የግንዛቤ እጥረት እና ‹‹የሚጥል በሽታ››

የሰው ልጅ አእምሮ እጅግ የተወሳሰበ ነው። አንጎል ደግሞ ከ100 ቢሊዮን በሚበልጡ የነርቭ ህዋሶች ይዋቀራል። እነዚህ ነርቮች በተለያየ መንገድ በመደራጀት የሰው ልጅ የእለት ተእለት ተግባሩን በሚገባ እንዲያከናውን ይረዳሉ። ለመስማት፣ ለመናገር፣ ለመብላት፣ ለማሰብ፣ እቅድ ለማውጣት፣ ትኩረት ለመስጠት፣ ለመወሰን፣ የሰውነት ጡንቻዎችን ለማዘዝና ለመቆጣጠር ያግዛሉ። በተጨማሪም፣ አተነፋፈስን፣ ስሜትን፣ የደም ዝውውርንና የልብ ምትን ያቀናጃሉ፤ ይቆጣጠራሉ።

ስለዚህ ሁሉም አስፈላጊ የሕይወት ተግባራት የሚከናወኑት በኤሌክትሪክ ንዝረትና በኬሚካል ምልክቶች አማካኝነት መልእክትች ከአንድ የነርቭ ሴል ወደ ሌሎች ሴሎች በቅፅበት ሲተላለፍ ነው። የአንጎል ነርቭ ኤሌክትሪካዊ ንዝረት ጊዚያዊ መረበሽ ሲኖረው ወይም ሲዠር /seizure/ ሲከሰት ድንገተኛና ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የአእምሮ ተግባርን የሚያውከውን የሚጥል ህመም ወይም /epilepsy/ ይፈጥራል።

በዚህ ህመም ምክንያት ሰዎች በመንገድ ላይ ሲወድቁ ማየት የተለመደ ነው። ነገር ግን ህመሙን በሚገባ አውቆ የመጀመሪያ ርዳታ በመስጠት በኩል ችግሮች ይታያሉ። ህመሙን ከእርኩስ መንፈስ ጋር የማያያዝ ሁኔታም ይታያል። አብዛኛው ህብረተሰብም በእንዲህ አይነቱ ህመም ምክንያት የወደቀን ሰው እንደመጀመሪያ ርዳታ እርጎ የሚጠቆመው ክብሪት ለኩሶ ወደአፍንጫው በማስጠጋት እንዲያሸተው ማድረግ ነው። ይህም ከበሽታው ጋር በተያያዘ የግንዛቤ እጥረት መኖሩን ይጠቁማል።

ምንም እንኳን ከ50 እስከ 70 ከመቶው የሚሆነው የሚጥል ህመም /epilepsy/ መንስኤ በግልፅ ባይታወቅም ከሚታወቁት መንስኤዎች ውስጥ በአንጎል ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ማለትም ስትሮክ፣ የአንጎል እጢ፣ ከባድ የጭንቅላት ጉዳት፣ የአንጎል ኢንፌክሽን ማለትም ወባ፣ ማጅራት ገትርና ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ በወሊድ ጊዜ ህፃኑ በቂ ኦክስጂን አለማግኘት ወይም መታፈን ይገኙበታል። እንደ ኦቲዝም ያሉ የነርቭ ህዋሳትን የሚገድሉ በሽታዎች፣ የአንጎል አፈጣጠር ችግር፣ የዘረመል ችግሮች ማለትም የአእምሮ ዝግመትና በአንዳንዶቹ ህመሞች በዘር መውረስ ተጨማሪ የህመሙ መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ።

