ አፈላልጋለች፡፡ በየእለቱ ከትምህርትና ከጥናት መልስ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በመስጠት እንዲያነብና ሃሳቡን እንዲያስረዳቸው ያደርጋሉ፡፡ በመቀጠል ጋዜጣው ላይ ያሉ ጽሑፎችን አስመስሎ እንዲጽፍ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ሂደት ብዙም ሳይቆይ የእጅ ጽሑፉ መሻሻል አሳየ፡፡

በዚህ የተነሳም በእጅ ጽሑፉ ማስጠላት ሲወቀስበት በነበረው ዱከም በሚገኘው በቀድሞው ደጃዝማች ፍቅረማርያም ትምህርት ቤት በአሁኑ ኦዳ ነቤ ትምህርት ቤትም ሆነ ቢሾፍቱ በሚገኘው ልዕልት ተናኜ ወርቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በነበረው ቆይታ በእጅ ጽሑፉ ውበት ተለይቶ የሚታወቅ ተማሪ ነበር፡፡ ለጽሑፉ መስተካከል ብቻ ሳይሆን ለሁሉ ነገር መሠረቴ ናት የሚላት እናቱ ሁሌም ከሚያገኘው ገቢ ላይ ለፈጣሪ አሥራት በኩራት እንዲያወጣና በተወጉ እጆችህ እጆቼን ባርክ ብለህ ጸልይ የዘወትር ምክራቸው ነውና እሱም ይተገብረዋል፡፡

ከፍ እያለ ከሄደና የእጅ ጽሑፉን ካስተካከለ በኋላ ሌላው ወላጅ ያስመጣው ነገር ቢኖር በሌላ ክፍለ ጊዜ ሥዕል መሳሉ ነው፡፡ ያም ቢሆን መምህራኖቹ አልጨከኑበትም። የሥዕል ውድድር መኖሩን በሬዲዮ ሲሰሙም ሆነ ጋዜጣ ላይ ስለሥዕል ውድድር ማስታወቂያ ካዩ የሱ ነገር ትውስ ይላቸዋል፡፡ እናም በቻሉት ሁሉ ነገሮችን አቀናጅተው በውድድሩ እንዲሳተፍ ያመቻቹለታል፡፡ ሠዓሊ ወንደሰን ባለፈበት መንገድ ስማቸውን የሚያነሳው የበርካታ መልካም መምህራን እገዛ አልተለየውም፡፡ ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ለመምህራኖቹ የእሱና የሥዕል ጉዞ ረዥም እንደሆነ ተገልጾላቸው ነበርና “በሥዕል በዓለም ታዋቂ ትሆናለህ” ይሉት ነበር፤ አለፍ ሲልም የሚሰራቸውን ሥዕሎች በጥንቃቄ እንዲያስቀምጥ ከእሱ አልፈው እናቱን ይመክሩ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለ የሠራቸው ሥዕሎች ሳይቀሩ እናቱ አሁን ድረስ በክብር አስቀምጠዋቸዋል፡፡

ወንደሰን ለሥዕል የተሰጠ መሆኑን ገና በጊዜ ተረድቷል፤ ተሰጥኦውን በትምህርት ቢደግፈው የተሻለ ውጤታማ እንደሚሆን ገብቶታል፡፡ የአንደኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ተፈትኖ ወደ ዘጠነኛ ክፍል እንደተሸጋገረ ‘አርት ኤንድ ሳይንስ’ ወይም ‘ናቹራል ሳይንስን’ መምረጥ እንደሚችል ተነገረው፡፡ በሱ አረዳድ ‘አርት ኤንድ ሳይንስ’ የሚለው ዘርፍ ስለሥዕል የሚማርበት ነውና ያለማመንታት መረጠው፡፡ ታዲያ ሥዕል ለመማር እንደቋመጠ ወደ ትምህርት ቤት ቢመላለስም የሥዕል መምህር ወደ ክፍል ሳይገቡ ወር ተቆጠረ፡፡ ያኔ ግራ የተጋባው ወንደሰን “የሥዕል መምህር አይመጡም እንዴ?” ሲል ጠየቀ፡፡ የክፍል ጓደኞቹ “የምን ሥዕል?” ቢሉ “እኛ አርት ተማሪ አይደለን እንዴ” ሲል ጠየቀ ያኔ በተማሪዎች የተሳቀበትን ያስታውሳል፡፡

