ወርቁን ማን ሰወረው?

በመጀመሪያም ጥበብ ከዓለም ላይ ነበረች፤ ጥበብም ከኢትዮጵያ እጅ ነበረች፤ ብንል ምኑ ጋር ይሆን ግነቱ? አዎን ለነበር ያልራቅን ወርቁን ጥለን ጨርቁን የታቀፍን ስለመሆናችን የምንክደው ሀቅ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን በኪነ ጥበቡም፤ በሥነ ጥበቡም፤ በሥነ ውበቱም፤ በሥነ ፈለኩም ታላቅና ገናና ያደረጋት እንቁ ወርቅ ስለመኖሩ፤ ዛሬ ግን ከስፍራው ስለመሰወሩና መጥፋቱ ይገባናል። ታዲያ ወርቁን ማንስ ሰለበው? ሰላቢው ሰይጣን? እግዜር? የምድር ቤርሙዳ ወይንስ እኛው እራሳችን? ምላሹ ቀርቶ ጥያቄው በራሱ አይነኬ መስሎ መቆየቱ አስገራሚ ነው፡፡

ከጣልናቸው የዘመን ወርቆች መካከል አንደኛው ከስድስተኛው እስከ አስረኛው ክፍለ ዘመን ባለው ውስጥ ይገኛል፡፡ ዛሬ ላይ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሆነን ያንን ዘመን ያስናፈቀን፤ ያስመኘን ጉዳይ ቀላል አይደለም። ወደኋላ ዞረን የጣልነውን ወርቅ ለማንሳት ተገደናል። በየዘመናቱ ቁጭት እያሳከካቸው ለፍለጋ የወጡ ብዙዎች ቢሆኑም፤ በስኬትና በድል ለመመለስ ሳይችሉ ቀርተዋል።

በመጀመሪያም ኢትዮጵያ ዓለምን ሁሉ በቀደምትነት የምትመራበት የጥበብ፣ የእውቀት፣ የፍልስፍናና የሥነ ፈለክ በትር ነበራት፤ ያውም የወርቅ በትር፡፡ በኪናዊ ጥበብ ዓለምን የምታሻግርበት የሙሴ በትር ከእጇ ላይ ጠፍቷል። የብዙ ዓለማት ዓይንም ከዚሁ እጇ ላይ ነበር። እየዳበሱና እያባበሉም ዘመናትን ተሻግሮ አስጣሏት። እነርሱም ይቀራመቱት ጀመሩ። ሀገራችን ኢትዮጵያ ፊደላትን ቀርጻ መጻሕፍትንና ልዩ ልዩ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን መሥራት ከጀመረች 2 ሺህ ዓመታት ገደማ ቢሆንም አሁን የምናገኛቸው ግን እጅግ ጥቂቶቹን ነው፡፡ ታዲያ ቀሪዎቹስ? ምናልባትም የእንቅልፍ ሸለብታ ውስጥ ሳትገባ አልቀረችም። ከሞቀው አልጋ ላይ በእንቅልፍ ሰመመን አስምጠው ፤ በቀስታ ከእቅፏ የነበረውን ወርቅ በመውሰድ እንደ ሕፃን ልጅ አሻንጉሊቱን አስታቀፏት። እየዘገየች በባነነች ቁጥር፤ ጠያቂዎች ብቅ እያሉ ለምን? ማለት ከጀመሩ የዛሬ አይደለም፤ እልፍ ዓመታትን ተሻግሯል።

በጥንታዊ ሥነ ጥበብና ኪነ ጥበብ የዓለም እራስ የነበረችው ኢትዮጵያ፤ ዛሬ ለምን የዓለም ጭራ ሆነች? ጥያቄው ዛሬ ላይ በቁጭት እያንገበገበ፤ ቆይቶም እንደ ሳማ እያቃጠለን አለ። ከእነዚያ ሁሉ የተሰወሩ ወርቆች መካከል፤ አንደኛውን በዛሬው የዘመን ጥበብ እልፍኛችን እንስተናገድበታለን። ርዕሰ ጉዳዩ በዋናነት ከ6ኛው እስከ 10ኛው ክፍለ ዘመን በነበረው ወርቃማ የጥበብ ወንበር ላይ ያስቀምጠናል። ከዚሁ ዱካ አረፍ ብለን የዘመን እልፍኙን ጣራና ግርግዳ፤ ዙሪያ ገባውን ስንቃኝ፤ ቅዱስ ያሬድ የዚህ እልፍኝ ምሰሶ ሆኖ እናገኘዋለን። ያሬዳዊ የዜማ፣ የሥነ ውበትና የፍልስፍና ቅስቶች እልፍኙን ስለመሸከማቸው እንረዳለን። “የሰው ወርቅ አያደምቅ” የምንል ሕዝቦች “ከእጅ ያለ ወርቅ እንደ መዳብ…” ሆኖብን የጣልነው አንደኛው የዘመን ወርቅ ይሄው ነው። ባስታወስነው መጠን በቁጭት የማሳከኩ መጠን አድምቶ እባጭ የሚያስወጣ ቢሆንም፤ ነገር ግን በየዘመናቱ ውስጣቸውን እየበላው፤ በትንሹም ቢሆን ሲያኩና ሲያሹ ያለፉ ትውልዶች ነበሩ።