ዶክተር ህሊና ዳኛቸው የኢትዮጵያ ነርቭ ሀኪሞች ማህበር ፕሬዚዳንት ናቸው። እርሳቸው እንደሚገልፁት፣ በሚጥል በሽታ ዙሪያ በኢትዮጵያ የተጠኑ ጥናቶች ረጅም ዓመት የቆዩ ናቸው። ከሰላሳ ዓመት በፊት በፕሮፌሰር ረዳ በተጠና ጥናት መሠረት እንኳን ከ100 ሺ ሰው 5 ነጥብ 2 ሰው ያክል የሚጥል ህመም አለበት ተብሎ ይገመታል። አሁን ባለው ደረጃ ግን ከአጠቃላይ ማህበረሰብ ውስጥ ከ1 እስከ 2 ከመቶው ወይም 6 ሚሊዮን የሚጠጋው የሚጥል ህመም እንዳለበት ይገመታል። የሚጥል ህመም አንድን ሰው ብቻውን የሚያጠቃ ስላልሆነና በታማሚው ዙሪያ ያለውን አካባቢና ማህረሰብንም ጭምር ስለሚያጣቃ ቢያንስ 30 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ በሚጠል ህመምና ተያያዥ ችግሮች ይጠቃ ተብሎ ይታሰባል።

የሚጥል ህመም ህክምና በአብዛኛው በመድሃኒት የሚሰጥ ነው። በርግጥ አሁን ላይ ከበፊቱ የተሻለ የመድሃኒት አማራጮች አሉ። ቅርቡ ደግሞ የሚጥል ህመም የቀዶ ህክምናዎችን ለማድረግ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ። በተለይ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚጥል ህመምን በቀዶ ህክምና ለማከም የሚደረጉ የተለያዩ የህክምና አማራጮችን ለማስጀመር ጥረቶች እየተደረጉ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ የሚጥል ህመምን ለማከም ከህክምና ባለሙያዎች በተጨማሪ የኤም አር አይና የኢ ጂ አገልግሎት ስለሚፈልግ አገልግሎቱን በተቻለ መጠን በሪፈራል ሆስፒታሎች ውስጥ እንዲኖሩ የማድረግ ሥራዎችም አብረው እየተከናወኑ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የነርቭ ሀኪሞች ቁጥርም ከበፊቱ መሻሻል አሳይቷል።

በአሁኑ ጊዜ 53 የአዋቂ የነርቭ ስፔሺያሊስት ሀኪሞች፣ 10 የውስጥ ደዌና የነርቭ ስፔሺያሊስት ሀኪሞች እንዲሁም 7 የህፃናት የነርቭ ስፔሽያሊስት ሀኪሞች አሉ። አንድ ሀኪም ለ 2 ሚሊዮን ሕዝብ ይደርሳል እንደማለት ነው። ይህ ቁጥር ግን ካለው የታካሚ ብዛት አንፃር በቂ ባለመሆኑ በቀጣይ ሰፊ ሥራ ይጠይቃል።

ፕሬዚዳንቷ እንደሚያብራሩት የሚጥል ህመም በመድሃኒት እንደሚታከም አለማወቅ ታማሚዎች ወደ ህክምና ተቋም እንዳይሄዱ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በማህበረሰቡ በኩል የሚደርስባቸው መገለልና መድልኦ ወደ ህክምና ተቋም እንዳይመጡ ያደርጋቸዋል። የሚጥል ህመም ኖሮባቸው መድሃኒቶቹ የት እንደሚገኙ ባለማወቅ በበሽታው የሚሰቃዩ አሉ።

ከዚህ አንፃር በተደጋጋሚ በልዩ ልዩ የመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ስለሚጥል በሽታ ምንንነት፣ የመድሃኒትና የህክምና አማራጮች ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ከተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት፣ የግልና የመንግሥት ተቋማት ጋር በመሆን የሚጥል ህመም ያለባቸው ሰዎች ወደ ህክምና ተቋም እንዲሄዱ የማድረግ ሥራዎችም አብረው እየተሠሩ ነው። መድሃኒቶቹን በተቻለ መጠን በጤና መድህንም ሆነ በተለያዩ የመንግሥት መድሃኒት ቤቶች በብዛት እንዲገኙ የማድረግ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

የሚታየውን የነርቭ ሀኪሞች እጥረት ከግምት ውስጥ በማስገባት በመጀመሪያ ደረጃ ህክምና ተቋማት የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችን፣ ነርሶችንና ጠቅላላ ሀኪሞችን በቂ ሥልጠና በመስጠት ምን አይነት መድሃኒት መስጠት እንዳለባቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ማስተማር፤ ሲከብዳቸው ደግሞ ማንን ማናገር እንዳለባቸው ማህበሩ ይሠራል።

