አዳማ፡– በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አማካይነት የተቋቋመው ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የሁለቱን ክልሎች ሰላምና ልማት ከማጠናከር አኳያ ላቅ ያለ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ ተገለጸ፡፡
ሰላም ሚኒስቴር ከኦሮሚያና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሰላምና የልማት የጋራ ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤትና ከጋምቤላ ክልል ጋር በመተባበር በጥምረት በተዘጋጀ መድረክ ላይ እንደተገለፀው፤ በዋናነት የመድረኩ ተዋናይ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ናቸው። መድረኩ በዋናነት በሁለቱ ክልሎች መካከል ሰላምንና ልማትን ለማረጋገጥ የተዘጋጀ ነው፡፡
በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ የጋራ የመንገድ ፕሮጀክት፣ የመስኖ ፕሮጀክት እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብት ፓርኮች እንዲኖራቸው ለማድረግም የሚያግዝ በመሆኑ በድህነት ውስጥ ያሉትን አጎራባች ሕዝቦች የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው፡፡
ዶክተር ግርማ እንዳሉት፤ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ በእስካሁኑ ሂደቱ የሁለቱን ክልል ግንኙነት በእቅድ እንዲመራ አስችሏል፤ ሌላው ለረጅም ጊዜ ጥያቄ የሆኑ ጉዳዮች መመለስ ጀምረዋል። ለአብነትም አፋን ኦሮሞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ትምህርት እየተሰጠበት ይገኛል፡፡ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተፈናቀሉ አካላትም ሙሉ ለሙሉ ወደየቀያቸው መመለስ ችለዋል፡፡
«በቀጣይ የሚታሰበውና በዋናነት የሚያተኩረው በአካባቢው ያሉትን ሀብቶችና ጸጋዎች እንዴት አድርገን ለጋራ ልማት እናውል የሚለውን በማጤን ኅብረተሰቡ በጋራ እንዲያለማ፣ እንዲያድግና እንዲበለፅግ ለማድረግ ነው፡፡»ያሉት ዶክተር ግርማ፣ በዚህ ዓመት ከጋምቤላ ክልል ጋር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል። የጋምቤላ ክልል በዚህ መድረክ የመሳተፉ ምስጢርም ከመድረኩ ልምድ ቀምረው ለቀጣይ እንዲዘጋጁ በመታሰቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዕለቱ «የፌዴራሊዝምና የመንግሥታት ግንኙነት ጽንሰ ሐሳብ» በሚል ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት በሰላም ሚኒስቴር ፌዴራሊዚም አስተምሮና ስርፀት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ጥላሁን እንደተናገሩት፤ የትብብር መድረኩ በሰላም ጉዳይ እንዴት ይሰራ የሚለውን የሚመለከት ነው፡፡
«አብዛኛውን ጊዜ በሁለቱ ክልሎች አጎራባቾች መካከል ችግሮች አሉ፡፡» ያሉት ዳይሬክተሩ ከዚህ ችግር ጋር ተያይዞም ብዙ ልማቶች የወደሙበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡ ያንን ችግር ለመቅረፍ የዕለቱ መድረክ አጋዥ ከመሆኑም በተጨማሪ ቀጣይነት እንዲኖረውም ለማድረግ መታሰቡን ተናግረዋል፡፡ ሰላም ከመታጣት የተነሳ የወደመ ንብረት መኖሩ የሚታወቅ ሲሆን፣ ያ እንዳይደገም የቀረበ የጋራ የምክክር መድረክ እንደመሆኑ ግንዛቤ በመጨበጥ በቀጣይ ግንኙነቱን የተሻለ ለማድረግ መጣር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ እንደ ሰላም ሚኒስቴር እየታሰበ ያለው ጉዳይ የሁለቱ ክልሎች ግንኙነቶች ሥርዓት ባለው መንገድ መደበኛ እንዲሆን ነው። ችግርን በዋናነት የሚፈታው ሥርዓት ወዳለው አሠራር መሄድ ሲቻል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ጉዳይ አሁን ላይ ተጀምሯል፡፡ ግንኙነታቸውንም የተሻለ ለማድረግ ጥረቶች እየታዩ ነው፡፡ ችግሮች ሳይባባሱ እንዴት ቶሎ ማስቀረት እንደሚቻልም ነው የተለያዩ ጽሑፎች የመቅርባቸው ፋይዳ፡፡
አቶ ገዛኸኝ፣ «የማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱን ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ ጀምረውታል፡፡ ይህን ጉዳይ በተለይ በምዕራቡ በኩል እንዲሁም አማራ ክልልን በመጨመር ማስፋት ያስፈልጋል። እንዲሁም ጋምቤላንም በመጨመር ሥራውን በማስፋት አለመግባባትን ለመቅረፍ ነው መሰራት ያበለት፡፡» ብለዋል፡፡
እርሳቸው እንዳሉት፤ ጋምቤላ ክልል የመድረኩ ተካፋይ እንዲሆን የተደረገው ውይይቱን በመከታተል የቀረበውን ሪፖርትና የታቀደውንም እቅድ በመገንዘብ ልምድ እንዲቀስምና በቀጣይም ዝግጁ እንዲሆን በማሰብ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በቀጣይ ጋምቤላ መሰል ሥራዎችን ከኦሮሚያ ጋር እንዲያደርግ ይፈለጋል፡፡ ይህም ጉዳይ በቀጣይ በአገር አቀፍ ደረጃም እንዲሰፋ ይደረጋል፡፡
በዕለቱ መድረክ ላይ የፌዴራሊዝምና የመንግሥታት ግንኙነት ፅንሰ ሐሳብ፣ የምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪካዊና ሁለንተናዊ ግንኙነት ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ በተሳታፊዎቹ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡
እንዲሁም የማስተባበያ ጽሕፈት ቤቱ የ2011 ዓ.ም የእቅድ አፈፃፀምና እና የ2012 ዓ.ም የእቅድ ዝግጅት ቀርቧል፡፡ መድረኩ ዛሬም ቀጥሎ እንደሚውል የታወቀ ሲሆን፣ ተሳታፊዎቹም የየክልሎቹ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ በአጎራባች በኩል በየደረጃው ያሉ በሰላምና ልማቱ በኩል የሚመለከታቸው አመራሮች የተገኙበት መድረክ ሲሆን፣ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተወከሉም አካላት ተገኝተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት ሰኔ 2/2011
አስቴር ኤልያስ
ፎቶ በገባቦ ገብሬ