በዚህኛው ትውልድ ወርቁን ፍለጋ ለመውጣት ከወዲሁ የተዘጋጁ ስለመኖራቸው ሰምተናል። ሁለት ተቋማት በአንድነት በመጣመር፤ “የቅዱስ ያሬድ ወርቃማ አስተምህሮ የኢትዮጵያን ወርቃማ ዘመን ለመዋጀት” የሚል መሠረታዊ ዓላማን አንግበው ተነስተዋል። አንደኛው፤ በኢትዮጵያ ዘመን ተሻጋሪ የሥነ ጽሑፍና ጥንታዊ የጥበብ ሀብቶችን በማሰባሰብና በመጠበቅ ለትውልድ የማስተላለፍ ሥራ እየሰራ ያለው የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት(ወመዘክር) ነው።

ሁለተኛው ተቋም ደግሞ የኢትዮጵያ ያሬዳዊ ጥበብ፣ ሥነ ውበትና ክዋኔ ጥበብ ማበልጸጊያ ድርጅት ይሰኛል። ከመነሻው የተቋቋመበት ዓላማም ከጣልናቸው ወርቆች አንዱ የሆነውን ያሬዳዊውን የሕይወት መርህና የጥበብ ሥራዎች ከተቀበሩበት ቆፍሮ በማውጣት፤ ሀገራችንን ዳግም ወደ ከፍታው መመለስ ነው። አመሠራረቱም ለሁለት አስርተ ዓመታት ያህል ስለ ጉዳዩ በግልና በጋራ ሲብከነከኑና ለምን እያሉ ሲጠይቁ በነበሩ ጠያቂዎች ነው። ሕጋዊ ማንነቱ ተረጋግጦለት ሥራውን በውል ከጀመረ ግን ገና ሁለት ዓመታትን ለማስቆጠር ከጫፍ ደርሷል።

እነዚህን ሁለት አካላት በአንድ ዓላማ ያጣመረው እንቅስቃሴም ትልሙን ተልሞ ግቡን ለመምታት ጉዞውን ጀምሯል። ለዚህም ይመስላል ሁለቱ ተቋማት ከአንድ ጣራ በታች ተሰባስበው የምክረ ሃሳብ ጉባኤ ማዘጋጀታቸው፡፡ የካቲት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ለያሬዳዊው ጥበብ ባለድርሻ የሆኑትን አካላትን በማከል፤ በወመዘክር የስብሰባ አዳራሽ ተገናኝተው በርካታ ሃሳቦችን እያነሱ የእንቅስቃሴውን ጉዞ ለማቃናት መንገዱን ጠርገውበታል፡፡ በሙዚቃው ዘርፍ ያሉትን ጨምሮ፤ በርከት ያሉ የኪነ ጥበብና የታሪክ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጥሪው የደረሳቸው ሊህቃንም በመድረኩ ላይ ተገኝተዋል፡፡

መጋቤ ምስጢር አፈወርቅ ተክሌ የቅዱስ ያሬድን ትሩፋቶች እያስታወሱ ሰፋ ያለ ዳሰሳ አቅርበውበታል። ጸሀፊ ተውኔት አያልነህ ሙላት ያሬድን ምን ያህል እናውቀዋለን? ሲሉ የቅዱስ ያሬድን ማንነትና የዛሬውን ትውልድ እይታ አመልክተውበታል፡፡ አንጋፋው ጋዜጠኛ ንጉሤ አክሊሉ ደግሞ ወግ አዘል ሃሳባዊ ማዕድቸውን በቅኝታዊ ዜማ ለታዳሚው አቅርበውለታል፡፡

