አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ የሚገኙ የሦስት ወረዳዎች የወጣት ማዕከላት ለወረዳ አስተዳደር ቢሮነት በመዋላቸው ለወጣቱ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑ ተገለጸ።
በአዲስ አበባ ከተማ የወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ የወጣት ማዕከላት አገልግሎት ማስተባበሪያ ክትትል ቡድን መሪ አቶ ጤናዬ ታምሩ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንዳሉት፤ የካ ክፍለከተማ ወረዳ አራት፣ ቦሌ ክፍለከተማ ወረዳ ዘጠኝ እና ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለከተማ ወረዳ ሁለት የሚገኙ ወጣት ማዕከላት ለወረዳ አስተዳደሩ ቢሮነት እያለገሉ ይገኛሉ። በዚህም ለወጣቱ የተፈለገውን አገልግሎት እየሰጡ አይደለም።
እንደ አቶ ጤናዬ ገለፃ፤ ወረዳዎቹ የሥልጠና፣ የሥራና የቢሮ ጥበት ሲኖር ወጣት ማዕከል ውስጥ የሚገኙ ክፍሎችን ይወስዳሉ።ችግሩን ለመፍታት ለወረዳ አስተዳደሮቹ ደብዳቤ በመፃፍና በአካል ተገናኝቶ ውይይት ተደርጓል። ወረዳዎቹ እድሳት ላይ ስላለን ታገሱን የሚል መልስ ብቻ በመስጠት እስካሁን ሊለቁ አልቻሉም።
በኮልፌ ቀራንዮ ወረዳ ሁለት ወጣት ማዕከሉን የወረዳው አስተዳደር ለቢሮነት እየተጠቀመበት ይገኛል። እንዲወጡ ሲጠየቁ አዲስ ሕንፃ እያስገነባን በመሆኑ እስኪያልቅ ጠብቁ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። እነዚህ ችግሮች ወጣት ማዕከላቱ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዳይሰጡ አድርጓቸው።
ወጣት ማዕከላት ሲገነቡ በዋነኛነት ለወጣቱ አገልግሎት ለመስጠት ነው የሚሉት አቶ ጤናዬ፤ ነገር ግን ከባለሙያ እጥረትና በግብዓት ችግር ምክንያት በአግባቡ አገልግሎት የማይሰጥባቸው አካባቢዎች እንዳሉ አመልክተዋል። ማዕከላቱ ሲመሰረቱ ለወጣቱ አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ በመሆኑ ባላቸው ሀብት አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ጤናዬ አባባል፤ ወጣት ማዕከላት መዝናኛ ቦታዎች አይደሉም። በማዕከላቱ የሚሰጡ አገልግሎቶች የወጣቱን ሰብዕና የሚገነቡ፣ ክህሎታቸውን የሚያሳድጉና ግንዛቤ የሚያስጨብጡ አገልግሎቶች ናቸው። ለምሳሌ ቤተመጽሐፍት፣ የኢንተርኔት አገልግሎት፣ መሠረታዊ የኮምፒዩተር ሥልጠና፣ የጤና ምርመራና የኤች.አይ.ቪ ምክር አገልግሎት እንዲሁም የአመራርና የሕይወት ክህሎት ሥልጠናዎች ይሰጣሉ።
ከኢኖቬሽንና ከቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሳይንስ ካፌ ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው። በዚህም ወጣቱ የፈጠራና የምርምር እውቀቱን እንዲያሳድግ ወጣት ማዕከላት በዘመናዊ መንገድ እየታደሱ ይገኛሉ።
በአዲስ አበባ ውስጥ በ104 ወረዳዎች ላይ ወጣት ማዕከል ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2011
መርድ ክፍሉ