አዲስ አበባ፡- በግል ትምህርት ቤቶች ያለውን ትምህርት አሰጣጥና ጥራት ያለበትን ደረጃ ለማወቅ መንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው ተገለጸ፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀውን የግል ትምህርት ቤቶች ኤግዚቢሽን ያዘጋጀው የኤድቬት አዲስ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ብሌን ምስክር እንዳሉት፤ የግል ትምህርት ቤቶች ከመንግሥት ጋር ተቀራርበው በመስራት የትምህርት ጥራት እንዲመጣ መስራት አለባቸው፡፡ ለዚህም እንዲረዳ በግል ትምህርት ቤቶች መካከል ያለውን የትምህርት አሰጣጥና ጥራት ደረጃ ለማወቅ አላማ ያደረገ ኤግዚቢሽን እንዲዘጋጅ ተደርጓል፡፡
በኤግዚቢሽኑ በአዲስ አበባ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች የሚሰጡት አገልግሎት እንዴት እንደሆነ፣ ብቁ ዜጋ ለማፍራት የትምህርት አሰጣጡ ምን እንደሚመስል፣ ወላጆች ልጆቻቸው ስለሚማሩበት ትምህርት ቤት ምን ያክል ያውቃሉ እንዲሁም በአሁን ወቅት በግል ትምህርት ቤቶች ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች እንዴት ይታያሉ? የሚሉ ጉዳዮች በውይይት መልክ እንደቀረቡ ወይዘሮ ብሌን አመልክተዋል፡፡
በግል ትምህርት ቤቶች ኢግዚቢሽን ላይ በርካታ ትምህርት ቤቶች እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቦላቸው እንደነበር በመጥቀስ፤ ከፈተና መቃረብና በሌሎች ጉዳዮች የተፈለገውን ያክል ትምህርት ቤቶች አለመሳተፋቸውን ጠቅሰዋል። በቀጣይ ዓመት በሚደረገው ኤግዚቢሽን ላይ ትምህርት ቤቶቹ እንዲሳተፉ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አበበ ቸርነት በበኩላቸው፤ ለአገሪቱ ትምህርት እድገት የግል ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ ይህንን አስተዋፅኦ ይበልጥ ለማሳደግ የትምህርት አሰጣጣቸውን የሚያሳይ ኤግዚቢሽን መዘጋጀቱ ጥቅሙ የጎላ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በግል ትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚነሱ የክፍያ መናሮችን ለመቆጣጠር ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ተግባር ላይ የዋለው መመሪያ ውጤት ማምጣቱን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ወላጆች ከትምህርት ቤቶች ጋር ተቀራርበው የሚሰሩበት ሁኔታ ለማመቻቸትና የሚፈጠሩ ቅሬታዎችን ለመቀነስ የከተማ አስተዳደሩ የመፍትሄ ሃሳብ እያዘጋጀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በቀጣይ የግል ትምህርት ቤቶች አንድ ላይ በመሆን ተመሳሳይ ኤግዚቢሽኖች በማቅረብ ለኅብረተሰቡ ስለአሠራራቸው ማሳወቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2011
መርድ ክፍሉ