በጤና ሚኒስቴር በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ሂወት ሰለሞን እንደሚናገሩት የሚጥል በሽታን በሚመለከት በኢትዮጵያ እምብዛም ሰፊ ጥናቶች አልተሰሩም። ነገር ግን አሁን ካለው መረጃ አንፃር 6 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የሚጥል በሽታ እንዳለባቸው ይገመታል።

የሚጥል በሽታ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካከል ይመደባል። ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ደግሞ ከሰው ወደ ሰው አይተላለፉም። ነገር ግን እነዚህ በሽታዎች በቁጥር እየተበራከቱ መጥተዋል። ተላላፊ ካልሆኑ በአእምሮ ላይ የሚደርሱ የተለያዩ የጤና ችግሮች መካከል ደግሞ የሚጥል በሽታ አንዱ ነው። ይህን በሽታ ያመጣሉ ተብለው የሚታሰቡ በርካታ መንስኤዎች አሉ። በዛው ልክ ደግሞ ይህ ነው ተብሎ የማይታወቅ መንስኤ እንዳለው ይታመናል።

ነገር ግን በአንጎል ላይ የሚደርስ አካላዊ ምት ወይም የአካል ጉዳት አንዱ መንስኤ ነው። በተጨማሪም ከስትሮክ ጋር በተያያዘ ቀጥታ ግንኙነት ይኖረዋል። እንዲሁም የሚጥል በሽታ አልፎ አልፎም ቢሆን ከፍተኛ የሆነና መጠኑ የጨመረ መድሃኒት ወይም አደንዛዥ እፅ አልያም ደግሞ አልኮል በከፍተኛ ደረጃ ከመውሰድ ጋር በተያያዘ በሽታው ሊከሰት ይችላል። በወሊድ ጊዜ በተለይ ደግሞ በቂ ኦክስጂን አለማግኘትም የበሽታው መንስኤ ሊሆን ይችላል። በአንጎል ላይ ያሉ የነርቭ ሴሎች ላይ የሚደርስ ጉዳት ይህን በሽታ ሊያስከትል ይችላል።

ይህ የማንቀጥቀጥ፣ የመጣልና የመሳሰሉት በሽታ ደረጃው ይለያያል። ስለዚህ በቅድሚያ ተገቢውን ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል። በህክምናም በሽታውን ማከምና መቆጣጠር ይቻላል። እስከ 80 በመቶ የሚሆነውን የበሽታውን መጠን በህክምና በሚደረግ ድጋፍ ማሻሻል ይቻላል። እንዲያም ሆኖ ግን በሽታው በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች ታዳጊ ሀገራት እንደትልቅ ችግር እየታየ ነው።

በአብዛኛውም በህብረተሰቡ ዘንድ ከእርኩስ መንፈስና ከእርግማን ጋር ተያይዞ ይታያል። በተለይ በህፃናት ላይ በሽታው ሲከሰት ወላጆችም ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ ወደ ህክምና ተቋም ልጆቻቸውን ይዞ በመሄድ የማስመርመርና ህክምናውን እንዲከታተሉ የማድረግ ልምድ የለም። ሆኖም በረጅም ጊዜ በሚወሰድ መድሃኒትና የህክምና ክትትል ታማሚውን ወደ ነበረው ጤና መመለስ ይቻላል።