የቅዱስ ያሬድ እውቀትና ጥበብ፤ ኢትዮጵያን እንደምን ያቀናታል? በሚለው ጥያቄ ዛቢያ እየተሽከረከሩ፤ ልጅ ወንድሜ ላእከማርያም ጥናታዊ ዳሰሳቸውን አስደምጠውበታል፡፡ በዕለቱ፤ የቅዱስ ያሬድን ሙዚቃዊ ቃና እያስማገ፤ በሙያዊ ትንታኔ የዜማውን ዓለም ያስጎበኘው ሌላኛው የጥበብ ሰው ሠርጸ ፍሬ ስብሐት ነበር፡፡ የያሬድ የሙዚቃ ሽታ በዛሬው የዘመናዊ ሙዚቃ ውስጥ ጭምር መዓዛው የሚያውድ ስለመሆኑ በአንክሮ አስቀምጦታል፡፡

በጉባኤው የነበሩት እኚህና ሌሎች ጉዳዮችም በሙሉ የጠፋውን ወርቅ ፍለጋ የሚዳክሩ ነበሩ፡፡ ከእነዚህ የታላቅነትን ፍለጋ ጉዞዎች መካከል ከነበሩት ግብሮች፤ አንደኛው አንኳር ነጥብ በወመዘክር የሚገኙትን፤ ጥንታዊ የግዕዝና የአረብኛ መጻሕፍትን መጎብኘት ነበር፡፡ በዚህም ከጅማና ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲዎች በመጡ ምሁራን አጋፋሪነት በቅርሶቹ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተውበታል። ከሥዕላዊ መግለጫ ጋር በብራና ሰፍረው የሚገኙት እኚህ መጻሕፍትም፤ የጥንቱን አባቶቻችንን ኪናዊ ጥበብ ቁልጭ አድርገው ከማሳየታቸውም፤ ወርቁን ፍለጋ ለሚደረገው ጉዞ በወኔና በሞራል የሚቀሰቅሱ፤ አልፎም በቁጭት የሚያሳክኩ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የታሪክ ምህዋር ውስጥ የአክሱም ዘመነ መንግሥት የክርስትናው እሳት የተቀጣጠለበት ስለመሆኑ ይነገራል። በዚህ የክርስትና ወላፈን ሲበስል የነበረው መንፈሳዊው ስንቅ ብቻም ሳይሆን ኪናዊው የጥበብ አገልግልም ጭምር ነበር። በዚያ ዘመን ከነበሩ የምንጊዜም የጥበብ ፈርጦች አንዱና ዋነኛው፤ ታላቁ ባለቅኔ ቅዱስ ያሬድ ነው። በዘመኑ ያሬድ ብቻውን አልነበረም፤ ይልቅስ የእርሱ ስም በተነሳ ቁጥር በግራና በቀኝ የነበሩ ሁለት ምርኩዞቹ አብረው ይወሳሉ።

የመጀመሪያው አፄ ገ/መስቀል ሲሆኑ ሁለተኛው ሰው ደግሞ አቡነ አረጋዊ ናቸው። አፄው በመሪነቱ፤ አቡኑም በመንፈሳዊነቱ ይታወቁ እንጂ፤ እንደ ያሬድ በቀጥታም ባይሆን በእጃዙር ከጥበብ ጋር ቁርኝት ነበራቸው። እነዚህ ሦስት ሰዎች ወዳጅነታቸው የላቀ በመሆኑ እጅና ጓንት ሆነው፤ በሦስት ማዕዘን ሀገርን ለመሥራት ሲታትሩ ነበር። እናም በ6ኛው ክፍለ ዘመን መነሻውን ከቤተ ክርስቲያን በማድረግ የተነሳው የጥበብ ትኩሳት እንዳማረበት እስከ 10ኛው ክፍለ ዘመን ለመድረስ ችሏል። በተለይ በትኩሳቱ የመጨረሻ ዘመን አካባቢ በቤተ ክርስቲያን ብቻም ሳይሆን በውጭ የነበረው ፍካትም ቀላል የሚባል አልነበረም።

ዛሬ ፍለጋ የወጣንለት የያሬድ ወርቅ እያደር በውጭ እየደበዘዘ ከቤተ ክርስቲያን እጅ ላይ ብቻ ለመውደቅ ተገደደ። የዜማ ቅኔው፣ እውቀትና የአስተምህሮ ፍልስፍናው ሁሉ ለመንፈሳዊ ግብር እንጂ ለሌላ የማይሆን መስሎ ታየ። በዚህ ምክንያትም ሙሉ አደራና ኃላፊነቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሆኗል። ቤተ ክርስቲያኗም ይህን ታላቅ አደራ ጠብቃ ዛሬም ድረስ ለማቆየቷ ኪናዊ ምስጋና ይገባታል። ነገር ግን ወርቁን በባለቤትነት እንደመያዟ፤ ከቤተክርስቲያኗ ውጭ እንዲወጣ ያላት ፈቃደኝነት ምንስ ያህል ነው?