በወቅቱ ከናፈቀው የሥዕል ትምህርት ጋር ባይገናኝም፤ በወረቀት ላይ ከሚሰራቸው ሥዕሎች በተጨማሪ በገንዘብ ለቡና ቤቶች መሳል ጀምሮ ነበር፡፡ ያም ቢሆን በትምህርቱ የደረጃ ተማሪ ነበርና በ1995 ዓ.ም ለከፍተኛ ትምህርት ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ተመደበ፤ በዩኒቨርሲቲው በነበረው ቆይታ ሥዕልን ግሩም አድርጎ ይጠበብት ጀመር፡፡ በጥቁር ሰሌዳም (በብላክ ቦርድ) ሆነ በወረቀት የሳላቸውን ሥዕሎች ያዩ ሁሉ ይወዱታል፡፡ ግን እሱ ሥዕልን መሥራቱን እንጂ መማር እንደሚችል አላወቀም፡፡

ችሎታውን ያዩ በስድስት ኪሎ የቀለም ትምህርት ከሚማር አራት ኪሎ የሚገኘውን አለ ፈለገ ሰላም የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤትን ቢቀላቀል የተሻለ ውጤታማ እንደሚሆን ነገሩት፡፡ አላመነታም፤ የተባለው ቦታ ደርሶ ሥዕል መሳልን እንደሚወድና ከሚማርበት ስድስት ኪሎ ተዘዋውሮ መማር እንደሚፈልግ በወቅቱ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ለነበሩት ሰው ነገራቸው፡፡

ከዳይሬክተሩ የተሰጠው መልስ ግን “ይሄ እኮ ጠጅ ቤት አይደለም፤ ዝም ተብሎ አይገባም፡፡” የሚልና ያልጠበቀው ነበር፡፡ ባገኘው መልስ ቢከፋም የተመደበበትን ትምህርት እየተከታተለ በተጓዳኝ ሥዕል መሥራቱን አላቋረጠም። ይልቁንም እሱ የተከለከለው ቦታ ገብተው የሚማሩ ጓደኞችን በማፍራት ከእነሱ ልምድ መቅሰም ቀጠለ፡፡ ሁሌ ከትምህርት ክፍለ ጊዜው ቀድሞ ወደ ክፍል በማምራት ብላክቦርድ ላይ መሳል የዘወትር ተግባሩ ነው፡፡ የአለ ፈለገ ሰላም ተማሪዎች ሞዴሎችን ከፊት ለፊታቸው አስቀምጠው ሲስሉ ያየውን እሱም በስድስት ኪሎ ይተገብራል፡፡

ዴቪድ ሼርማ የተሰኙ የእንግሊዘኛ መምህሩን ሲያስተምሩ በወረቀት ስሎ በማግስቱ ብላክቦርድ ላይ በትልቁ ሣላቸው፡፡ መምህሩ ሲገቡ ሁሌ ከራሳቸው ገራሚ ምስል ጋር ከብላክቦርድ ላይ ይፋጠጣሉ፤ በግርምት ደቂቃዎችን አባክነው ወደ ዕለቱ ትምህርት ያመራሉ፡፡ ትዕይንቱ የተደጋገመባቸው መምህር “ማን ነው የሚስለው?” ሲሉ ጠየቁ፤ እኔ ነኝ የሚልም ሆነ የሳለው እከሌ ነው የሚል ተማሪ አልተገኘም፡፡ ያኔ ታዲያ መምህሩ “ማን እንደሆነ የሚስለው የማትናገሩ ከሆነ ለሁላችሁም ኤፍ ነው የምሰጣችሁ” ሲሉ አስፈራሩ፡፡ ያኔ አማራጭ ያልነበራቸው ተማሪዎች በድምጻቸው ባይናገሩም የተመካከሩ ይመስል ሁሉም ዓይናቸውን ወደ ወንደሰን አቅጣጫ ላኩ፡፡ ይሄን ጊዜ መምህሩ “አንተ ነህ የምትስለኝ?” አሉ አማራጭ የለውምና እየፈራ “አዎ” አለ፡፡ ክፍለ ጊዜው እንዳለቀ ቢሮ እንድትመጣ አሉት፡፡

