አዲስ አበባ፡- አገርም ካላት ባህላዊ ሀብት እንድትጠቀም ለማስቻል ምርቱና አምራቹ የሚገኙበት ላይ በመድረስ የደላላን ጣልቃ ገብነት እንደሚያስቀር ተጠቆመ።
በባህል ልማት ላይ የሚሰሩ አካላትን ያሳተፈ መድረክ ሰሞኑን በወላይታ ሶዶ ከተማ በተደረገበት ወቅት የዝግጅቱ አስተባባሪ ዶክተር ልደቱ አፈወርቅ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ እንዲህ ዓይነት ዝግጅቶች የኅብረተሰቡን ዋነኛ ችግር መፍቻ ናቸው። አምራችና ነጋዴውን ያለምንም ጣልቃገብነት ያገናኛሉ።
የውጭ ዜጎች ሳይቀሩም አምራቹ ጋር ምን እንዳለ እንዲረዱም ያደርጋል። ይህ ደግሞ ለአምራቹ ተጠቃሚነት በር ከመክፈቱ ባሻገር የደላላን ጣልቃ ገብነት ያስቀራል።
እንደዚህ ዓይነት መድረክ በሽመናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ሥራቸው እንዲታይና የገበያ አማራጭ እንዲያገኙ ዕድል ይሰጣቸዋል የሚሉት ዶክተር ልደቱ፤ ተማሪዎችም ቢሆኑ ልምድ የሚቀስሙበት መሆኑን ተናግረዋል። የወላይታ ባህል እንዲተዋወቅና አልሚዎችና ነጋዴዎች ያለማንም ጣልቃ ገብነት ከአምራቹ ምርትን ተቀብለው ትርፋማ እንዲሆኑ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።
በወላይታ ሶዶ ከተማ የሰላም ፌስቲቫሏን ያዘጋጀችው ዓለምአቀፏ ሞዴሊስትና ዲዛይነር የክብር ዶክተር ሰናይት ማሪዮ በበኩሏ እንደተናገረችው፤ አምራች ሥራዎቹ በዲዛይነሮችና በሞዴሊስቶች ታግዞለት ለገበያው ከተዋወቀ ሥራውን ወዶት ይሰራል። ጥቅም ሲያገኝ ደግሞ የበለጠ ጥበባዊ ሥራውን ያጎላበታል። በመሆኑም እንዲህ ዓይነት ተግባራት ከከተማ ዝግጅትነታቸው ወጥተው አምራቹ ጋር መድረስ አለባቸው።
እንደ ዲዛይነር ሰናይት ገለጻ፤ «ዓለም የሚያውቀን እኛ አምራቹን ይዘን ስንጓዝና ራሳችንን ስንሸጥ ነው። ነገር ግን ብቻዬን ልብላው የምንል ከሆነ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታችን በእጅ አዙር ለውጭው እንሰጣለን።
ምክንያቱም ብዙ የውጭ ዜጎች ዛሬ አምራቹን አግኝተው በቀጥታ ግዥ እየፈጸሙና ደላላን ከውስጣቸው እያራቁ ነው። አገራቸው ወስደውም በዶላር መልሰው እየሸጡልን ይገኛሉ። ስለዚህም መንቃትና አምራቹን ከእነጥሬ ሀብቱ መያዝ ይጠበቃል።»
አገሪቱ በአልባሳት ዲዛይንም ይሁን በጥሬ ዕቃ አቅርቦት ብዙ የተሻሉ ነገሮች ቢኖሯትም በኢኮኖሚው ተጠቃሚነቷ ግን የሚገባትን ያህል አላገኘችም የሚሉት ደግሞ የዚሁ ፌስቲቫል አዘጋጅ ኮሚቴ ኢንጅነር በጸጋው አክሊሉ ናቸው።
የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱ በሚገባ ሊረጋገጥ ያልቻለው አምራቹን ያሳተፈ ሥራ ባለመሰራቱ እንደሆነ የሚያነሱት ኢንጅነሩ፤ ደላላ ገብ ሥራዎች በብዛት በመንሰራፋታቸው ሸማኔው ወይም አምራቹ የልፋቱን ያህል አላገኘም። ብዙ ዲዛይነሮችም ሆነ ሞዴሎች ደግሞ ሥራዎቻቸውን የሚያሳዩት ከተማ ላይ ብቻ ነው።
በዚህም ታች ያለው አምራች በቴሌቪዥን ካልሆነ በስተቀር በሌላ መልኩ ሥራዎቹን የሚያይበት ሁኔታ የለም። በዚህም የዘወትር ድካሙን ብቻ ይዞ ይጓዛል። ስለሆነም እንዲህ ያሉ ሥራዎች መለመድ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው