አዲስ አበባ፡- በተለያየ ስም የሚጠሩ የአሰሪዎች ኮንፌዴሬሽኖች እንዲዋሃዱና ለአንድ ዓላማ እንዲሰሩ ተጠየቀ፡፡
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ይመር በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ትልቅ ሥራ መሥራት የሚቻለው በአንድነትና በመተባበር ነው።
የተለያየ የአሰሪ ኮንፌዴሬሽን ሆኖ መሥራት አስቸጋሪ እንደሚሆንና በተለያየ ኮንፌዴሬሽን የሚነሳው ጉዳይም የተበታተነ ስለሚሆን የሠራተኛው ተወካይ የሚሰጠው ምላሽ ለሕዝብም ሆነ ለኮንፌዴሬሽኖች አጥጋቢ እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡
አዳዲስ የሚመጡ ኮንፌዴሬሽኖችም እንደሚዋሃዱ የጠየቁት አቶ ታደለ፣ የኮንፌዴሬሽኑ ዋና ዓላማ አንድ ሆኖ ሰላምን ማስፈንና የአሰሪዎችንና ሠራተኞችን መብት ማስጠበቅ ነው ብለዋል፡፡ አዲስ የተቀየሰው አሠራርም በተለያየ ስያሜ የተበታተኑ ማህበራትና ፌዴሬሽኖችንም ወደ አንድ ያመጣል፡፡ ለዚህም አሁን የሚዋሃደው ኮንፌዴሬሽን ምሳሌ ሆኖ መታየት አለበት ነው ያሉት፡፡
እንደ አቶ ታደለ ገለፃ፤ ኮንፌዴሬሽኑ አምስት የቴክኒክ ኮሚቴዎችን ይመርጣል። የተመረጡ የቴክኒክ ኮሚቴዎች የሚዋሃዱ ኮንፌዴሬሽች የሚጠሩበትን ስምና ሕገ ማህበር በማጽደቅ የጋራ ጉባኤ እንዲኖራቸው ይደረጋል፡፡ የተመረጠው የቴክኒክ ኮሚቴም በቅርቡ ሥራውን ይጀምራል ብለዋል፡፡
የአዳማ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ኑሪት አባዝናብ በበኩላቸው፤ የኮንፌዴሬሽኑ መቋቋም ችግሮች ሲኖሩ በጋራ በመፍታት በአሰሪውም ሆነ ሠራተኛው ላይ ያለውን ጫና ለማቃለል ያግዛል፡፡ በሠራተኛውም ችግሮች ሲያጋጥሙ በጋራ ለመፍታት አንድነት ያስፈልጋል፡፡
እስካሁን የነበረው የተለያየ ኮንፌዴሬሽን መሆን በአሰሪው መካከል የተለያየ ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል። መዋሃዱ ግን ለትብብርና ለአሠራር እንደሚያመች ነው ምክትል ፕሬዚዳንቷ የተናገሩት፡፡ ሠራተኛውም መብቱን ማስከበር የሚያስችል ሁኔታ ይፈጠርለታል።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን፤ የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን፣ የአዳማ አሰሪዎች ፌዴሬሽን፣ የቢሾፍቱ አሰሪዎች ፌዴሬሽን፣ የሐረሪ አሰሪዎች ፌዴሬሽን፣ የድሬዳዋ አሰሪዎች ፌዴሬሽን፣ የጋምቤላ አሰሪዎች ፌዴሬሽን፣ የጅማ አሰሪዎች ፌዴሬሽን እና የትግራይ አሠሪዎች ፌዴሬሽንን በውስጡ ይዟል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2011
ዋለልኝ አየለ