የያሬድ ሥራዎች እንዲወጡና ዓለም እንዲያውቃቸው ባለመደረጉ ያጣነው ብዙ ነው። ለአብነትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘመናዊ የሙዚቃ ኖታ የታወቀው በ10ኛው ክፍለ ዘመን በጣሊያናዊ የሙዚቃ ሊቅ ጊዶ አሪዞ እንደሆነ ነው። ዓለምም የምታወቀው የመጀመሪያው ባለኖታ ሙዚቀኛ ይኸው ጣሊያናዊ ነው። ቅሉ ዓለም ሁሉ ይህንኑ ይበል እንጂ፤ ወደኛ መለስ ስንል ከእርሱ አምስት ክፍለ ዘመናትን ቀደም ብሎ ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ ነበረ፡፡ ያሬድ በ6ኛው ክፍለ ዘመን ብቅ ያለ የሙዚቃ ሊቅ ነበር።

በሁለቱም መካከል ያለው የዘመን ርቀት ፈጽሞ የሚገናኝ አይደለም፡፡ ጊዶ የመጣው ከያሬድ አራት ያህል ምእተ ዓመታትን ዘግይቶ ነው። ወርቁን ከእጃችን ተነጥቀናል፤ አሊያም ጥለነዋል፡፡ ስለዚህ የገሀድ ሀቅ ብናውጠነጥን በየትኛው የሂሳብ ቀመር ነው ይህ ጣሊያናዊ የመጀመሪያው ሊሆን የሚችለው? እኛስ ብንሆን ግዙፍ እውነታ ይዘን በዝምታ የተቀበልነው፤ ለዚህ የሚሆን ተጨባጭ ማስረጃ ስላጣን? ወይንስ ከቁብ ሳንቆጥረው ስለቀረን? ጥያቄው ለትዝብታችን ይሁን፡፡

ታዲያ የያሬድ የኖታ ዜማዎች እጅግ በርካታ የነበሩ ቢሆንም በዋናነት ግን ዜማዎቹ ከነ ኖታ ምልክቶቻቸው የተቀመጡ አምስት የዜማ ድርሰቶቹ ዛሬም ተጠቃሽ ናቸው። ከሁሉም በፊት፤ በመጀመሪያም ቅዱስ ያሬድ ስለመኖሩና የዓለም የዘመናዊ ሙዚቃ አባት ስለመሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም። ችግሩ ግን ነብይ በሀገሩ አይከበርምና “ባለቤቱ ያቀለለውን… ባለእዳ አይመልሰውም” የያሬድም ጉዳይ እንዲያ ነው፤ በእጅ የነበረው ወርቅ እንደ መዳብ ተቆጥሮ ዓለም እንዳታውቀው ሆኗል።

የቅዱስ ያሬድን የዘመን ጥበብ፤ ዛሬም መንፈሳዊ እንደሆነ ብቻ የምናስብ ብዙ ነን። በከፊል ልክ ብንሆንም ከእውነታው ግን አጉድለናል። ምክንያቱም አራቱን የኢትዮጵያ ሙዚቃ ቅኝቶችን ብንመለከት ከያሬድ የዜማ ስልት የወጡ መሆናቸውን እንረዳለን። የያሬዳዊው “ግዕዝ” ከአንቺሆዬ የዜማ ስልት ጋር ልክክ ብሎ የሚሄድ ነው። “አራራይ” መልከ ቁመናው የትዝታን ባህሪ የተላበሰ ነው። በሦስተኛ ደረጃ “እዝል”ን እናገኘዋለን። የእዝል የዜማ ቅኝት በባህሪው አድቦ ከአንድ የማይረግጥና በሁለት ቅኝቶች መካከል ማለትም ከአንቺሆዬና ከትዝታ ቤት የሚመላለስ ጣፋጭ የዜማ ስልት ነው።

