አዲስ አበባ፡- በአገራችን የሚገኙ ከባለ አንድ እስከ ባለ አምስት ኮከብ ደረጃ ላይ ያሉ ሆቴሎች በዘርፉ የሰለጠኑ ምሩቃንን ቀጥሮ የማሰራት ፍላጎታቸው ዝቅተኛ መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የሆቴል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር ዳዊት በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ በአገራችን ያሉትና ከባለ አንድ እስከ ባለ አምስት ኮከብ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዓለምአቀፍ ሆቴሎች በዘርፉ የሰለጠኑ የሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎችን የመቅጠርና የማሰራት ፍላጎት የላቸውም።
ወይዘሮ አስቴር እንደሚሉት፤ ኢንስቲትዩቱ ባስጠናው ጥናት እንዳረጋገጠው አገሪቱ ከባለ አንድ እስከ ባለ አምስት ኮከብ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሆቴሎች ውስጥ በሥራ ላይ ከተሰማሩት ሠራተኞቻቸው መካከል በዘርፉ የሰለጠኑ 23 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው።
አብዛኞቹ ባለ ሆቴሎች ባለሙያን ቀጥሮ ከማሰራት ይልቅ ዘመድ መቅጠር ምርጫቸው ያደርጋሉ የሚሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ይህ ደግሞ ለባለሙያዎቹ የሥራ ዕድልን ካለማስገኘት፣ ቱሪስቶችን ካለመሳብና የአገር ኢኮኖሚን ከማቀ ጨጭ እንዲሁም በዘርፉ የሚሰጠውን አገልግሎት ቀልጣፋ ካለማድረጉም ባለፈ እራሳቸውን ባለ ሆቴሎቹን እና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችንም እንደሚጎዳና ከተወዳዳሪነት ውጪም እንደ ሚያርጋቸው ጠቁመዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ አስቴር አባባል፤ በየዓመቱ ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተመረቁ የሚወጡት ወጣቶች በቂ አለመሆናቸው እየታወቀ ማንም ሆቴል አይቀጥራቸውም፡፡ ዘርፉ ውጤታማና አትራፊ እንዲሆን ከተፈለገ ዘመድን በቦታው ላይ ማሰማራት ሳይሆን የሰለጠኑ ባለሙያዎችን መጠቀም ይገባል፡፡
ኢንስትቲዩቱ ከአራት ወር እስከ አራት ዓመት (ዲግሪ) ድረስ በሚወስዱ ፕሮግራሞችና በ15 የትምህርት መስኮች፤ በበቁ መምህራን የሰለጠኑ ወጣቶችን አስመርቆ ለሥራ ዝግጁ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች እነዚህን በሙያው በቂ እውቀት ያላቸውን ወጣቶች በመቅጠር ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በተለይ ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዝኛ እና ቻይንኛ እና የተለያዩ ቋንቋዎች በቂ እውቀት ያላቸውን እነዚህን ባለሙያዎች ከማፍራታችን አኳያ በሆቴልና ቱሪዝሙ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ወጣቶቹን ሊጠቀሙባቸው እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በእነዚህና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከባለሀብቶቹ ጋር በተለያዩ ጊዜያት ምክክር ማድረጋቸውን የገለፁት ወይዘሮ አስቴር፤ በተወሰኑ ባለሀብቶች አካባቢ ለውጥ በመምጣቱ በባለሙያዎች የመጠቀሙ ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱንም ተናግረዋል።
ኢንስቲቲዩቱ 50ኛ የምስረታ ኢዮቤልዩ በዓሉን ከሰኔ 1 ቀን እስከ 3 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች እያከበረ የሚገኝ ሲሆን ከፕሮግራሞቹም አንዱ በሆቴል እና ቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችንና ተመራቂ ተማሪዎችን በማገናኘት የጋራ ውይይት በማድረግ ምሩቃኑ የሥራ ዕድል የሚያገኙበትን፤ ዘርፉም የበለጠ የሚለማበትን ሁኔታ ማመቻቸት መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2011
ግርማ መንግሥቴ