‹‹ብቁዋ ሴት ማጀት እንዳትቀር በሴት አክባሪ ሴቶች ትደገፍ›› ወይዘሮ ሲና ጌታቸው የሚዲያ ማናጀር

በትምህርት እውቀት ያካበቱ፣ በተሰማሩበት የሙያ ዘርፍም ችሎታ ያዳበሩ ሰዎች የሀገር ባለውለታና የሕዝብ አለኝታ እንዲሆኑ ይታሰባል። ሀገርም በእውቀት ከመጠቁት በትምህርት ካደጉት ዜጎቿ ብዙ ትጠብቃለች። ይሁን እንጂ የመማር እድሉን አግኝተው በትምህርት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ አንዳንድ ሴቶች ሀገርና ሕዝብ የሚጠብቅባቸውን ሲወጡ አይስተዋሉም።

ምክንያቱ ደግሞ እናት ከመሆን ጋር የተያያዘ ነው። እናት በመሆናቸው ብቻ በተማሩት ትምህርት ሀገራቸውን ሳያገለግሉ። ራሳቸውንም በኢኮኖሚ ሳያሳድጉ ልጅ በማሳደግ በቤት ውስጥ ተወስነው ይቀራሉ። ምን ያህሉ ሴቶች በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ጥናት የሚያስፈልግ ቢሆንም ጥቂት እንዳልሆኑ ግን አሁን እየታየ ካለው ነባራዊ ሁኔታ መገንዘብ ይቻላል።

ልጅን በማሳደግ ቤተሰብን መንከባከብ ሴቶች ከፍተኛው ድርሻ እንዳላቸው ይታወቃል። ግን ደግሞ በጤናው ዘርፍ ተምራ ብዙዎችን ትታደጋለች ተብላ የምትጠበቅ ሐኪም ልጅ በመውለድ ምክንያት በቤት ውስጥ መወሰኗ ምን ያህል አግባብነት አለው? ጥያቄ ይፈጥራል። እንደ ሀገር ሲታሰብም ጉዳቱ ከፍተኛ ነው። የሕክምና ትምህርት ለመማር የተማረችው ሴት ድካም ብቻ ሳይሆን፤ ለትምህርት የወጣው ወጪ ጥቅም ላይ ሳይውል ባክኖ መቅረቱ ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም አንፃር ጉዳት አለው።

የተነሳው ርዕሰ ጉዳይ በቀላሉ የሚታለፍ ጉዳይ እንዳልሆነም በችግሩ ውስጥ ያሉት ሴቶች ሲያነሱት አሳሳቢነቱን መገንዘብ ይቻላል። ተምረው ግን ልጅ በመውለዳቸው ምክንያት በተማሩት ትምህርት ሥራ መሥራት ካልቻሉትና ልጅ በማሳደግ በቤት ውስጥ ከተወሰኑት መካከል አንዷ ከሆነችው ወይዘሮ መክሊት አየነው ጋር ተጨዋውተናል።

ወይዘሮ መክሊት በመካከለኛ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ ሴት ናት። እናቷ የቤት እመቤት ናቸው። አባቷ ደግሞ የሕክምና ባለሙያ ናቸው። ከአምስት ልጆች መካከል ሶስተኛ ልጅ ናት። ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ የሚቻለው በትምህርት ብቻ እንደሆነ ከቤተሰቦችዋ እየሰማች ነው ያደገቸው። እርስዋም በትምህርቷ ጠንክራ ውጤታማ ለመሆን ለትምህርቷ ትኩረት ሰጥታ ቀን ተሌት ነበር በጥናትና በንባብ የምታሳልፈው።

ወይዘሮ መክሊት ለትምህርቷ ጊዜ ብትሰጥም፤ በቤት ውስጥ የሚያስጨንቃት ነገር ደግሞ የመማር ጉጉቷን መጨመሩንም ታስታውሳለች። እናቷ ልጆች ለማሳደግ፣ በተለይም በወር መጨረሻ ላይ ጓዳቸው ጎሎ ለማሟላት ሲጨነቁ ታይ ስለነበር እናቷን ከጭንቀታቸው ለማውጣት ነበር ህልሟ። እድል ቀንቷትም በትምህርቷ ገፍታ በመጀመሪያ ዲግሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመረቀች።