መሪ ሥራ አስፈፃሚዋ እንደሚሉት ታማሚዎቹ ወደጤና ተቋማት መጥተው የህክምና አገልግሎት እንዳያገኙ በርካታ ተግዳሮቶች አሉ። አብዛኛዎቹም በህብረተሰቡ መሃል ሆነው ህክምናውን ሳያገኙ ከነችግራቸውና ጉዳታቸው አብረው የሚኖሩ ናቸው። ሆኖም ግን የህክምና አገልግሎቱ ከሌሎች የአእምሮ ጤና አገልግሎቶች ጋር አብሮ ይሰጣል። ምንም እንኳን የበሽታዎቹ ደረጃዎች ቢለያዩም አብዛኛው በመድሃኒት የሚሰጥ የህክምና አገልግሎት ነው። በሽታው ለመመርመር የሚያስችሉ መሣሪያዎችም አሉ። አልፎ አልፎ በቀዶ ህክምና የሚሰጥ የህክምና አገልግሎትም አለ።

ይሁንና አብዛኛዎቹ ታማሚዎች እንዲህ አይነቱን ህክምና አገልግሎት አያገኙም። በተለይ ህፃናት በእድሜ ገና እንደመሆናቸው በቀጣይ ሕይወታቸው ላይ በሽታው ብዙ ተፅእኖ ሊያደርስ ይችላል። በተጨማሪም ከሌሎቹ ህመሞች አንፃር ከራስ መሳት ጋር ተያይዞ ሕይወት እስከማሳጣት የሚደርስ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ስለዚህ ህመሙን በህክምና መቆጣጠር ያስፈልጋል። በማህበረሰብ ደረጃም በሚጥል በሽታ ዙሪያ የጠራ ግንዛቤ ሊኖርና ለበሽታው ተገቢውን ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል።

በተለይ ታማሚው ራሱን ስቶ በሚወድቅበት ጊዜ ሰዎች ሳይደናገጡ ተገቢውን የመጀመሪያ ርዳታ መስጠት ይኖርባቸዋል። እንዲያም ሆኖ ግን ስለበሽታው በቂ ግንዛቤ ወስዶ ድጋፍ ከማድረግ አኳያ አሁንም ብዙ ይቀራል። በሽታውን በሚመለከት በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤም ዝቅተኛ ነው። ስለዚህ የመጀመሪያ ርዳታ አሰጣጥ ላይ ብዙ መሠራት አለበት።

ለበሽታው በህክምናው ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ከማህራዊ ኑሮ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ስላለው የሥነልቦናና ማህራዊ ድጋፍ ይፈልጋል። ከህብረተሰቡ በኩልም አጋዥ ሆኖ መገኘትን ይጠይቃል። ከዚህ አንፃር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የራሱ የሆነ ድርሻ ይኖረዋል። ስለዚህ በህክምና ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ጤና ባለሙያዎችና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ሊሠሩ ይገባል።

በተለይ በትምህርት ቤቶች አካባቢ መምህራን ስለበሽታው ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል። በተማሪዎ ቻቸው ላይ ይህ በሽታ ተከስቶ ሲያዩ ምን ማድረግ እንዳለባቸውና ተማሪዎችን ጨምሮ ሌሎችም የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ግንዛቤ ኖሯቸው ደጋፊና አጋዥ እንዲሆኑ ሰፊ ሥራ መሠራት ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ ግን ከበሽታው ታማሚዎች በኩል የመገለል፣ የመገፋትና የመሳቀቅ ሁኔታ ተፈጥሮ ትምህርታቸውን እስከማቋረጥ ሊያደርሳቸው ይችላል።

እንደ መሪ ሥራ አስፈፃሚዋ ገለፃ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻለ ነገር ቢኖርም አሁንም ቢሆን ጤና ሚኒስቴር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን በበሽታው ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠርና የህክምና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ሰፋፊ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። በቅርቡም የአእምሮን ጤና በሚመለከት ሀገር አቀፍ ማስተግበሪያ ስትራቴጂ ተነድፎ ወደሥራ ተገብቷል። በስትራቴጂው የአእምሮ ጤናን በተለይ ደግሞ የሚጥል በሽታን ጭምሮ ለሌሎችንም የ ‹‹ኒዮሮሎጂካል ዲስኦርደር›› በሽታዎች በሚገባ ተካተዋል። ለስትራቴጂው ትግበራ ግን የበርካታ ባለድርሻዎችን ተሳትፎና ሥራ ይጠይቃል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን  የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You