የሚጠብቀውን ቁጣና የሚወስዱበትን ርምጃ እያሰበ ሲፈራ ሲቸር ወደ ቢሮአቸው ሄደ፡፡ “እዚህ ምን ትሰራለህ?” የሳቸው ጥያቄ ነበር፡፡ የተማሪያቸውን ግር መሰኘት ያዩት መምህር “አራት ኪሎ የአርት ትምህርት ቤት አለና ለምን እዛ አትማርም?” አሉት፡፡ በሥዕል ጥሩ ተሰጥኦ ስላለው ከሚማረው የቀለም ትምህርት ይልቅ እዛ ቢማር የተሻለ መሆኑን መከሩት፡፡ እዛ ሞክሮ ያልተሳካላት መሆኑን ሲነግራቸው፤ ወደ ተቋሙ መግቢያ ሌላ አማራጮች ካሉ ሊሞክሩለት ቃል ገብተው ሥዕሉን ይሰራበት ዘንድ ሙሉ ደስታ ወረቀትና 200 ብር እርሳስ ግዛበት ብለው ሰጡት፡፡

የ1996 የትምህርት ዓመት ተጀምሯል፤ በዩኒቨርሲቲው የትምህርት ምርጫ ተካሂዶ ወንደሰንም ማኔጅመንት የትምህርት ክፍል ተመድቦ መማር ጀምሯል፡፡ በጠዋት እንደለመደው ከተማሪዎችም ሆነ ከመምህራን ቀድሞ ክፍል ውስጥ ተገኝቶ በብላክ ቦርዱ ላይ መሳል ጀምሯል። በዚህ መሃል የክፍል ጓደኞቹ መሰባሰብ ጀምረዋል፡፡ አለፍ ሲልም በዕለቱ ሊያስተምሩ ፕሮግራም የተያዘላቸው ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ ለማስተማር ከክፍል ዘልቀዋል። የእሳቸውን መምጣት እንዳየ በድንጋጤ መሳሉን ቢያቆምም ጨርስ ብለው መመልከታቸውን ቀጠሉ። ፕሮፌሰሩም ለተማሪዎቹ “ይሄ ጓደኛችሁ ከአሁን በኋላ እዚህ መማር የለበትም” አሉ፡፡ እሱንም “የአርት ችሎታ እያለህ ማኔጅመንት ክፍል ውስጥ ምን ትሰራለህ? አንተ አርት ነው መማር ያለብህ” አሉት፡፡ ጠይቆ ይሄ ጠጅ ቤት አይደለም የሚል መልስ እንደተሰጠው ነገራቸው፡፡ እሱ ሥዕል መማር እንደሚፈልግ ካረጋገጡ በኋላ፤ ማድረግ የሚችሉትን ከባልደረቦቻቸውና ከሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተው ሊያሳውቁት ቃል ገቡ፡፡

ፕሮፌሰሩ እንዳሉት ከባልደረቦቻቸው ጋር ተመካከሩ፤ መምህራኖቹ ወንደሰን ተሰጥኦ አለውና ከሚማርበት ማኔጅመንት ወደ ታሪክ ትምህርት ክፍል ቢዛወር የተሻለ እንደሆነ አመኑ፡፡ በዚህም ዝውውሩ ተሳካ፤ እዛም አልቆመም ወደ አርት ትምህርት ቤት እንዲዛወር መጻጻፉ ቀጠለ፡፡ በመሃል እንዲያውም የታሪክም የጥበብም ባለሙያ እንዲሆን ለምን በአንዴ ሁለቱንም አይማርም የሚል ሃሳብ ተነሳ፡፡ ያኔ ታዲያ ሕጉ በአንዴ ሁለት ዲግሪን አይፈቅድምና ጉዳዩ እስከ ዩኒቨርሲቲው አመራሮች ብሎም እስከ ትምህርት ሚኒስቴር ዘለቀ፡፡ በወቅቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት የሆኑት ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ ቀደም ሲል የፊሎዞፊ መምህሩ ከመሆናቸውም ባሻገር የሥዕል ሥራውን አይተው በመደነቃቸው በየወሩ ለቁሳቁስ መግዣ እንዲሆንህ ቢሮ እየመጣህ 500 ብር ውሰድ ብለው አበረታቹ ነበሩና የዩኒቨርሲቲውን ፈቃድ ለማግኘት ብዙ አልከበደውም፡፡