ከፍ ማለት፤ የተሻለች ሆና ለመገኘት የነበራት ህልሟንም ለማሳካት ትምህርት ተቀዳሚ ምርጫዬ ነው ያለችው ወጣት ወዲያው ነበር ሁለተኛ ዲግሪዋን ለማግኘት የተመዘገበችው። የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን በመከታተል ላይ እያለች ነበር ከልጅነት ጓደኛዋ ጋር ወደ ትዳር የገባችው። ትዳር መያዝዋ ግን የጀመረችውን ትምህርት ከማጠናቀቅ አላገዳትም። ይሁን እንጂ በተማረችው ትምህርት ሥራ ለመሥራት አልወሰነችም። በወቅቱ “አንደኛሽን ወልደሽ ሥራ ትፈለጊያለሽ” የሚል አስተያየት የበዛ ስለነበር እርሷም ተቀበለችው። በተከታታይ ሶስት ልጆች ወለደች።

እርስዋ እንዳለችው፤ የትዳር መጀመሪያ አካባቢ ሁሉ የሞላላት የቤት እመቤት እንደሆነች ዓይነት ስሜት ነው የነበራት። ውሎ ሲያድር ግን የእሷ መማርና የሁለት ዲግሪ ባለቤት መሆን ካልተማረቸው እናቷ የተለየ ሕይወት ሊሰጣት ያለመቻሉ ነገር ውስጧን ይከነከናት ገባ።

ልጅ በልጅ ላይ ሲደራረብ በአንድ ሰው አቅም ቤተሰብን እንደ ልብ መምራት ሲያቅት ቤት ያለው ጭቅጭቅ እየጨመረ ቤተሰቡ ደስተኝነቱ እየጠፋ እሷም ያላሰበችው ዓይነት የእእምሮ ውጥረት ውስጥ ልተገባ ቻለች። በራሷ ሰርታ ማግኘት ባለመቻሏና የሌላ ሰው እጅ ጠባቂ መሆኗ ከእለት ወደ እለት እያስከፋት መጣ።

ያንን ታግላ ለማሸነፍ ብታስብም እችላለሁ የሚል አስተሳሰብ ከውስጧ ቀስ በቀስ ወጥቶ በራስ መተማመኗ መጥፋቱን ታስተውላለች። ወይዘሮ መክሊት ደጋግሞ መውለድ ያመጣባት ድባቴ፤ የኢኮኖሚ ጥገኝነቱ፤ የማኅበረስብ ጫናን መቋቋም አቅቷት እጅግ ከባድ የሚባሉ ቀናትን አሳልፋ እንደነበረ ታስታውሳለች።

በትምህርትም፤ በደረጃም ከእሷ ጋር ከማይስተካከሉ ሰዎች ጋር መዋሏ ለዓመታት የለፋችበት የትምህርቷ ነገር በዜሮ መባዛቱን ስታስብ ነበር ከባድ ሀዘን ውስጥ የገባችው። ያኔ ነው አብረዋት የተማሩት ከሷ ቀድመው ሥራ የያዙ ጓደኞቿ በሰጧት ልባዊ ድጋፍ ተገፋፍታ ከጓዳ የወጣችው። ሰፊ ቀሚሷን አውልቃ በሥራ ልብስ አደባባይ መውጣቷን ማመን እስኪያቀታት ድረስ እጅግ ብዙ ከባድ የሕይወት ትግልን አሳልፋ ኃላፊነት ቦታ የደረሰችው።

ሴቶች ለልጅ ብለው ከከፍተኛ ኃላፊነታቸው የወረዱ፤ ተምረው ጓዳ የዋሉ እናቶችን ዳግም በልበ ሙሉነት ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ሊያደርግ የሚችል ተቋም ቢኖር ስትል ምኞቷን ተናገራለች።

በርካታ የመክሊት ዓይነት እናቶች ከሁለት ዲግሪ በላይ ይዘው ልጅ በማሳደግ ሰበብ ቤት ከዋሉ በኋላ በተለያዩ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ ስር በመውደቃቸው በራስ መተማመናቸው ሲጠፋ መታየቱንም፤ በተለያዩ እናቶች ሃሳባቸውን በሚያካፍሉበት ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ለመመልከት ይቻላል። እናት እናትን ብትደግፍ፤ ሴት አክባሪ ሴት ብትፈጠር፤ ሀገር ካላት ላይ በርካታ ገንዘብ ያፈሰሰችባቸው የተማሩ ሴቶች ቤት ከመቀረት አደባባይ ወጥተው ማገልግለ ይጀምራሉ።

