አዲስ አበባ:- የተፈጥሮ ሀብታችን በአያያዝ፣ አጠቃቀምና አመራር ችግር እና የአየር ለውጥ ሳቢያ የከፋ አደጋ ላይ በመሆናቸው ሁሉም እንዲታደጋቸው ጥሪ ቀረበ።
የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪና በኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት የአየር ንብረት ሳይንስ ምርምር ዳይሬክተር ዶ/ር አደፍርስ ወርቁ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፣ ከደን ሀብታችን ከሰል እየተጠቀምን በመሆኑ በቀጣይ አደጋ ላይ ነው። ስለሆነም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመቀናጀት ሊታደጓቸው ይገባል ብለዋል።
እንደ ተመራማሪው ገለጻ፣ ከዛሬ 16 እና 17 ዓመት በፊት ስምጥ ሸለቆ አካባቢ ያሉ ወንዞች (የዝዋይ፣ ላንጋኖ …) በግራር ዛፍ ተሸፍነው አይታዩም ነበር። አሁን አንድ ቦታ ቆሞ ወይም በመኪና ሲታለፍ ሁሉንም በቀላሉ ማየት ይቻላል። ይህም ምን ያህል የደን ሀብታችን እንደተመናመነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል።
የአብያታ ሐይቅ በ40 ዓመት ጊዜ ውስጥ 477 ሄክታር የውሃ አካሉ የብስ ሆኗል፤ ምናልባትም በዚሁ ከቀጠለ ከ40 ዓመት በኋላ ይህ ሐይቅ ጭራሹንም ሊጠፋ ይችላል፤ ልክ እንደ ሃሮማያ ሐይቅም ታሪክ ሆኖ ሊቀር ነው የሚሉት ዶ/ር አደፍርስ «ድሮ የቆቃ ግድብ አጠገባችን ሆኖ ነበር የምንመለከተው፤ አሁን ሐይቁ አይታይም። ውሃ በደንብ ሲይዝ የነበረው ጥልቅ ገንዳ ዛሬ የእርሻ መሬት ሆኗል።» ሲሉም የቆቃን ድሮና ዘንድሮ በማነጻጸር የአደጋውን አሳሳቢነት አብራርተዋል።
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ከጥቂት ዓመታት በፊት ጥልቀታቸው 15 እና 16 ሜትር የነበሩ ሐይቆቻችን ዛሬ ሁለትና ሦስት ሜትር ጥልቀት ላይ ይገኛሉ። ውሃው ሲሸሽ፤ ዙሪያውን ሲታረስ፤ በደለል እየተሞላ ሲሄድ፤ የመጨረሻው ውጤት ውሃ የሚጠራቀምበት ጥልቀት ያለው ስፍራ ያጣና ሳይጠራቀም ይቀራል። ከዚያ ሐይቆቹ ወደ ሜዳነት እየተቀየሩ ይሄዳሉ። አሁን ደግሞ እምቦጭ አረም መጣ። ሐይቆች የሚጠፉት በዚህ መልኩ መሆኑን በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል።
ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት፣ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር፣ ሠራተኛና የተማረ የሰው ኃይል፣ እያለን መጠቀም አልቻልንም። አገራት አንድ ወንዝ ይዘው የትና የት ሲደርሱ፤ እኛ ግን ይሄንን ሁሉ ጋራና ተራራ ይዘን በደን ባለመሸፈናችን፣ በአንድ ቦታ ስንትና ስንት ጅረቶችን ይዘን ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም መቀየር አልቻልንም።
ያለን የደን ሀብት በአግባቡ ባለመመራቱ ተጠቃሚ ከመሆን ይልቅ ዳር ላይ ቆመን እየተመለከትን እንገኛለን የሚሉት ዶ/ር አደፍርስ፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከዚህ ችግር እንደምንወጣና የተሻለ ውጤት እንደምናመጣ የተናገሩ ሲሆን፤ በተለይም የዶ/ር አቢይ መንግሥት ወደ ኃላፊነት መምጣት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ተፈጥሮ ሀብቶቻችን ለመታደግ በቅንጅት የተሻለ ሥራ መስራት ይቻላል፤ ለዚህም የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላትና መላው ሕዝብ የየድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2011
ግርማ መንግስቴ