ከትምህርት ሚኒስቴር ጉዳዩ የተመራለት አለ ፈለገ ሰላም ትምህርት ቤትም አዲስ ኃላፊ ተመድቦለት ነበርና አጭር ደቂቃ በፈጀ የተግባር ፈተና ትምህርት ቤቱን እንዲቀላቀል ይሁንታን ተቸረው፡፡ ከአራት ኪሎ ስድስት ኪሎ ምልልሱ ቢበዛና የክፍለ ጊዜ መደራረብ ቢያጋጥመውም በተወሰኑ መምህራኑ የትራንስፖርት ወጪ ድጋፍ፤ አለፍ ሲልም በመኪናቸው እየወሰዱት ሁለቱንም በብቃት ተወጣ። ቀድሞ ከጀመረው ከስድስት ኪሎ በአፕላይድ ሂስትሪ በ1998 ዓ.ም ከአራት ኪሎ በፔይንቲንግ ደግሞ በ1999 ዓ.ም በጥሩ ውጤት ተመረቀ፡፡

ትምህርቱን እንደጨረሰ ለተወሰነ ጊዜ በመምህርነት አገልግሏል፡፡ የተወሰነ ጊዜ በሕትመት ውጤቶች ላይ ካርቱኒስት አለፍ ሲልም ፀሐፊ በመሆን ኑሮውን መርቷል። አብዛኛውን የሥራ ዘመኑን ግን የሙሉ ጊዜ ሠዓሊ ሆኖ ኖሯል፡፡ የሥዕል ሥራዎቹ የኢትዮጵያን ታላቅነት መመስከርና ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ላይ ያተኩራሉ። ሚስጥራዊና ጥንታዊ የሆኑ የኢትዮጵያ ታሪኮች ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ ይናገራል፡፡ አብዛኛው ሥራዎቹ በመጠናቸው ገዘፍ ያሉ በሚያነሱት ሀገራዊ ሃሳብም ጎላ ያሉ ናቸው፡፡ ግን ሠዓሊ ወንደሰን በብዙኃኑ ኢትዮጵያውን ልብ ውስጥ እንዲቀመጥ ያደረገው ሥዕል አንዲት ሕፃን ፊቷ ላይ ኮስተር፣ ደግሞም ቁጣ፣ ቆራጥነትን ተጎናጽፋ በኢትዮጵያ ባንዲራ ተጠቅልላ የምትታይበት ነው፡፡ በሥዕሉ ላይ የምትታየው የመጀመሪያ ልጁ ኢትዮጵያ ወንደሰን ናት፡፡ ሥዕሉን የሳለበትን አጋጣሚ መለስ ብሎ ሲያስታውሰን፤ ሀገር ወዳድ ነውና ቤቱ ውስጥ በርካታ ሰንደቃላማዎች አሉት፡፡ በአጋጣሚ ስለቆሸሹ ሊታጠቡ ከየቦታቸው የወረዱት ሰንደቃላማዎች ሶፋ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ሰዓሊ ወንደሰን ከጓደኞቹ ጋር ተቀምጦ የሞቀ ጨዋታ ውስጥ ናቸው፡፡

በዚህ መሃል ማንም ያላስተዋለው አንድ ሰንደቃላማ መሬት ላይ መውደቁን ያስተዋለችው፤ በወቅቱ የሦስት ዓመት ከስድስት ወር ዕድሜ የነበራት ልጁ ኢትዮጵያ “አባባ አባባ ጣልከው” እኮ ብላ በቁጣ ስትናገር፤ አባት ደንግጦ “ይቅርታ ጨዋታ ውስጥ ሆነን አላየነውም” ሲል “አዎ እንደዛ ነው የሚባለው” ብላ ሰንደቃላማውን ከወደቀበት አንስታ ለበሰችው ፊቷ ላይ የነበረው ስሜት የተለየ ነበርና ከእንግዶቹ እንደተለያየ ሥዕሉን መሥራት ጀመረ፡፡ በወቅቱ ትልቅ የሥዕል ኢግዚብሽን ተዘጋጅቶ ነበርና የሥዕሉ መጠን ከፍ ያለ ቢሆንም በኢግዚቢሽኑ ከሚቀርቡት ጋር እንዲታይ ስለፈለገ ያለእረፍት በተከታታይ አምስት ቀናት ውስጥ ሥሎ ለኢግዚቢሽን አደረሰው፡፡ ሥዕሉ ከመወደዱ የተነሳ በኢግዚቢሽኑ የእንግዛህ ጥያቄ ቢቀርብለትም ለመሸጥ አልፈቀደም፡፡ ከኢግዚቢሽኑ መጠናቀቅ በኋላም በርካቶች ስቱዲዮው እየተመላለሱ ይጎበኙት እንደነበር ያስታውሳል፡፡