ሌላዋ ባለታሪካችን ይህ ጉዳዬ ነው ያለች ተምሮ ቤት መቅረት በእኔ ይብቃ ያለች፤ ቤት የቀሩ የተማሩ ሴቶችን አነቃቅቶ አደባባይ ማውጣትን ዓላማው አድርጎ የሚንቀሳቀስ “ሴት አክባሪ ሴት” የሚል መሪ ሃሳብ ያለው ፕሮጀክት ቀርፃ መንቀሳቀስ ጀመረች። በፕሮጀክቱ የተማሩ አቅም ያላቸው እናቶች ጓዳ አይቅሩ የምትለን የአንድ ሰው ፕሮሞሽንና ኢቨንት ሚዲያ ማናጀር የሆነችው ወይዘሮ ሲና ጌታቸው ናት። ይህች ሴት “የሴት አክባሪ ሴት” የተባለው ፕሮጀክት ኃላፊ ናት።

ይህን ፕሮጀክት እንድታስብ ያደረጋት በሙሉ ጊዜ የእናትነት ወቅት ልጆቿ ሲተኙ የተለያዩ ፊልሞችና ድራማዎች ስትፅፍ የቆየች ሲሆን፤ ሥራዎቿ እጇ ላይ ሲጠራቀሙ ልጆቿ እያደጉ ቢሄዱም ወደ ሥራ ለመመለስ ማሰብ ብትጀመርም ወደ ሥራዋ እንድትመለስ የሚያበረታት ሁኔታም ሆነ ሰው ከጎኗ ታጣለች።

እናቷ እህቶቿ በአጠቃላይ ዙሪያዋ ያሉ ሰዎች በሙሉ ሴት ካገባችና ከወለደች በኋላ ባለቤቷንና ልጆቿን መንከባከብ ብቻ ይበቃታል የሚል አስተሳሰብ ይዘው የመውጣት ፍላጎቷን እንድታቆም ይጎተግቷት ጀመር። ያኔ ነው እንግዲህ ለአርት የተፈጠረችው ይች ሴት ቢያንስ የፃፈቻቸው ጽሑፎች ለመድረክ መብቃት ይኖርባቸዋል የሚል ሃሳብ ይዛ ተነሳች።

እናትነት፤ ለቤተሰብ ኃላፊ፤ ለባልም ጥሩ ሚስት መሆን ጥሩ ቢሆንም እየሠሩ ያንን ማድረግ መቻል የሚቻል መሆንን ለማየት በማህበራዊ ሚዲያ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ማውራት ጀመረች። ያኔ ብዙ ሰዎች ልጆቼ ሲያድጉ ወደ ሥራ እመለሳለሁ ብለው ቤታቸው ቢቀሩም መልሶ መውጣት ግን እጅግ አስቸጋሪ የሚሆንባቸው ብዙ ሴቶች በየቤታቸው እንዳሉ ታውቃለች።

አብዛኛዎቹ ሴቶች ገንዘብ አግኝተው በራሳቸው ገንዘብ በርካታ ነገሮችን ሲደርጉ ቆይተው አሁን ግን ተቀባይ መሆን ሲጀመሩ በራስ መተማመናቸው መጥፋትና ደስ የማይል ስሜት ውስጥ መግባት ይጀምራሉ። ሴት ልጅ ውጭ ውላ ስትገባ ራሷን እንደምትጠብቀው ቤት ስትውል ግን የቤት ውስጥ ሥራ ጫና ጋር ራሷን መጣል በዛው ለራሷ ያላት ግምት የመውረድ ዓይነት ባህሪ ታሳያለች።

የተማረች ሴት ልጆቿ ካደጉ በኋላ እንኳን ወጥታ ለመሥራት ያላት ፍላጎት እየጠፋ ትናንት የነበረችበት አቋም እየወረደ ሲሄድ በትዳር አጋሮች በኩልም የሚመጡ ጫናዎች ይበዛሉ። የተቀባይነት መንፈሱና አልችልም የሚለው ስሜት እያደገ መምጣቱ በራሱ ከባድ መሆን ይጀምራል ትለናለች። ያኔ ልጆቿ አድገው ትምህርት ቤት ሲገቡ ነበር ከወሊድ በኋላ ካለው ድባቴ ውስጥ ለመውጣት መታገል የጀመረችው።