ታዲያ ባይነገርለትም ያሬድ በእነዚህ ቅኝቶች ውስጥም አለ። መሆን ያለበትን ያህል ባይሆንም በተለይ ቆየት ባሉት የሙዚቃ ሥራዎች ውስጥ የያሬዳዊ የዜማ ስልቶች በጉልህ እናገኛቸዋለን። ለአብነትም የጥላሁን ገሠሠን “ጥላ ከለላዬ” እንዲሁም የቴዎድሮስ ታደሰን “አጉል ተቆራኝቶ” የሚሉትን ዜማዎች ለማንሳት እንችላለን። ከዚህም ባለፈ በቲያትር ጥበባት ውስጥ ያሬዳዊ ዜማዎችን መጠቀም የተለመደ ነው። የያሬድን የወርቅ ስጦታዎች ውስጥ ውስጡን ላይ ላዩን እንደ ወርቅ ቅብ ብንጠቀመውም፤ ለረዥም ዘመናት እውነተኛውን ውድ ማንነት ሳናወጣው ቀርተን ያጣነው ብዙ ነው።

እንግዲህ ነገር በነገር ሲደራረት፤ ከላይ የጠቀስናቸውን ወርቁን ፍለጋ የወጡትን ሁለቱን አካላት እንዳንዘነጋ፡፡ በኢትዮጵያ ያሬዳዊ ጥበብ፤ ሥነ ውበትና ክዋኔ ማበልጸጊያ ድርጅት ፊታውራሪነትና በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት(ወመዘክር) አሳላጭነት እየተካሄደ ያለው ፍለጋ ህልምና ትልሙ ብዙ ነው፡፡ ወርቅ ተይዞ ሁለተኛ እንቅልፍ መቼስ የማይሆን ነው፡፡

ትላንትን በመፈለግ ሂደት ውስጥ ትልቁ ነገር ከትላንት ለመማር ዝግጁ መሆን ነው፡፡ በሁሉም የፍለጋ መስመሮች፤ ከፊትም ሆነ ከኋላ ባለው ሃሳብ ውስጥ፤ ያሬዳዊውን እውቀትና ጥበብ ማውጣት የመጀመሪያው እንጂ የመጨረሻው ግብ አይደለም፡፡ ትልቁ ዓላማ የእርሱን ሀገር አቅኚ የተፈጥሮና ማህበራዊ ሳይንስ፣ የጥበብ፣ የሥነ ምግባር፣ የሥነ ውበትና ክዋኔ ጥበብ ፍልስፍና፣ የሥነ ፈለክ እንዲሁም የባህልና እሴት አስተምሮዎቹን በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ዳግም ትንሳኤን መፍጠር ነው፡፡

ዳግም ትንሳኤ ካለ አስቀድሞ ሞት ነበር ማለት ነውና መቼ ነበር የሞተችው? ካልን… በኪነ ጥበቡም ቀደምት፤ በሥልጣኔውም ቀደምት፤ በእውቀቱም ቀደምት፤ ቀደምት…ቀደምት…ቀደምት… የምንላት ሀገር፤ አሁን ከቀደምትነት ወደ ጭራነት ተለውጣ፤ “ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነኑኝ” በማለት ላይ ያለችን ሀገር ከሞትና ትንሳኤ ውጭ ምንስ ሊገልጻት ይችላልና፡፡ እውነት ነው፤ ይህ የትንሳኤ አብዮት ከ6ኛው እስከ 10ኛው ክፍለ ዘመን የነበረውን እሳት ለመሞቅ የሚያስመኝ ነው፡፡

የሆነው ሆነና በሁለቱ አካላት የወርቅ ፍለጋ ውስጥ፤ ለማሳካት ከሚዳክሯቸው ነጥቦች መካከል…የኢትዮጵያን ወርቃማ ዘመን በመናኘት ወደ ቀድሞ ክብሯ መመለስ፤ በሀገር በቀል እውቀትና ጥበብ የተካነ ትውልድ መፍጠር፤ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ዳግም በመስቀል በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትፈራና ስሟ የናኘ ሀገርን መፍጠር፤ የዜጎችን የሥራ ባህል መቀየርና በጠነከረ ማህበራዊ ሕይወት ማስተሳሰር የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

እውነትም የጠፋውን ይህን ወርቅ በማግኘት እንደተነሱበት ዓላማ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታው ማማ ያሻግሯት ይሆን? ምናልባትም ወደፊት የምናየው ይሆናል።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን የካቲት 28/2016 ዓ.ም

Recommended For You