ለምን ብዙሃኑ ጋር አይደርስም በሚል አንድ ወዳጁ አስተባባሪነት በፖስተር ተዘጋጅቶ በመሰራጨቱ በሄደባቸው የአውሮፓ ካፌዎች ተመልክቶት መገረሙን ያስታውሳል፡፡ ይህ ሥዕል ታዲያ የበርካታ ኢትዮጵያንን ቀልብ የሳበና በርካቶች በሶሻል ሚዲያ የተቀባበሉት ግሩም ሥራው ነው፡፡ ለዚህ ሥዕል የእንግዛህ ጥያቄ ከበርካታ አካላት ቢቀርብለትም እሱ ግን ባለመሸጥ አቋሙ ጸንቷል። ሆኖም ከሥዕሉ ፈላጊዎች ውስጥ በኖህ ሳማራና ቤተሰቦች አደራዳሪነት የሚችጋን ዩኒቨርሲቲም ተካተተ። አልሸጥም በሚለው አቋሙ ሲጸና ከ30 ዓመት በኋላ ሊመልሱ የውሰት ውል አቀረቡለት፡፡ ያኔ ዓለም አቀፍ ተቋም ነውና የሀገርን ገጽታም ይገነባል በሚል በ2010 ዓ.ም በ30 ዓመት የውሰት ውል ለሚችጋን ዩኒቨርሲቲ ተሰጥቷል፡፡

የሚሰራቸው ሥዕሎች በአብዛኛው ሠዓሊዎች ከሚደፈሩት ይልቅ በመጠናቸው ከፍ ያሉ ናቸው፡፡ ታዲያ ገዢ ለማግኘት አይከብድህም ወይ ቢባል፤ ሥዕልን ለመሸጥ እንደማይሰራና በተለይ የተወሰኑት ሥራዎቹን አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ካልገባ አልሸጣቸውም ይላል፡፡ ታዲያ እነዚህ ሥራዎችን መሸጥ አይፈልግምና ቤተሰቡን ለማስተዳደር የሞዛይክ፣ የቅርስ ሥራና በትእዛዝ የሚመጡ የሥዕል ሥራዎች ኑሮውን ይደጉሙታል፡፡ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ከሸጠባቸው አጋጣሚዎች አንዱ ወደ ኳታር ለመሄድ ሰዓታት ብቻ ቀርተውታል፤ ሆኖም ከሀገር ይዞት የሚወጣው በቂ ዶላር የለውም፡፡ ባለቀ ሰዓት ስልክ ተደውሎ ማምሻውን ወደ ጣልያን የሚጓዙ የውጭ ዜጎች ወደስቱዲዮው እንደሚመጡ ተነገረው፡፡ በተስፋ ጠበቃቸው፤ ለሽያጭ ካቀረባቸው ሥዕሎች የሚወስዱትን ለመግዛት መርጠው በመሃል ለገበያ አይቀርቡም ብሎ ያስቀመጣቸውና ፊታቸውን ካዞራቸው ሥዕሎች መሃል አንዱን ይበልጥ ወደዱት፤ ይሄንን መርጠናል ሽጥልን አሉ። አይ መጀመሪያ የመረጣችሁትን ውሰዱ ቢባሉ አሻፈረን አሉ፡፡ በቁጭትና አማራጭ በማጣት ውስጥ ሆኖ ሳይወድ በግድ ሸጠላቸው፡፡ ከዛ ውጭ አሁንም በርካታ የማይሸጡ ሲል የወሰነላቸው የጥበብ ውጤቶች አሉት፡፡

ሠዓሊ ወንደሰን በበርካታ የዓለም ክፍሎች በመዘዋወር የሥዕል ሥራውን ለታዳሚ አቅርቧል፤ ከሥነጥበብ ሴሚናሮች ላይ ተካፍሏል፡፡ ለረዥም ጊዜ የኢትዮጵያ ሠዓሊያንና ቀራጺያን ማህበር ዋና ፀሐፊ በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም ስለጥበብ በተለያዩ መድረኮችና ሚዲያዎች ሃሳቡን በማካፈልና ልክ አይደለም ብሎ የሚያስበውን በግልጽ በመናገር ይታወቃል፡፡ በሀገራችን በሚገነቡ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ የጥበብ ባለሙያዎች በሚገባቸው ልክ እየተሳተፉ አይደለም የሚል ሃሳብ አለው፡፡ ለጋራ ሀገራዊ ዓላማ የጥበብ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን የሚያካፍሉበት ሁኔታ ቢመቻች የተሻለ ሥራ መሥራት ይቻላል ብሎ ያስባል።

ቤዛ እሸቱ

 

አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You