ይህን ሥራ ስታስብ የአስራ ሶስት ዓመት ሴት ልጇ ሴት ልጅ መውለዷ ካሰበችው ሕልም ሊያስቀራት የማይችል መሆኑን ለማሳየት ብሎም እሷን መሰሎችን አቅም ሆና ካሉበት ማህበራዊና ሥነ ልቦናዊ ተፅእኖ ገፍታ መውጣት ጀመረች። ለራስ ችግር እራስ ካልበረቱ ማንም ሰው እጅን ይዞ ሊያስወጣ የማይችል መሆኑን በማወቅ ሴት አክባሪ ሴት በሚል ቀድመው የወጡቱ ቤት የቀሩትን ሴቶች አቅም በማጎልበት አደባባይ እንዲወጡ የማገዝ ሥራ ላይ ተሰማራች።

እናትነት በራሱ የሚያመጣቸው ተፅእኖ በላይ ያለው ሥነ ልቦናዊ ጫና ከባድ መሆኑን ለማሸነፍ ስትሞከር እራሳቸው ሴቶቹ ጉዳዩን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸው ሥራው እንዳይሳካ አድርጎት እንደነበረ ሲና ትናገራለች።

ዳግም የመወለድ ያህል ሕይወትን እንደገና ለመጀመር የምትተጋውን ሴት በቅድሚያ የማነቃቂያ ሥልጠናዎችን መስጠት ማኅበረሰቡም ግንዛቤው ከፍ እንዲል የተለያዩ ዓይነት ሥልጠናዎች በሴት አክባሪ ሴት ፕሮጀክት ስር እንዲሰጥ መሥራት ጀመረች።

ሴት አክባሪ ሴት የሚለው ሃሳብ የተነሳው ሴቶች ራሳቸው ሌሎች ሴቶች አይችሉም የሚል አመለካከት ከውስጣቸው አውጥተው በመደጋገፍ ችግሮቻቸውን በመጋፈጥ ፊት መቆም እንደሚገባቸው ለማሳየት ነው የምትለው ወይዘሮ ሲና ይህንን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ የተለያዩ ኪነጥበባዊ መድረኮች፤ ድራማዎችና ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በሰፊው እየሠራች ትገኛለች።

ከክፍለ ከተሞች ከሴቶች ጉዳይ ጋር ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ሥራውን ያስጀመረችው ወይዘሮ ሲና አንዲት ሴት ልጆቼ አድገዋል ይበቃል መውጣትና መሥራት አለብኝ ብላ ለመነሳት የሌላዋ ጠንካራ ሴት ድጋፍ እንድትሰጥ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ይሰራል።

ይህ ሃሳብ የተነሳው እህቷ ላይ በር የምትዘጋ ሳይሆን፤ እህቷን የምትደገፍ ትውልድን ያፈራች ለሀገር ተረካቢ አበራካች የሆነች እናትን ሴቶች በራሳቸው ተደጋግፈው መቆም የሚችሉበት ምቹ ሁኔታን መፈጠር ነው። ሴቶች እናትነት የተሰጣቸው ትልቅ ፀጋ ሲሆን፤ እናት በመሆናቸው የተነሳ የተለያዩ ጫናዎች እንዳይፈጠርባቸው መደጋገፍ ላይ መሥራት ይገባል።

መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሚወለዱ እናቶች የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑ ያስመሰግንዋል የምትለው ሲና የወሊድ ፍቃድ ወደ አራት ወር ማደጉ፤ የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የሕፃናት ማቆያ መቋቋሙ ይበል የሚያሰኝ ነው። ሴቶች እናት በመሆናቸው ብቻ ያለችው አቅም ይወርዳል ብለው የሚያስቡ ሰዎችም ይበልጥ ኃላፊነት የሚሰማት መሆኑን ተርደተው ለተሻለ ኃላፊነት የማጨት ልምድ እንዲኖር መደረግ አለበት። አሁን የበቃች ሴት ወለድኩ በሚል ምክንያት ጓዳዋ እንዳትቀር በርካታ ሴት አክባሪ ሴቶች መፈጠር ይገባቸዋል ብላለች።

እኛም ትልቅ ፀጋ የሆነው እናትነት የሴትን ስኬት ወደኋላ እንዳይጎተት የበቃች ልጆቿን እያሳደገችም ሀገር የምትመራ ሴት ትኖር ዘንድ ሴቶች ራሳቸው ለሴቶች ይቁም እላለሁ።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2016 ዓ.ም

Recommended For You